ዓቃቤ ሕግ የጠየቀው የክስ መመሥረቻ ጊዜ ተፈቀደለት

የሁለት ሰዎች ሕይወት ያለፈበትና ከ160 በላይ ግለሰቦች ከፍተኛና ቀላል የአካል ጉዳተኛ የሆኑበት የሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. የመስቀል አደባባይ የቦምብ ፍንዳታ የመጨረሻው ተጠርጣሪ (በቁጥጥር ሥር ውለው ሲመረመሩ ከነበሩት ውስጥ)፣ የምርመራ ጊዜ ተጠናቀቀ፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ላለፉት አራት ወራት በተለያዩ ጊዜያት የፍርድ ቤት ቀጠሮዎች ምርመራ ሲደረግባቸው የነበሩት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ሹም አቶ ተስፋዬ ኡርጌን የምርመራ ሒደት አጠናቆ፣ ለዓቃቤ ሕግ መስጠቱን ሰኞ ጥቅምት 12 ቀን 2011 ዓ.ም. አስታውቋል፡፡

ለፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት ምርመራውን እንዳጠናቀቀ የገለጸው መርማሪ ቡድን፣ ምርመራው የዘገየው የምርመራ መዝገቡን ለዓቃቤ ሕግ ካስረከበ በኋላ፣ ዓቃቤ ሕግ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 38(ሐ) በመጥቀስ ተጨማሪ ምርመራ እንዲያደርግ መዝገቡን በመመለሱ መሆኑን አስረድቷል፡፡ በመሆኑም ዓቃቤ ሕግ በድጋሚ መመርመር የሚገባቸውን ነጥቦች ጠቅሶ የመለሰለትን የምርመራ ሒደት በመሥራት፣ አጠናቆ ማስረከቡን መርማሪ ቡድኑ አስታውቋል፡፡

ዓቃቤ ሕግም ቀርቦ የምርመራ መዝገቡን መረከቡን ለፍርድ ቤቱ አረጋግጦ፣ የምርመራ ሒደቱ ሰፊና ውስብስብ በመሆኑ፣ የምርመራ ሒደቱን ከማስረጃዎች ጋር አመሳክሮ ክስ ለመመሥረት፣ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 109 መሠረት የክስ መመሥረቻ ጊዜ 15 ቀናት እንዲፈቀድለት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡

በዓቃቤ ሕግ ጥያቄ ላይ አስተያየታቸውን የተጠየቁት አቶ ተስፋዬ እንደተናገሩት፣ ከታሰሩ አራት ወር እንደሆናቸው፣ በየቀጠሮ ፖሊስ 14 ቀናት የምርመራ ጊዜ እየጠየቀና እየተፈቀደለት አራት ወራት እንደሞላው፣ ስለዚህ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ስለማያስፈልግ ክስ ካለው እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡

በተጨማሪም መገናኛ ብዙኃን በቤታቸው ውስጥ ያልተገኘ የጦር መሣሪያ እንደተገኘ አድርገው ዘገባ እያሠራጩ መሆኑን ጠቁመው፣ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ መገናኛ ብዙኃን ትክክለኛ ዘገባ ስላለመዘገባቸው እርግጠኛ ስለመሆናቸው ጠይቋቸው በመጠራጠር ውስጥ ሆነው፣ ‹‹እያስተላለፉ ነው፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የግራ ቀኙን ክርክር የሰማው ፍርድ ቤቱ አቶ ተስፋዬ በመገናኛ ብዙኃን ላይ ያነሱት አቤቱታ በማስረጃ ያልተደገፈ መሆኑን በመጠቆም፣ አቤቱታውን ውድቅ አድርጎታል፡፡ ዓቃቤ ሕግ የጠየቀውን የ15 ቀናት የክስ መመሥረቻ ጊዜ በመፍቀድ፣ ለጥቅምት 27 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *