በራያ አላማጣ ከማንነት ጋር በተያያዘ የደረሰውን ጉዳት አስመልክቶ መግለጫ ያወጣው የትግራይ ክልል መስጠንቀቂያ ሰጠ። “…በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ኢጁን ያስገባ አካል በቸልታ እንደማያልፈው በዚህ አጋጣሚ ይገልፃል ” ብሏል። ሕዝብ የመከላከያ ሰራዊት ጣልቃ እንዲገባ መጠየቁን የአማራ ክልል ቲቪ ሲዘግብ፣ ተጎጂዎች ስከሬን ለመቅበር እንኳን አልቻልንም እያሉ ነው። የመንግስት ሚዲያዎችም ሆኑ ባለስልጣናት ጉዳዩን አስመልክቶ ያሉት ነገር የለም።

የትግራይ ክልል መንግስት ባወጣው ወቅታዊ መግለጫ ሶስት ሰዎች መሞታቸውን ይፋ አድርጓል። መግለጫው ህይወታቸው ያለፈው ዜጎች የት እንደተገደሉ ቦታውን አላመላከተም። የአማራ ማስሚዲያ በበኩሉ ከማንነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ በራያ አላማጣ ሰዎች መገደላቸውንና መቁሰላቸውን ከስፍራው ሰዎችን በማነጋገር ዘግቧል። በዘገባው ጥቃቱን ያደረሱት የታጠቁ ሃይሎች መሆናቸውን ከመጥቀስ ውጪ ታጣቂዎቹን በስም አላነሳም። የጉዳቱን መጠንም በአሃዝ አላብራራም።

ከስፍራው በስልክ ሲናገሩ የተደመጡ ነዋሪዎች እንዳሉት የደረሰው ጉዳትና አደጋ ከባድ ነው። በጥይት ተመተው የቆሰሉት ቁጥር ከፍተኛ ነው። በከተማዋ ወጣቶች እየታፈሱ ወደማይታወቅ አካባቢ ይጋዛሉ። ተሰብስቦ መሄድ ሰላማይቻል ቀብር ለማካሄድ እንኳን አልቻሉም።  እነሱ እንደሚሉት ጥያቄያቸው ሰላማዊና ህገ መንግስታዊ የማንነት ጥያቄ ነው። የትግራይ ክልል ባወጣው መግለጫ እንዳለው ጥያቄውን የማንነት በማስመሰል የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የተደረገ ነው።

ችግሩ እየከፋና እየተባባሰ ቢሄድም የፌደራል መንግስት ዝምታ ብዙዎችን አስገርሟል። ነዋሪዎች እንዳሉት ጥያቄያቸው በሰላማዊና ህገ መንግስታዊ በሆነ መንገድ እንዲፈታ አገር የሚያስተዳድረው አካል ዝምታን መምረጡ ቅሬታን ፈጥሯል። የአማራ ክልላዊ መንግስት ” አማራ ነን” ለሚሉት የህብረተሰብ ክፍሎች ጥያቄና አሁን እየደረሰ ባለው ጉዳት ዙሪያ እስካሁን በይፋ ያለው ነገር የለም።

አቶ ንጉሱ ጥላሁን ” ራያ አላማጣ በተፈጠረው ግጭት የሰው ህይወት ጠፍቷል፣ አካልም ጎድሏል። ችግሩ ህዝብን በማዳመጥ እንጂ በሀይል አማራጭ በፍፁም አይፈታም። ፈጥነን ህዝብን ማዳመጥ እና መፍትሄም መስጠት አማራጭ የሌለው አማራጭ ነው”  ሲሉ በፌስ ቡክ ገጻቸው ላይ የግላቸውን አስተያየት አትመዋል።

የትግራይ ክልል ጉዳዩን የሚያየው ከማንነት ጥያቄ አንሳር ባለመሆኑ፣ በዚህ ጉዳይ እጃቸውን ያስገቡትን በሙሉ በቸልታ እንደማያይ ነው በመግለጫው መጨረሻ ላይ ያመለከተው። በደፈናው በቸልታ እንደማያይ ከመግለጽ ውጪ ምን አይነት እርምጃ እንደሚወስድ፣ ከድርጊቱ ጀርባ አሉ ስላላቸው ሃይሎች አላብራራም። መግለጫው ሶስት ሰዎች መሞታቸውን ሲገልጽ፣ በስም ያልጠራቸውን የራሱ ክልል ልዩ ሃይል አካላት ስለመጠያቃቸው ያለው ነገር የለም።  

በትናንትናው እለት የመከላከያ ሰራዊት ወደ ከተማዋ ገብቶ የማረጋጋት ስራ እየሰራ ነው መባሉን ነዋሪዎች አስተባብለዋል። የመከላከያ ሰራዊት መለዮና ዩኒፎርም ለብሰው የገቡት የትግራይ ክልል ልዩ ሃይል መሆናቸውን ጠቁመው፣ መንግስት ይድረስልን ሲሉ ሲማጸኑ ኢሳት ካስተላለፈው ዘገባ ለማዳመጥ ተችሏል።

የወልቃይት ጠገዴ፣ የራያ፣የኩናማ፣የኢሮብ ፣የአገው እና አፋር ህዝቦች የማንነትና  ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ከትግራይ ክልል ጋር በተያያዘ የሚነሱ ሲሆኑ፣ በሌሎችም አካባቢዎች ተመሳሳይ ጥያቄዎች ስላሉ በአገር ደረጃ  አጠቃላይ መፍትሄ  ማፈላለጉ ግድ መሆኑንን የተለያዩ ባለሙያዎች ሲገልጹ መቆየታቸው የሚታወስ ነው።

 የራያ አላማጣ የማንነት ጥያቄ ሊታፈን እንደማይገባ የቆቦ ከተማ ነዋሪዎች ጠየቁ።

Related stories   ሰበር ዜና – ትህነግ በዲፕሎማሲ ዘመቻ ቀውስ ገጠመው፤ “ በሃሰት መረጃ አሳፈራችሁን ” የቅርብ አጋሮቻቸው

ባሕር ዳር፡ጥቅምት 11/2011 ዓ.ም(አብመድ) የራያ አላማጣ ነዋሪዎች ማንነታችን አማራ በመሆኑ ሊከበርልን ይገባል ሲሉ በተደጋጋሚ እየጠየቁ ይገኛሉ። ይሁን እንጂ እንግልት እና ወከባ እየደረሰባቸው መሆኑን ነው የሚናገሩት። አላማጣ ላይ ከትናንት ምሽት ጀምሮ የፀጥታ ችግር መኖሩንና ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች መኖራቸውንም ከአካባቢው የዓይን እማኞች ነግረውናል።

ስለ ጉዳዩ የጠየቅናቸው የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ በአካባቢው ስለሌሉ መረጃ መስጠት እንደማይችሉ ነው የተናገሩት። የቆቦ ከተማ ነዋሪዎችም ዛሬ በሰላማዊ ሰልፍ ድርጊቱን አውግዘዋል። “ማንነታቸውን ስለጠየቁ መብታቸው ሊታፈን፣ ሊንገላቱ እና ሊዋከቡ አይገባም” ሲሉ ነው የጠየቁት።

ከዚህ በፊት ስለ ጉዳዩ የተጠየቀው የትግራይ ክልል መንግስት “ጥያቄው ከማንነት ጋር አይያያዝም” ማለቱ ይታወሳል። ነዋሪዎቹ ግን ጥያቄያቸው የማንነት እና የነፃነት መሆኑን ነው የሚያስረዱት። በሰልፉ “ጣናና ላል ይበላን እንታደግ!” የሚሉ መልዕክቶችንም አስተላልፈዋል።

 

Related stories   መከላከያ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ “ጁንታውን” ሙሉ በሙሉ መደምሰሱን አስታወቀ! በርካታ በቁጥጥር ስር ውለዋል

የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ወቅታዊ መግለጫ

ዛሬ ጥቅምት 11 ቀን 2011ዓ.ም በአላማጣ ከተማ በማንነት ስም በሚንቀሳቀሱ አካላት እና በፀጥታ ኃይሎች መካከል በተፈጠረው አለመግባባት የሶስት ሰዎች ህይወት አልፏል። በፀጥታ አካላት ላይም ጉዳት ደርሷል።

የህዝብን የማንነት ጥያቄ በማስመሰል ሌላ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት እየተደረገ ያለው ሩጫ በማንኛውም መመዘኛ ተቀባይነት የሌለው ተግባር ነው። ይህ ሳያንስ የዜጎች ሰላም፣ ፀጥታና ደህንነት ለመጠበቅ ከተሰማራው የፀጥታ መዋቅር ጋር መጋጨትና አነሳስቶ እርምጃ እንዲውስድ መግፋት ደግሞ በፍፁም መደገም የሌለበት ተግባር ነው። በዚህ ሁኔታ የሶስት ሰዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትም በሁኔታው መረራ ሐዘን እንደተሰማው እየገለፀ ለቤተሰቦቻቸውንም መፅናናትን ተመኝቷል።

ማንኛውም ጥያቄ ያለው አካል ሕጋዊና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ጥያቄውን ማቅረብና መልስ ማግኘት በሚቻልበት ክልል ውስጥ ፍላጎትህን በኃይል ለማስፈፀም መንቀሳቀስ ተቀባይነት የሌለው ድርጊት ሲሆን የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ኢጁን ያስገባ የሆነ ይሁን አካል በቸልታ እንደማያልፈው በዚህ አጋጣሚ ይገልፃል።

የትግራይ ክልል የኮሙዩኒኬሽን ቢሮ
ጥቅምት 11 ቀን 2011ዓ.ም
መቐለ

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *