ከአስር ቀናት በፊት ዳሬሰላም ላይ ታግቶ የነበረው ታንዛኒያዊው ወጣት ቢሊየነር ከእገታ መለቀቁ ተሰማ፡፡ ዜናውን በአደኛው ድርጅቱ የትዊተር አድራሻ ላይ ያበሰረው ባለሃብቱ እራሱ መሀመድ ዴውጂ ሲሆን፥ በሰላም ወደ ቤቱ መመለሱን በመልዕቱ አስታውቋል፡፡

ባለሃብቱ የሀገሪቱን ፖሊስና በዓለም ዙሪያ አብረውት በጸሎት ለነበሩት ምስጋና አቅርቧል፡፡ የ43 ዓመቱ ቢሊየነር እስከአሁን ድረስ በምን መልኩ እንደተለቀቀ የታንዛኒያ ፖሊስ ያለው ነገር የለም ተብሏል፡፡

ወጣቱ ቢሊየነር  ከአስር ቀናት በፊት ወደ ስራ በሚጓዝበት ወቅት ነበር ዳሬሰላም ላይ የመታገቱ ዜና የተሰማው፡፡ በወቅቱ ከእገታው ጋር ተያይዞ ሶስት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው የነበረ ሲሆን፥ ከአጋቾቹ መካከልም ሁለቱ የውጭ ሀገር ዜጎች ሳይሆኑ አይቀርም ሲል ፖሊስ ማስታወቁ ይታወሳል።

ቢሊየነሩ ወጣት በጨርቃጨርቅ፣ በከፍተኛ የግብርና ምርቶች፣ በመጠጥት ኢንዱስትሪ እና በምግብ ዘይት ምርቶች ላይ በስድስት የአፍሪካ ሀገራት እንደተሰማራም ተነግሯል።

ግለሰቡ በ2016 ግማሽ ሀብቱን የሰዎችን ህይወት ለሚያሻሽሉ የሰብዓዊ  ፕሮግራሞች ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባቱን መረጃዎች ያመለክታሉ።

ፎርብስ መፅሄት በ1 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ሀብት ብቸኛው ታንዛናዊ ቢሊየነር መሆኑን   ያስታወቀ ሲሆን፥ በፈረንጆቹ 2017 አፍሪካዊ ወጣት ቢሊየነር መባሉም ተነግሯል።

ምንጭ፦ FBC

በአብርሃም ፈቀደ

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *