የአማራ እና ቅማንት ህዝቦች የሰላም ውይይት መድረክ በጎንደር ከተማ በትናንትናው እለት ተካሂዷል። በውይይት መድረኩ የሁለቱን ህዝቦች አንድነት እና አብሮነት ለማጠናከር የሚያስችል ከሁለቱም ህዝቦች የተውጣጣ 20 አባላት ያሉት ኮሚቴ ተቋቁሟል።

በሁለቱ ህዝቦች መካከል ልዩነትን የሚፈጥር ሳይንሳዊይም ሆነ ጂኦ ፖለቲካል ምክንያት ያለመኖሩን በውይይት መድረኩ ላይ የተሳተፉት አምባሳደር ዘመነ ካሴ ተናግረዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በሁለቱ ህዝቦች መካከል መቃቃርን የሚፈጥሩ ክስተት በመፈጠሩ ምክንያት የዜጎች መፈናቀልም ሆነ ተዘዋውረው መስራት እንዳይችሉ የሚያደርግ ምክንያት እየተፈጠረ መሆኑን ጠቁመዋል። በምክክር መድረኩ የተገኙ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በሁለቱ ህዝቦች መካከል ያሉ ልዩነቶች ለግጭት የማያበቁ መሆናቸውን አንስተዋል።

ሁለቱን ህዝቦች በማጋጨት ተግባር ላይ የሚሳተፉ አካላትም ከዚህ መጥፎ ድርጊታቸው እንዲቀጠቡም ተሳታፊዎቹ ጠይቀዋል። የተቃውሞ እና የድጋፍ ሀሳብ የተነሱበት የጋራ የምክክር መድረኩ ከተካሄደ በኋላም 20 አባላት ያሉት የሰላም ኮሚቴ አስመርጧል።

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ጉዳዮች የጸጥታ መምሪያ ሃላፊ ኮሎኔል ዘለቀ አለባቸው ለሁለቱ ህዝቦች ሰላም የበኩላቸውን ጥረት ሲያደርጉ ለነበሩ ግለሰቦች ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ከዚህ በኋላም የሰላም ኮሚቴው ከፍ ያለ ተግባር እንደሚፈጽም እምነታቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ቅማንትም ሆነ አማራ ማንነቱ እንዳለ ሆኖ ዜግነቱ ኢትዮጵያዊ መሆኑን ያነሱት ኮሎኔል ዘለቀ ሁለቱ ህዝቦች አንድነታቸውን የበለጠ ለማጠናከር መስራት እንዳለባቸውም አጽንኦት ሰጥተዋል።
የአመቻች ኮሚቴ እና የቅማንት ተወካይ የሆኑት አቶ ጸጋዬ ተስፋሁን በበኩላቸው፥ በሁለቱ ህዝቦች የተመረጠው የሰላም ኮሚቴ ችግሮች በታዩበት ቦታ ሁሉ እስከ ታች ድረስ በመውረድ ሃለፊነቱን ለመወጣት ቃል መግባቱን አስረድተዋል። መንግስትም ይህንን ጥረት በማገዝ ከጎናቸው መሰለፍ እንደሚገባውም አመላክተዋል።

ከአማራ የተወከሉት አቶ ብርሃኑ ይመር በበኩላቸው የሰላም ኮሚቴው ተግባር ሰላምን በማስፈን ዘላቂ አብሮነት እንዲፈጠር መስራት ነው ብለዋል። ልዩነቶች በሰላማዊ መንገድ የሀሳብ ትግል እየተደረገባቸው እንዲፈቱ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም ጠቁመዋል። ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ በመፍታቱ ሂደት የሁለቱ ህዝቦች ትብብር እንዲያደርጉም ጥሪ ቀርቧል።

በምናለ አየነው  

(ኤፍ.ቢ.ሲ)

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   Ethiopia’s transition misrepresented. Reply to Obang Metho

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *