ሐራ+ዘተዋሕዶ

ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ ከማኅበረ ቅዱሳን ጋራ እንዳልታረቁና እስከሞት ድረስ እንደሚረግሙት ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ተናገሩ፡፡

ፓትርያርኩ ይህን የተናገሩት፣ ብፁዕ አባ ማርቆስ ከምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስነት እንዲነሡ የቀረበባቸውን አቤቱታ ለመመልከት በጀመረበት ወቅት ነው፡፡

ብፁዕ አባ ማርቆስ፣ ከምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት እንዲነሡ ካህናቱና ምእመናኑ ስላቀረቡት አቤቱታ የተያዘው አጀንዳ ወደ ነገ እንዲተላለፍላቸው ቢጠይቁም ምልዓተ ጉባኤው ሳይቀበላቸው ጉዳዩን ማየት ይጀምራል፡፡ ሊቀ ጳጳሱም ወደ ውጭ ወጥተው ከአፍታ ቆይታ በኋላ እንደተመለሱ በድንገት፣ “ሰበር ዜና- ለቀቅሁላችኹ፤ እንደፈለጋችሁ አድርጉት” በማለታቸው አጀንዳው በአጭሩ የተቋጨ መስሎ ነበር፡፡ ኾኖም ስብሰባውን በርእሰ መንበርነት የሚመሩት ፓትርያርኩ ሊቀ ጳጳሱን ተከትለው በሰጡት ያልተጠበቀና ያልተገባ አስተያየት ምክንያት ጉዳዩ ወደ ኋላ ይመለሳል፡፡

east gojjam2

ሊቀ ጳጳሱ፣ አንሡኝ ብለው ካመለከቱ በኋላ ፓትርያርኩ፥ “ማኅበረ ቅዱሳን እንዳስነሣቸው እወቁ፤ ሌላም ሰው ብንመድብ እንዲሁ ጫና ፈጥሮ እንደሚያስነሣችሁ እወቁ” በማለታቸው ኹኔታው አነጋግሯል፤ ራሳቸው ሊቀ ጳጳሱ፣ አንሡኝ እያሉና ጥያቄውም የብዙኀን ምእመናን ኾኖ ሳለ፣ ማኅበሩን ለይቶ መውቀስ አግባብ እንዳልኾነ ፓትርያርኩ በምልዓተ ጉባኤው ቢነገራቸውም፣ የሚቀበሉ ኾነው አልተገኙም፡፡

ፓትርያርኩ እና ማኅበረ ቅዱሳን ዕርቅ ማውረዳቸው፣ የዘንድሮውን ምልዓተ ጉባኤ የተለየ ከሚያደርጉት ክንውኖች አንዱ እንደኾነ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ በምልዓተ ጉባኤ መክፈቻ ጸሎት የተናገሩት ቢጠቀስላቸውም፣“ሽማግሌዎችን በማክበር ነው ታርቄያለሁ ያልኩት እንጅ አልታረቅሁም፤ እናንተ ባትሰሙኝም እንኳ መጋፋት ባልችልም ባለኝ አቅም ሁሉ እስከምሞት ድረስ እረግመዋለሁ፤” በማለት ጉባኤው አሳዝነዋልም፤ አስገርመዋልም፡፡

ማኅበሩ በመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ 37ኛ ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባ ላይ መሳተፉ የዕርቁ ምልክት አድርገው ላነሡ ብፁዓን አባቶችም፣ እርሳቸው ፈቃደኛ እንዳልነበሩና በብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ አቡነ ዲዮስቆሮስ አማካይነት የተሳተፈ መኾኑን በመናገር የጠብ አቋማቸውን አጠናክረዋል፤ አህጉረ ስብከቱ በአጠቃላይ ጉባኤው ላይ ባቀረቡት ሪፖርታቸው የማኅበሩን ሥራዎች የጠቀሱትም፣ “ማኅበሩ ገንዘብ ስለከፈላቸው ነው፤” ሲሉ ከሠዋል፡፡

east gojjam1

ፓትርያርኩ ይህን በመናገራቸው የተበረታቱት ብፁዕ አባ ማርቆስም፣ አንሡኝ ብለው የጠየቁትን በመተው፣ “ቅዱስነትዎ አቋም ከያዙ እኔም እስከሞት ከጎንዎት ነኝ” በማለት በማኅበረ ቅዱሳን ላይ ያላቸው ጭፍን ጥላቻ እንደሚያስተባብራቸው አረጋግጠዋል፡፡ አጀንዳው ሳይቋጭ ምልዓተ ጉባኤው ለምሳ ዕረፍት ተነሥቶ ከተመለሰ በኋላም ማኅበሩን በኹሉም ነገሮች ሲከሡና ተጠያቂ ሲያደርጉ ውለዋል፤ “ያስነሣኝ ማኅበረ ቅዱሳን ነው” በማለትም የፓትርያርኩን ቃል ደግመዋል፡፡

ለሲኖዶሳዊ አንድነትና ለአባቶች ዕርቀ ሰላም የተንቀሳቀሰው ኮሚቴ ባደረገው ጥረት፣ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በማኅበረ ቅዱሳን ላይ የሚያነሷቸው ጥያቄዎች በአመራሩ ማብራሪያ ከተሰጠባቸው በኋላ መሠረታዊ መግባባት ላይ መደረሱ ተገልጾ እንደነበር ይታወሳል፤ በሒደትም ይታይልኝ ያሏቸው ጉዳዮች በጋራ በተቋቋመ ኮሚቴ አማካይነት ውይይት እየተደረገባቸው ቢኾንም፣ ፓትርያርኩ ዛሬ በተናገሩበት መልክ ጥላቻቸውን ዳግም ያንጸባርቃሉ ብሎ የጠበቀ አልነበረም፡፡ እንደ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ ያሉ አንጋፋ አባቶች፣ በዕርቀ ሰላም ኮሚቴው ከተያዘው ባሻገር ብፁዓን አባቶች በጉዳዩ እንዲገቡበት ሐሳብ ማቅረባቸው ታውቋል፡፡

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   መከላከያ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ “ጁንታውን” ሙሉ በሙሉ መደምሰሱን አስታወቀ! በርካታ በቁጥጥር ስር ውለዋል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *