አጭር መግቢያ

የማግኒትሰኪ ህግ – ሕጉ የተሰየመው ሩሲያዊው የንግድ ሒሳብ ሠራተኛ በነበረው ሰርጊዬ ማግኒትሰኪ ነው። ሰርጊዬ በሩሲያ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት የተሳተፉበትን ግዙፍ የግብር ማጭበርበር ዕቅድ በማጋለጥ ውስጥ በተጫወተው ሚና ባለሥልጣናቱ እርሱን ዒላማ በማድረግ ካሳሰሩት በኋላ እኤአ በ2009 ዓም በሞስኮ በሚገኝ እስርቤት ስቅየት ደርሶበት (ቶርቸር ተደርጎ) እና የህክምና ዕርዳታ እንዳያገኝ ተከልክሎ እዚያው ሞቶ ተገኘ።

በሰርጊዬ ማግኒትስኪ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ላይ ተሳትፎ በነበራቸው የሩሲያ ባለሥልጣናት ላይ  የአሜሪካ ኮንግረስ በ2012 ዓም በስሙ ሕግ አወጀ። ሕጉም እነዚህ ወንጀለኞች በአሜሪካ ያላቸው ማንኛውም ንብረታቸው እንዲታገድ እነርሱም ወደ ዩናይትድ ስቴትስ እንዳይገቡ በጥብቅ የሚያግድ ሆኖ የታወጀ ነው።

በቀጣይ ጉዳዩን ዓለምአቀፋዊ ተጠያቂነት በሚያስከትል መልኩ ለመተግበር ኮንግረስ በሩሲያ ላይ ብቻ ትኩረት በማድረግ ያጸደቀውን ሕግ በ2016 ዓም ዓለምአቀፋዊ ይዘት እንዲኖረው በማሰብ አሳደገው። በዚህም መሠረት ሕጉ የሥራ አስፈጻሚውን ቅርንጫፍ በተለይ የሰብዓዊ መብቶችን ጥሰት የፈጸሙና በሙስና የተዘፈቁ የተወሰኑ ግለሰቦችን ቪዛ ለመከልከልና በዓለም ላይ በየትኛውም ቦታ ቢገኙ ማዕቀብ ለመጣል የሚያስችል ፈቃድ እንዲኖረው በሚያደርግ መልኩ የሰፋ ሆነ። ይህ በሁለቱም የአሜሪካ ፓርቲዎች ድጋፍ ያገኘ ሲሆን ረቂቅ ሕጉን ዓለምአቀፋዊ ይዘት በመጨመር አስተካክለው የሜሪላንዱ ጠቅላይ ግዛት ዴሞክራት ሴናተር ቤን ካርዲን አምስት ሪፓብሊካን እና አምስት ዴምክራት ሴናተሮችን በማስፈረም የረቂቁ ተባባሪ ስፖንሰሮች እንዲሆኑ በማድረግ በሕግ እንዲጸድቅ አደረጉ። በቀጣይም ፕሬዚዳንት ኦባማ ሥልጣናቸውን ከመልቀቃቸው አንድ ወር በፊት ፊርማቸውን በማኖር ሕግ ሆኖ እንዲፀድቅ አደረጉ።

ዓለምአቀፉ የማግኒትስኪ ሕግ የሚያደርገው ምንድነው?

ዓለምአቀፉ የማግኒትስኪ የሰብዓዊ መብቶች የተጠያቂነት ሕግ (Global Magnitsky Human Rights Accountability Act) የተወሰኑ “የውጭ ሰዎችን” (ግለሰብ ወይም ድርጅት ሊሆን ይችላል) ቪዛ እንዳያገኙ ለመከልከል፣ ለመሻር፣ ለመዘረዝ፣ ለመንጠቅ እንዲችል ወይም ንብረታቸው ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ለፕሬዚዳንቱ ሙሉ ሥልጣን ይሰጣል። ሰዎች ማዕቀብ የሚጣልባቸው፤

  1. “ፍትህ ሳይበየን ግድያ፣ ስቅየት (ቶርቸር ማድረግ) ወይም በዓለምአቀፍ ደረጃ ዕውቅና የተሰጣቸውን አስከፊ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን” በሌሎች ሰዎች ላይ ከፈጸሙ፤ ወይም
  2. የመንግሥት ባለሥልጣናት ወይም የመንግሥት ባለሥልጣናት ከፍተኛ ተባባሪዎች በመሆን “መጠነ ሰፊ የሙስና ተግባር” ከፈጸሙ ነው

ዓለምአቀፉ የማግኒትስኪ ሕግ ለምንድነው ጠቃሚ መሳሪያ የሆነው?

ሕጉ የሰብዓዊ መብቶች በሁሉም የመንግሥት የሥልጣን ዕርከኖች እንዲከበሩ የሚያበረታታ ሲሆን የሰብዓዊ መብቶችን በጣሱ ከከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጀምሮ እስከ ዝቅተኛ ግለሰቦች ድረስ ይህም መንግሥታዊ ያልሆኑ ተባባሪዎቻቸውን ጨምሮ በእነርሱ ላይ ያነጣጠረ ማዕቀብ የአሜሪካ የሥራአስፈጻሚው አካል እንዲጥል የሚያስችል ነው። ይህ ማዕቀብ በአሜሪካ ውስጥ የሚገኝ ማንኛውንም ንብረት ሆነ ገንዘብ ከማገድ ጀምሮ ግለሰቦቹ ወደ አሜሪካ እንዳገቡ ቪዛ እስከመከልከለ የዘለቀ ነው። … ይህንን ሕግ በማስከበር አገራት ከአሜሪካ ጋር በሚያብሩበት ጊዜ በአገራቸው ለሚገኙ የሰብዓዊ መብቶችን ለሚጥሱ ግፈኞች ትዕግስት እንደሌላቸው ያሳያሉ።

ዓለምአቀፉ የማግኒትስኪ ሕግ የሚጥለው ማዕቀብ ምን ያህል ውጤታማ ነው?

የሚጣለው ማዕቀብ ግለሰቦችን ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ማገድ፣ በዚህ አገር ውስጥ ያላቸውን ንብረት መቆጣጠር እና ከበርካታ ባንኮች እና ኩባንዎች ጋር ምንም ዓይነት የንግድ ልውውጥ እንዳያደርጉ መከልከልን ያካተተ ነው። ከእነዚህ ማዕቀብ ከተጣለባቸው ግለሰቦች ጋር ምንም ዓይነት የንግድ ልውውጥ የሚያደርጉ የአሜሪካ ድርጅቶች እና/ወይም አሜሪካ ቅርንጫፍ ያላቸው ዓለምአቀፍ ድርጅቶች ይህንን ሕግ እንደጣሱ ተቆጥሮ በሕግ ይጠየቃሉ።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ በዚህ ሕግ ላይ ያላቸው አቋም ምንድነው?

ባፈው ዓመት ሚያዚያ ወር (ኤፕሪል 20፣2017) ፕሬዚዳንት ትራምፕ ለኮንግሬስ አባላት በላኩት ደብዳቤ የእርሳቸው አስተዳደር ይህንን “አስፈላጊ ሕግ እንደሚደግፍ” እና “ለተግባራዊነቱ ያለንን ቁርጠኝነት” እንገልጻለን ብለዋል። ከዚህ በተጨማሪም ፕሬዚዳንቱ በደብዳቤያቸው እንደገለጹት አስተዳደራቸው ሕጉ ተግባራዊ ሊደረግባቸው የሚገቡ ግለሰቦችንና ድርጅቶችን በመለየት ሂደት መሆኑን በመጠቆም “በተግባር ለመፈጸም አስፈላጊውን ማስረጃ እየተሰበሰበ” እንደሆነ ገልጸዋል። እስካሁን በሥልጣን በቆዩባቸው ወራት የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃን በተመለከተ ይህ ነው የሚባል ተግባር ባይፈጽሙም፤ ፕሬዚዳንቱ ዓለምአቀፉ የማግኒትስኪ ሕግ ተግባራዊ በማድረግ በሰብዓዊ መብቶች ላይ ጥበቃ ማድረግ አሁንም የአሜሪካ የውጭ ፖሊሲ መሠረታዊ ዓላማ መሆኑን የማሳየት ዕድሉ አላቸው።

ግለሰቦች ማዕቀብ እንዲጣልባቸው ለፕሬዚዳንቱ ሐሳብ የሚያቀርበው ማነው?

ሕጉ እንደሚለው ከሆነ በውጭ ጉዳይ ሚ/ር (ስቴት ዲፓርትመንት) የዴሞክራሲ፣ የሰብዓዊ መብቶች እና የሠራተኞች ረዳት ሚኒስትር (ጸሃፊ) ከሌሎች የውጭ ጉዳይ መ/ቤት ባለሥልጣናት ጋር በመመካከር ለሚኒስትሩ ማዕቀብ ሊጣልባቸው የሚገቡ ሰዎች ስም ዝርዝር ያቀርባል። በሕግ መወሰኛው ም/ቤት (ሴኔት) የባንክ፣ የቤቶች እና ከተማ ጉዳዮች ኮሚቴ እና የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ እንዲሁም በእንደራሴዎች ም/ቤት የፋይናንስ አገልግሎቶች ኮሚቴ እና የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ለፕሬዚዳንቱ ስም ዝርዝር ሊያቀርቡ ይችላሉ።  ማዕቀቡን መጣል ተገቢ መሆኑን ለመወሰን ፕሬዚዳንቱ ሌሎች አገራትና የሰብዓዊ መብቶችን ጥሰቶች በሚከታተሉ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ያወጧቸውን ተዓማኒነት ያላቸውን መረጃዎች በድጋሚ ሊመለከቱ ይችላሉ። ይህም ሆኖ የተግባር አሠራሩ በአብዛኛው የሚከናወነውና ማዕቀቡ የሚጣለው የውጭ ጉዳይ እና የገንዘብ ሚ/ር መ/ቤቶች በጥምረት በሚያደርጉት ውሳኔ ነው።

በአሁኑ ጊዜ ዓለምአቀፉ የማግኒትስኪ ሕግ በተመለከተ ምን እየተደረገ ነው?

በሕግ መወሰኛው ም/ቤት የውጭ ግንኙነቶች ኮሚቴ ካሉት አባላት የላቀ ደረጃ ያላቸው ሴናተር ካርዲን እና የውትድርና አገልግሎቶች ኮሚቴ ሊቀመንበር የሆኑት ሴናተር ጆን ማኬይን ባለፈው ነሐሴ ወር ለፕሬዚዳንት ትራምፕ በጻፉት ደብዳቤ በዓለምአቀፉ የማግኒትስኪ ሕግ መሠረት ማዕቀብ ሊጣልባቸው የሚገቡ የ20 ግለሰቦችን ስም ዝርዝር ሰጥተዋል። ፕሬዚዳንቱም ደብዳቤውን ከተቀበሉ በኋላ መስከረም ወር መጀመሪያ አካባቢ በሕጉ መሠረት የገንዘብ ሚኒስትሩ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማዕቀብ እንዲጥሉ በይፋ ሥልጣን ሰጥተዋቸዋል።

ዓለምአቀፉ የማግኒትስኪ ሕግን የሚመስል ሕግ ሌሎች አገራት አሏቸው?

በርካታ የአውሮጳ አገራት፣ ካናዳ እና የአውሮጳ ፓርላማ ከሰርጊዬ ማግኒትስኪ ሞት ጋር ግንኙነት ባላቸው የሩሲያ ባለሥልጣናት ላይ ሕግ አውጥተዋል። በቅርቡ በርካታ አገራት የሚጥሉትን ማዕቀብ ሰፋ በማድረግ የሰብዓዊ መብቶችን የጣሰ የየትኛውም አገር አገዛዝ ማዕቀብ እንዲጣልበት ወስነዋል። በያዝነው የካቲት ወር (ፌብሩዋሪ 21) ታላቋ ብሪታኒያ የአሜሪካው ዓለምአቀፍ የማግኒትስኪ ሕግን የሚመስል የራሷን ሕግ አጽድቃለች። ኢስቶኒያ እኤአ በ2016 ተመሳሳይ ሕግ አውጥታለች። የካናዳ ፓርላማ እና የአውሮጳ ፓርላማ ዓለምአቀፍ የሰብዓዊ መብቶች የጣሱ ሁሉ ላይ ያነጣጠሩ ረቂቅ ህጎችን እያወጡ ነው።


የቀድሞው የድህንነት ተቋም ዋና ሃላፊ የነበሩት አቶ ጌታቸው አሰፋ የሚጠበቀው ቀርቶ አዲስ ሹመት ማግኘታቸው ይፋ ከሆነ በሁዋላ ለደጋፊዎቻቸው ደስታ፣ ለፍትህ ፈላጊዎች ቁጭት ሆኖ ከርሞ ነበር። ዛሬ የተሰማው አዲስ ዜና ግን በእሳቸው ብቻ ስለማያበቃ ድንጋጤው አይሏል። በተለይም አሁንም እየተከናወነ ያለው ግድያና የጅምላ አፈና መቀጠሉ ይህ አስደንጋጭ ዜና አቶ ጌታቸው ጋር ብቻ ይቆም ይሆን የሚል መወያያም ሆኗል። የጅረመን ራዲዮ ደብዳቤውን እንዲህ ወደ አማርና መልሶታል። 

የአሜሪካ ኮንግረስ አባል የሆኑት ማይክ ኮፍማን የኢትዮጵያ የቀድሞው የደህንነት መስሪያ ቤት ኃላፊ አቶ ጌታቸው አሰፋ የጉዞ እና የንብረት ማንቀሳቀስ ማዕቀብ እንዲጣልባቸው ጠየቁ። የኮንግረስ አባሉን ይህን የጠየቁት ለአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ ዛሬ በላኩት ደብዳቤ ነው።

DW በስልክ ያነጋገራቸው የኮፍማን ረዳት ማይክ የቀድሞው የኢትዮጵያ የደህንነት መስሪያ ቤት ኃላፊን በተመለከተ ደብዳቤ መጻፋቸውን አረጋግጠዋል። ኮፍማን በአሜሪካ ኮንግረስ በርካታ ኢትዮጵያውን የሚኖሩበት የኮሎራዶ ግዛት አካባቢ ተወካይ ናቸው። የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ጌታቸው አሰፋ “ድርጊቶች እና ያላቸው አቅም” እርሳቸውንም ሆነ የመረጧቸውን ኢትዮጵያውያን አሜሪካውያን እንደሚያሳስባቸው ተወካዩ በደብዳቤያቸው ላይ ገልጸዋል።

አቶ ጌታቸው በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የተፈጸሙ ዘር ተኮር ብጥብጦችን ጨምሮ በበርካታ ከባድ ወንጀሎች ስማቸው እንደሚነሳ ኮፍማን ጠቅሰዋል። “አቶ ጌታቸው በቅርቡ በህወሓት ለአመራር ቦታ መመረጣቸው በህዝቦች ላይ የሚያደርሱትን ጉዳት የመቀጠል ዕድል ይሰጣቸዋል” ብለዋል የኮንግረስ አባሉ። ባደረሱት የትየለሌ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ምክንያት እና ከተጠያቂነት ለመራቅ በያዙት አካሄድ ምክንያት የጉዞ እና የንብረት ማዕቀብ እንዲጣልባቸውም ጠይቀዋል።

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት “የማግንትስኪ አክት” በመባል የሚታወቀውን ህግ ተጠቅመው ማዕቀቡን ተግባራዊ ሊያደርጉ እንደሚችሉ የኮንግረስ አባሉ በደብዳቤያቸው አመላክተዋል። ይህም “ዩናይትድ ስቴትስ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጎን እንደምትቆም እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እና ሙስናን እንደማትታገስ ያሳያል” ብለዋል። ኮፍማን በአቶ ጌታቸው ላይ ከሚጣለው ማዕቀብ ባሻገር በባልደረቦቻቸው እና ድርጊቶችን እንዲፈጽሙ በሚያስችሏቸው አስከፊ ወንጀል ፈጻሚዎች ላይ ተጨማሪ እርምጃ እንዲወሰድም ጠይቀዋል።

letter.jpg

ህጉን ለማወቅ ይረዳ ዘንድ ጽሁፉ የተወሰደው ከጎልጉል ነው

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *