ለበርካታ ወራት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ኃላፊ በመሆን ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ ፍጹም አረጋ ወደ ቀድሞ መሥሪያ ቤታቸው የኢንቨስትመንት ጽ/ቤት እንደሚመለሱ ከተነገረ ወዲህ ቦታቸውን የሚተካው ማን እንደሚሆን እስካሁን አልታወቀም ነበር።

ዛሬ ከተለያዩ ምንጮች የተሰራጨው መረጃ እንደሚያመለክተው አቶ ሽመልስ አብዲሣ የፍጹም አረጋን ቦታ ተክተው እደሚሠሩ ታውቋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት በአዲስ መልክ በተደራጀው “ፕሬስ ሴክሬተሪ” ዛሬ ጥቅምት 26 ቀን 2011 ዓ.ም. ከቀኑ በ8:00 ላይ በጽ/ቤቱ አዳራሽ ጋዜጣዊ መግለጫ የሚሰጥ ሲሆን ሹመቱም በዚሁ ጊዜ ይፋ እንደሚገለጽ ይነገራል።

አቶ ሽመልስ አረጋ በቡድን ለማ (ቲም ለማ) ውስጥ ቁልፍ ቦታ የነበራቸው የለውጡ አካል ሲሆኑ የኦዴፓ እና ኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ አባል ናቸው።

አቶ ሽመልስ በኦሮሚያ ክልል የኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ፤ በመቀጠልም የከተማና ቤቶች ልማት ምክትል ኃላፊ በመሆን የኦሮሚያ የኢኮኖሚ አብዮትን የመሩ ናቸው።

አቶ ፍጹም በቲዊተርና በፌስቡክ መረጃዎችን በመልቀቅ በጥሩ ሁኔታ ግንኙነት ሲያደርጉ እንደቆዩ ቢነገርላቸውም ከጠ/ሚ/ር ዐቢይ ጋር ለመገናኘት የሚያዙ ቀጠሮዎችን በማዛባት ብቻ ሳይሆን እጅግ በተደጋጋሚ የሚደወልላቸውን ስልክ ባለመመለስ፣ ለሚላክላቸው አጭር የጽሁፍ መልዕክት (ቴክስት) ምላሽ ባለመስጠት ወዘተ ኃላፊነታቸውን ባግባቡ እንዳልተወጡ በግል ሳይሆን በድርጅት ደረጃ ጠ/ሚ/ሩን ለማግኘት ጥረት ያደረጉ ምሬታቸውን ይገልጻሉ። ከአቶ ሽመልስም ከዚህ የተሻለ እንደሚጠብቁ ይናገራሉ።

አቶ ሽመልስ የኦዴፓ እና የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ መሆናቸው የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ሆነው በፌዴራል መንግሥት ውስጥ ከሚገኙት ዐቢይ አህመድ፣ ወርቅነህ ገበየሁ፣ አዳነች አቤቤ፣ ወዘተ ቀጥሎ ተጨማሪ የኦዴፓ ኃይል ሆነው  መምጣታቸው አንዳንዶች የህወሓት የበላይነት በኦዴፓ የመተካት ሁኔታን ያሳያል ይላሉ።

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *