በቤተሰብ የተያዙ 5 ወይም 6 የሚሆኑ የንግድ ተቋማት አጠቃላይ የአገሪቱን የወጪ ገቢ ንግድ እንደሚቆጣጠሩት የፌደራል እምባ ጠባቂ ተቋም ያሰራው ጥናት አመለከተ᎓᎓

የፌደራል እምባ ጠባቂ ተቋም በአዲስ አበባ በሸማቾች ላይ የሚደርሰውን የዋጋ ንረት በተመለከተ ባስጠናው ጥናት ላይ በቢሾፍቱ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል፡፡

በመድረኩ ለሸቀጥ ዋጋ መናር ምክንያት በሆኑ ደላሎች፣ ዋጋን በምክር የሚወስኑ አድመኛ ነጋዴዎችና ያልተገባ ጥቅም ለማግበስበስ ሲሉ በሚተባበሯቸው የመንግሥት ተቆጣጣሪ አካላት ላይ ተገቢው እርምጃ እንዲወስድ የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ጠይቋል።

ኪራይ ሰብሳቢነት የበላይነቱን በያዘበት ሁኔታ ነፃና ፍትሃዊ የገበያ ውድድርን ተግባራዊ ማድረግ የማይታሰብ እንደሆነ የህዝብ እንባ ጠባቂ ም/ዋና እንባ ጠባቂ ወ/ሮ ሠራዊት ስለሺ ገልፀዋል።

በአገሪቱ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በንግድ ሂደቱ ላይ ህገወጥ ድርጊቶች ይታያሉ በዚህም ምክንያት ሸማቹን ኅብረተሰብ ሊቋቋመው ወደማይችለው የኑሮ ውድነት እየተገፋ ነው ብለዋል።

በዋጋ ንረት ሳቢያ ነዋሪው ከፍተኛ አቤቱታ እያሰማ እንደሚገኝና ህዝቡ በመንግስት ላይ እምነት እንዳይኖረው ማድረጉም በአውደ ጥናቱ ተገልጿል᎓᎓

የትርፍ ህዳግ አለመኖር አንድ ነጋዴ በ100 ብር የሚሸጠውን እቃ እስከ 1000 ሺሀ ብር የመሸጥ መበት እንደሚሰጥና ይህም ሸማቹን እየጎዳ እንደሚገኝ ተነስቷል᎓᎓

የሸማቶች ኅብረት ስራ ማህበራት አመራሮች የተረከቡትን ምርት በቀጥታ ለተጠቃሚው ከማዳረስ ይልቅ የተወሰነውን ካከፋፈሉ በኋላ ቀሪውን አየር በአየር ለሚነግዱ ህገ ወጥ ሰዎች የሚሸጡበት አጋጣሚ መኖሩንም በጥናቱ ተጠቁሟል።

መንግሥት ያደረገው የውጭ ምንዛሪ ማስተካከያ 15 በመቶ ሆኖ እያለ አብዛኛዎቹ ጭማሪዎች ግን ከ30 እስከ 50 በመቶ መድረሳቸው በጥናቱ ግኝት ውስጥ ተካቷል።

መንግሥት በገበያ ስርአቱ ውስጥ ጣልቃ ገብቶ በህገ ወጦች ላይ እርምጃ እንዲወሰድና ህብረተሰቡም የራሱን አስተዋፅኦ በማበርከት ህጋዊ ነፃና ፍትሃዊ የግብይት ስርዓት ለመዘርጋት ገምቢ ሚና እንዲጫወት ተቋሙ ጥሪ አቅርቧል።

ጥናቱ በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ የንግድ ውድድርና የሸማቶች ጥበቃ ባለሥልጣን፣ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ፣ የአዲስ አበባ ገቢዎች ባለስልጣን፣ የፌዴራል ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽንና የፌዴራል የኅብረት ሥራ ኤጀንሲ ያካተተ ነው።

ጥናቱ የሥራ ኃላፊዎችን፣ ሠራተኞችን ነጋዴዎችንና ሸማቶችን ጨምሮ 1ሺ 98 ሰዎች በመጠየቅና በውይይት አሳትፏል።

ሪፖርተር፡- ሳሙኤል ዮሃንስ – EBC

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *