የተለያዩ ሚዲያዎች በምዕራብ ኦሮሚያ በኦነግና በመከላከያ ሰራዊት መካከል ግጭት መከሰቱን፣ ግጭቱን ተለትሎ መንገድ መዘጋቱንና የንግድ ግንኙነት መስተጓጎሉን እየዘገቡ ነው። የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳም ወጣቶች ዘመናዊ መሳሪያ ከታጠቀ ሃይል ጋር ለመዋጋት ወደ ጫካ መግባታቸው እንዳሳዘናቸውም ተጠቁሟል። ስለ ጉዳዩ በቅርብ የሚያውቁ እንደሚሉት ጉዳዩ አሳሳቢ አይደለም። ከዳውድ የትወልድ ቀዬ አልፎ የትም አይደርስም። ሲሉ ሌሎች መነሻው ቢኒሻንጉል በመሆኑ ምንጩን ማድረቅ ግድ ነው ባይ ናቸው።

የዳውድ ኢብሳ ጦር

ለሁለት አስርት ዓመታት አስመራ የነበሩት አቶ ዳውድ ኢብሳ ከኢህአዴግ ከድተው ወታደር በመያዝ ወደ ኤርትራ የገቡትን ጀነራል ከማል ገልቾን ሰራዊት ነጥቀዋቸዋል። ከማል ኤርትራ እንደገቡ ከኦነግ ጋር አብረው መስራት ጀመረው የነበረ ቢሆንም ድርጅቱ ተሃድሶ እንዲያደርግ ከሌሎች አመራሮች ጋር በመሆን ጠይቀው ነበር። ትግሉ በዚህ መልክ ከቀጠለ የትም አይደርስም በሚል የኤርትራን ድንበር ሰብረው ለመውጣት ሙከራ የተደረገበትና ዋጋ የተከፈለበትም ጊዜ ስለመኖሩ ውስጥ አዋቂዎች ይናገራሉ።

በዚህን ወቅት አቶ ዳውድ የአካባቢያቸውን የሆሮ ልጆች በማሰባሰብ አቅም አልባ ኦነግ ይዘው ቀጠሉ። የእነ ከማልን ሰራዊትም እንዲጠቀልሉ ተደረገ። እናም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ኤርትራ ተቀምጠው ምንም ሊፈይዱ የማይችሉትን ሌሎችን ተቃውሚዎች ጨምሮ ነጻ አውጥተው ወደ አገር ቤት እንዲገቡ ሲያደርጉ አቶ ዳውድም በዚሁ እድል በትግራይ በኩል ሰራዊታቸው ልከው አዲስ አበባ ገቡ።

READ also this – ዳውድ ኢብሳ ጡረታ!! ቄሮ “በቃ” እያለ ነው!

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ “ማንም የማይደፍረውን የዛላምበሳ ምሽግ አሳልፈን ነው ያስገባናቸው” ሲሉ እንደገለጹት የዳውድ ኢብሳ ከነከማል የነጠቁትን ጨምሮ በዛላምበሳ የገባው ሁለት ሺህ የማይሞላ ሰራዊት የስብሀት ነጋን ቀይ ወጥ በልቶ ትጥቁን ፈቶ ካምፕ ሲገባ እነ ከማል ገልቹ ተረከቡት። ይህ ከከማል ገልቹ ጋር ተማምሎ ኤርትራ የገባው ሰራዊት ምንም ከዳውድ ጋር በነበረው ቆይታው ደስተኛ ይልነበረ፣ የጉልበት ስራ ላይ የተሰማራ፣ በምግብ ለስራ የደቀቀ፣ ለአገሩ ምድር መብቃቱን እንደ ተዓምር የሚያይ አብይን አምላኪ ሰራዊት ነው።

አሁን በሰላም ለመታገል ከገቡ በሁዋላ የኦነግ ሰራዊት ከየት መጣ የሚለው ጉዳይ የበርካቶች መነጋገሪያ ሆኗል። ዛጎል ያነጋገራቸው ጉዳዩ ከጀርባው በርካታ እጅ እንዳለበት ይገልጻሉ። እነዚህ ከጀርባ ያሉ ሃይሎች ይፋ ከሆኑ ድፍን የኦሮሚያ ህዝብ በከሃጂነት ስለሚፈርጃቸው አድፍጠዋል። ይሁን እንጂ መንግስት፣ በተለይም የለማ መገርሳ አስተዳደር ነገሮችን በጥበብ ለመያዝ ባለው አቋም መለሳለስን ቢመርጥም ከጀርባ ያለውን የፖለቲካ ቁማር ያውቀዋል። መነሻቸውን ቢኒሻንጉል ያደረጉና በጋምቤላ በኩል ክላሽ የሚላክላቸው እነዚህ ወገኖች የዳውድ ኢብሳን ስም በስመ ኦነግ ያነሳሉ እንጂ ጉዳይ ሌሎች ጋር ነው።

የዳውድ ድንበርና ተቀባይነት እምን ድረስ?

ዳውድ ኢብሳ አሁን የሚታወቅ ሰራዊት የላቸውም። የሚታወቀው ሰራዊት ያለው ካምፕ ነው። በካምፕ ያለው ሰራዊት አሁን የኦሮሚያ የጸጥታ ሃላፊ ሆነው የተመደቡት ከማል ገልቹ እጅ ነው። ይህ መሆኑ አቶ ዳውድን አላስደሰተም። እሳቸውን ደስ አላቸውን አላላቸውም ሰራዊቱ ተሃድሶውን ከውሰደ በሁውላ ተመልሶ የዳውድ ኢብሳ አካል የመሆኑ ጉዳይ ያከተመ ስለመሆኑ እሳቸው ራሳቸው ጠንቅቀው ያውቃሉ።

ኦነግ እ.አ.አ በ2008 ከኦነግ በተለየው ሸኔ ኦነግ መሪ ጀነራል ሃይሉ ጎንፋና ከማል ገልቾን አስመራ ሆኖ በከሃጂነት ከፈረጀ በሁዋላ ሞት ፈርዶባቸው እንደነበር የሚያስታውሱ እንደሚሉት፣ ዳውድ አስቀድሞም ሆነ አሁን የሚመሩት ኦነግ በሆሮ ልጆች የሚመራ መሆኑ ፣ የሌሎች አካባቢ ተወላጆችን በማግለሉ፣ አሁንም ከጀርባ የሚነዱት ክፍሎች የሚታወቁ በመሆናቸው ተቀባይነት የለውም። ከዚያም በላይ የመጨረሻ መውደቂያው ላይ ተዳርሷል ሲሉ የሚናገሩም እየተበራከቱ ነው።

አሁን የአካባቢያቸውን ልጆች ካልሆነ በስተቀር ሌሎችን ማዘዝም ሆነ መምራት እንደማይችሉ የሚናገሩት ክፍሎች፣ የሸዋ / የመካከለኛው ክፍል ኦሮሞ ከኦሮሚያ በሕዝብ ብዛት ትልቁና በሰው አቅም ቁልፍ ሚና የሚጫወት በመሆኑ የዳውድ ኦሮሚያን የመምራት እቅድ የሚሳካ አይሆንም። በአካባቢያቸውም ቢሆን ነገሮች ይፋ ሲሆኑ ተቃውሞ የሚነሳባቸው፣ ከነብስ ጋር በተያያዘም የሚወነጀሉ ስለመሆናቸው ዝርዝር መረጃ ጠቅሰው የሚተቹዋቸው በርካታ ናቸው። 

ከአካባቢያቸው ውጪ አምስት ከመቶ እንኳን ተቀባይነት የሌላቸው ዳውድ ኢብሳ እየዋለ ሲያድር ይህ ጭንቀታቸው ስህተት ውስጥ እንደሚከታቸው የሚያውቋቸው አስቀድመው ያውቁ ነበር። በኦሮሚያ እሳቸው የሚመሩት የምርጫ ቦርድ ቢቋቋም፣ ድምጽ ራሳቸው ቆጥረው እንኳን ማሸነፍ እንደማይችሉ በስላቅ የሚናገሩ፣ አሁን ወደ ማክተሚያቸው መቃረባቸውን ከትንቢት ባለፈ ተናግረዋል። ነገር ግን ረጋ ብለው እጃቸውን ከታጠቡ ከወረዳቸው ተመርጠው በፓርላማ የመወከል እድል ሊኖራቸው እንደሚችል በማመላከት የጡረታ ዘመናቸውን እንዲጠቀሙበት ይመክሯቸዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ ዳውድ እንዲህ እየበጠበጡ፣ የገቡበትን የስምምነት አግባብ እየጣሱ መኖር እንደማይችሉ የሚጠቁሙ ክፍሎች ኮሽ ባለ ቁጥር የእሳቸው ስም መነሳቱ የሌላቸውንና እሳቸው የማያውቁትን ዝናና ሃይል እያጎናጸፋቸው መሆኑንን ይናገራሉ። ዋናው ጉዳይ የሚነሳው ከቤኒሻንጉል በመሆኑ የቤኒሻንጉል አስተዳደር ሚናውን እንዲለይ፣ ካልሆነም አርፎ እንዲቀመጥ የአማራ ክልልና የኦሮሚያ ክልል ጫና ሊፈጥሩ እንደሚገባ ምክርና ማሳሰቢያ የሚሰጡ አሉ። 

የመረራ ሃይልና  – የጓሮው አክሮባት

ዶክተር መረራ ከሚታወቁበት ግልጽ ፖለቲካቸው አንዱና ትልቁ የመንደርና የዘውግ ትግልን አለመደገፋቸው ነው። በዚህ እምነታቸው በመላው አገሪቱ ሕዝብ ያከብራቸዋል። በኦሮሞና ከሌሎች የሚወለዱ የኦሮሞ ልጆች ይኮሩባቸዋል። በየትኛውም ዘመን አጎብዳጅና የሚለዋወጥ ባህሪ የሌላቸው በመሆናቸው ክብር አላቸው። እናም መረራ ይደመጣሉ። ይወደዳሉ። ተከታዮቻቸው ሁሉ በልዩ ጽናት ስለሚያውቋቸው አይከዷቸውም።

ታማኝ ምንጮች እንደሚሉት አቶ በቀለ ገርባን ከመረራ እና ከአቶ አዲሱ ቡላላ ለመገንጠል ከውጪ የገቡ እክቲቪስቶች ደፋ ቀና ሲሉ መክረማቸውን ይናገራሉ። እነዚህ አክቲቪስት ነን የሚሉ ክፍሎች አቶ በቀለን በመያዝ የመረራን የሰለጠነ አካሄድ አጨናግፈው የከረረ ፖለቲካቸውን ለመትከል ድክመዋል። መረራን ከፓርቲያቸው ለመቁረጥ የተወሰነውም እሳቸው የሸዋ ኦሮሞ በመሆናቸው ነው። እነዚህ ውስጥ አዋቂዎች እንደሚሉት መረራ ዝምታ የመረጡት ለጥንቃቄ በሚል እንደሆነ ይናገራሉ።

አስተያየታቸውን ሲያጠናክሩ የሰሞኑ የአቶ በቀለ ያልተለመደ የፖለቲካ ትንታኔና የማክረር አካሄድ የዚሁ የአክቲቪስቶቹ ተጽዕኖ ስለመሆኑ ማሳያ መሆኑን ይናገራሉ። እጅግ ክብር ያላቸው በቀለ ገርባ ሙሉ በሙሉ ባይወሰዱም አክቲቪስቶች የሚባሉት ሃይሎች ተጽዕኖ እዳሳደሩባቸው ግን ያውቃሉ።

የመረራን ጉዳይ የሚያነሱት ክፍሎች ከዳውድ ኢብሳ ጀርባ ያሉት ክፍሎች የሸዋን ጉዳይ የመረራን ፓርቲ በመጥለፍ ለመቆጣጠር መሞከራቸው ቂልነት ነው። እነ ዲማ ነገዎ፣ ሌንጮ ለታ፣ ሌንጮ ባቲና የመሳሰሉት እንዲህ ያለው አካሄድ አክሳሪ እንደሆነ በሚገልጹበት በአሁኑ ወቅት እነዚህ ክፍሎች አክርረው በመሄድ ምን ትርፍ እንደሚያገኙ፣ የመካከለኛውን ኦሮሚያን ከስረው የትኛውን ኦሮሚያን ሊፈጥሩ እንደሚያስቡ ግራ የሚያጋባ እንደሆነ ይናገራሉ።

ቄሮ የማን ነው? ቄሮ አንድ ነው?

ቄሮ አቶ ለማ መገርሳ እንዳሉት ወጣት ማለት ነው። ሁሉም የኦሮሞ ድርጅቶች ቄሮ አላቸው። ይሁን እንጂ በዋናነት የሚታወቁት ቄሮ ኦሮሚያና ቄሮ ቢሉሱማ ወይም ነጻነት የሚባሉት ናቸው። እነዚህ ሁለት ዋና የወጣት ክንፎች መሪዎቻቸው በዋናነት የሸዋ ልጆች ናቸው። ኦቦ ጫሉ እንደሚሉት እነዚህን የሸዋ ልጆች በዳውድ ኢብሳ አካባቢ ልጆች ለመተካት ሙከራ ተደርጎ ነበር። በዚህም የተነሳ አለመግባባት ተከስቷል።

በዚህ ጉዳይ ዝርዝር መናገር ለጊዜው አግባብ እንዳልሆነ የሚናገሩት ኦቦ ቃሉ፣ በጊንጪ፣ በግንደበረት፣ በአምቦ፣ በጅማ፣ በአዳማ፣ በቢሾፍቱ፣ በሞጆ፣ በዝዋይ፣ መቂ፣ ሻሸመኔ፣ አሰላ፣ በሱሉልታ እስከ ፍቼ፣ በለገጣፎ እስከ ደብረብረሃን፣ በሰበታ እስከ ጅማ፣ በቡራዩ እስከ ባኮ፣ ድፍን ናኖና ጥቁር … ያለው የኦሮሚያ ክፍል ያሉ ቄሮዎች አደረጃጀታቸው የተለያየና የተለያዩ ፓርቲዎች ቢያደራጇችውም የማክረር አካሄድን ፈጽመው አይቀበሉም።

“በዚህ ሃቅ ጃዋር መሃመድ እንኳ ፖለቲካ ውስጥ በቀጥታ አገር አውቆ፣ ጸሃይ ሞቆ ቢገባ እንደማይሳካለት ያውቃል” ያሉት ኦቦ ቃሉ፣ የዳውድ መጨረሻ ከእነ አቶ ለማ መልካም ፈቃድ እንደማይወጣ ያምናሉ። አቶ ለማና ቡድናቸው አሁን ያለው ተቀባይነት እንዲሁ በቀላሉ የሚሸረሸር እንዳልሆነ አቶ ዳውድም ሆነ ለጊዜው ስማቸውን የማይጠቅሷቸው አክቲቪስቶች ጠንቀቀው እንደሚረዱ እምነታቸው መሆኑንን ይናገራሉ። ይሁን እንጂ በለውጥ ግርግር ውስጥ ” ሳይሰክን ” በሚል ብሂል መንፈራገጥ ሌላ ታሪካዊ ስህተት ከመስራት ውጪ አንድም ጥቅም አይኖረውም። ዞሮ ዞሮ ሁሉም የተላላኪነት ድምር ነው። ማንንም አይጠቅምም። ቄሮም ይህንን ያውቃል። ይዋጋል። ከተዋጋ ደግሞ ተዋጋ ነው። ቄሮ ውስጥ አቶ ለማ መገርሳና ቡድናቸው ያለው እጅ ቀላል ባለመሆኑ!!

 

 

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *