(ኤፍ ቢ ሲ) በደርግ ዘመነ መንግስት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና ትምህርት ሚኒስትር የነበሩት ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ በዛሬው እለት ወደ ሃገራቸው ገቡ።

ኮሎኔል ጎሹ አዲስ አበባ ሲገቡ የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአሜሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀኔራል አቶ ነብያት ጌታቸውን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።

የቀድሞው ሚኒስትር በቦሌ አለም ዓቀፍ አየር መንገድ በሰጡት መግለጫ የደርግን አገዛዝ በመቃወም ሃላፊነታቸውን በፈቃዳቸው በመልቀቅ ላለፉት 32 አመታት ኑሯቸውን በአሜሪካ አድርገው መቆየታቸውን ተናግረዋል።

በሀገሪቱ ያለውን አጠቃላይ የለውጥ ሂደት ለመመልከት፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸውን ለመጠየቅና የተጀመረውን የሰላም፣ የፍቅርና የመደመር ሂደት በሚችሉት መጠን ለመደገፍ ወደ ሃገራቸው መምጣታቸውንም አንስተዋል።

ፖለቲካዊ ውድድር የማድረግም ሆነ ስልጣን የማግኘት ፍላጎት የለኝም ያሉት ኮሎኔል ጎሹ፥ በአሁኑ ወቅት በሃገሪቱ የተጀመረውን የሰላም፣ እርቅና የመደመር እንቅስቃሴ ሁሉም ሊደግፈው እንደሚገባም ነው የተናገሩት።

ይህን የእርቅና የመደመር ጉዞ ላስጀመሩት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ወጣቱም የሰላምን አስፈላጊነት በሚገባ ተገንዝቦ ለግጭት ከሚዳርጉ እንቅስቃሴዎች እንዲቆጠብም ጠይቀዋል።

በሃገሪቱ አሁን ላይ ማንኛውንም ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ በማቅረብ መፍትሄ ማግኘት የሚያስችል ሁኔታ ተፈጥሯል የሚል እምነት እንዳላቸውም ገልጸዋል።

ለዚህም ያላቸውን ልምድና ተሞክሮ ለማጋራትና ለሰላማዊ ሂደቱ መጎልበት የተቻላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ መናገራቸውን፥ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ደመቀ መኮንን በፊንላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከሚመራ የአውሮፓ ህብረት ልዑክ ጋር ተወያዩ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *