ምክትል ሊቀመንበር የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ለማድረግ የታቀደው ሤራ ከከሸፈ በኋላ አዲሶቹ አመራሮች በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት እንደሚፈለጉና ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ ጥሪ ይደርሳቸዋል። ጥሪው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ዕውቅና ውጪ የተደረገ መሆኑን ሊቀመንበሩ ዑመድ ኡጁሉ ያውቁት አዲስ አበባ ሲደርሱና የስብሰባው ገምጋሚዎች ከሌሎች ወታደራዊና የደኅንነት አባላት ጋር ጠርተው ሲያነጋግሯቸው ነው።


ተጠናቀቀ በተባለው የጋምቤላ ክልል ግምገማ የክልሉን ርዕሰ መስተዳድርና ምክትል ለመሾም የገንዘብ ኃይል ከፍተኛ ተጽዕኖ እያደረገ መሆኑ ተሰማ። ግምገማውን እንዲመሩ የተመደቡት ግለሰቦች የክልሉን ርዕሰ መስተዳድር ምደባ በተመለከተ ከሌሎች ጋር በመሆን በገንዘብ ኃይል የሚፈልጉትን ለመሾም ጥረት እያደረጉ መሆናቸው እየተነገረ ነው።

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ የጋምቤላ ክልል ነዋሪዎች “ጋትሉዋክና ተባባሪዎቻቸው በሙሉ ለፍርድ መቅረብ አለባቸው” ማለታቸውን ጠቅሶ በክልሉ የተንሰራፋውን ግፍና ሙስና (ሌብነት) በተመለከተ ሰፋ ያለ ዘገባ ካወጣ በኋላ የክልሉን ርዕሰ መስተዳድር ለመሾም በታቀደው ድብቅ አጀንዳ ላይ ችግር መፈጠሩ ተሰምቷል።

ለአሥር ቀናት የተካሄደውን ግምገማ የመሩትን በተመለከተ ጎልጉል ዘገባውን ሲያቀርብ “ግምገማውን እንዲመሩ ከፌዴራል መንግሥት የተወከሉት ፈቃዱ ተሰማ እና ተፈራ ድሪቦ ግምገማው ከመጠናቀቁ በፊት በጋትሉዋክና በሰናይ ምትክ ዑመድ ኡጁሉ የጋህአዴን ሊቀመንበር፤ ታንኩዌይ ጆክ ምክትል አድርገው አስመርጠዋል። ሆኖም ሁለቱ ከፌዴራል የተወከሉትን የግምገማ መሪዎች በርካታ የተዓማኒነት ጥያቄዎች የሚቀርብባቸው ብቻ ሳይሆኑ ምናልባትም የጋትሉዋክን ዓላማ በማሳካት ሰፊ ሚና የተጫወቱ ናቸው ተብለው በአንዳንዶች ዘንድ ይወቀሳሉ” ብሎ ነበር

ግምገማው ከመጠናቀቁ በፊት የግምገማው መሪዎች የክልሉ ርዕሰ መስተዳድርና ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሹመት መወሰን አለበት በሚል ያቀረቡት አጀንዳ በስብሰባው ላይ ከፍተኛ አለመግባባትን ፈጥሮ እንደነበር ጎልጉል ከተሰብሳቢዎቹ ያገኘው መረጃ ያመለክታል። ፈቃዱ ተሰማ እና ተፈራ ድሪቦ የተባሉት የግምገማው መሪዎች የጋትሉዋክ ሚስት ወንድምና የፓርቲው (ጋሕአዴን) ምክትል ሊቀመንበር እንዲሆኑ የተመረጡትን ታንኩዌይ ጆክ ሮምን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር፤ የፓርቲውን ሊቀመንበር ዑመድ ዑጁሉን ደግሞ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እንዲሆኑ ሃሳብ ያቀርባሉ

ይህንን ከአሠራር ውጪ የሆነ ሃሳብ ከሊቀመንበሩ ሌላ የስብሰባው ተሳታፊዎች አጥብቀው ይቃወማሉ። ያቀረቡትም መከራከሪያ በኢህአዴግ ድርጅታዊ አሠራር መሠረት የፓርቲው ሊቀመንበር የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ይሆናል፤ ሆኖም ሊቀመንበሩ በፌዴራል ደረጃ ከፍተኛ ሥልጣን ካለውና ክልሉን ማስተዳደር የማይችል ከሆነ ብቻ ነው ምክትሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የሚሆነው፤ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ፣ በሶማሊ ክልሎች የተደረገው ይኸው ነው፤ ከዚህ ውጪ የሆነ ምደባ በጋምቤላ ማድረግ ሕዝቡን መናቅ ብቻ ሳይሆን ክልሉን ለከፍተኛ ብጥብጥ የሚዳርግ ነው፤ ሕዝቡ የሚፈልገው መሪ ሊሾምለት ይገባል የሚል ነበር።

በዚህ ወቅት የግምገማው መሪዎች ወደ ክልላችሁ ሄዳችሁ ከሕዝባችሁ ጋር ተነጋግራችሁ ጉዳዩን ፍቱት በማለት ለግምገማ የተጠራውን ስብሰባ ያጠናቅቃሉ። ከግምገማው መጠናቀቅ በኋላ ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ ላይ አዳዲሶቹ የፓርቲው አመራሮች ሂስና ግለሂስ ማድረጋቸውን ገለጾ “በዚህ መሠረት ሶስት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን እስከሚቀጥለው ጉባዔ ድረስ ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት ሲያግድ አንድ የሥራ አስፈፃሚ አባልን ደግሞ ወደ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት እንዲወርድ” መወሰኑን አስታወቀ

የድርጅቱ መግለጫ ይፋ ከሆነ በኋላ የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው ከድርጅቱ የታገዱትና እርምጃ የተወሰደባቸው አባላት እንደተባለው በሂስና ግለሂስ ምክንያት ሳይሆን ኢፍትሓዊ የሆነውን የርዕሰ መስተዳድር አመዳደብ የተቃወሙ ነበሩ። ከህወሓትና ከሌሎች በርካታ በጥቅም ከተሳሰሩ ጋር የተወሳሰበውን የጋትሉዋክን አመራር በሌላ መልኩ ለማስቀጠል የተቀነባበረ ሤራ አንዱ አካል እንደሆነ ለጎልጉል የደረሰው መረጃ ያመለክታል። እነዚህ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አጠራር “ሌቦች” የሚባሉትና “የሌብነት” ሥራቸው እንዳይጋለጥ የሚፈልጉ በአገር ውስጥና በውጪ የሚገኙ ኃይሎች፤ በጋምቤላ የሚፈለገው ለውጥ እንዳይመጣና አሁንም በግፍና በሌብነት የተሳሰረው ሠንሠለት እንዳይበጠስ እስከ 10 ሚሊዮን ብር እንደመደቡ ይህንንም ለአስፈጻሚዎቹ እንዳስረከቡ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ያስረዳሉ።

የጋሕአዴንን ምክትል ሊቀመንበር የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ለማድረግ የታቀደው ሤራ ከከሸፈ በኋላ አዲሶቹ አመራሮች በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት እንደሚፈለጉና ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ ጥሪ ይደርሳቸዋል። ጥሪው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ዕውቅና ውጪ የተደረገ መሆኑን ሊቀመንበሩ ዑመድ ኡጁሉ ያውቁት አዲስ አበባ ሲደርሱና የስብሰባው ገምጋሚዎች ከሌሎች ወታደራዊና የደኅንነት አባላት ጋር ጠርተው ሲያነጋግሯቸው ነው።

ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ የተደረጉት አመራሮች በተለይ ሊቀመንበሩ ከፍተኛ ዛቻና ማስፈራሪያ የተሰጣቸው ሲሆን ይህም ዋንኛ ምክንያት ምክትል ሊቀመንበርና የጋትሉዋክ ሚስት ወንድም የሆኑትን ታንኩዌይ ጆክ ሮምን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዲሆኑ እንዲቀበሉ ሲሆን ሊቀመንበሩ ግን በአቋማቸው ፀንተዋል። ከሕዝባቸውና ከፓርቲው አሠራር ውጪ የሚደረገውን ምደባ እንደማይቀበሉ ለተናገሩት ሊቀመንበር ተጨማሪ ዛቻና ማስፈራሪያ ተሰጥቷቸው ቅዳሜ ጥቅምት 24፤ 2011 ለሌላ ስብሰባ እንዲመጡ ተነግሯቸው ከስብሰባው ወጥተዋል።

ይህንን በጋምቤላ ሕዝብ ላይ ያለፍላጎቱ ለማስቀጠል የሚደረገው የህወሓትና የለውጡ ተቃዋሚዎች ሤራ በፌዴራል መንግሥቱ ቀጥተኛ ጣልቃገብነት ካልተቀለበሰ በክልሉ ከፍተኛ ቀውስ እንደሚያስከትል ጎልጉል ያነጋገራቸው የክልሉ የቀድሞ አመራር ሥጋታቸውን ይገልጻሉ። በሌሎች ክልሎች በተለይ በሶማሊ ክልል ከተደረገው ያነሰ በጋምቤላ እንዲሆን መፍቀድ ለዓመታት መሬቱን እየተነጠቀ፣ ግፍ እየተፈጸመበት የኖረውን የጋምቤላ ሕዝብ ወገብ የሚሰብር ብቻ ሳይሆን ግፍ የመረረውን የክልሉን ወጣት ላልተፈለገ አመጽ መጋበዝ ነው ሲሉ እኚሁ ሰው ይናገራሉ። ከደቡብ ሱዳን ጋር የተቆራኘው የጋምቤላ ጉዳይ የክልሉን ሕዝብ ፍላጎት በሚያረካ መልኩ ካልተጠናቀቀ አሁንም በግፍ፣ በጉቦ፣ በማስፈራራትና በዛቻ የሚደረገው አሠራር በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ገና በሁለት እግሯ ባልቆመችውን ደቡብ ሱዳንና በቀጣናው ከፍተኛ አለመረጋጋት እንደሚፈጥር በብዙዎች ይታመናል።

goolgule

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *