በርካታ ኢትዮጵያውያን ስለ ጥላቻ ንግግር ሲያስቡ ቀድሞ የሚመጣባቸው በማኅበራዊ ድረገጾች ላይ የሚስተናገዱ ክርክሮች፣ ትችቶች፣ ግላዊ አስተያየቶች እና እንዲሁም እርስ በርስ መነቋቆሮች ናቸው፡፡ “እነዚህ በርግጥ የጥላቻ ንግግሮች ናቸውን?

በፍቃዱ ኃይሉ


ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ መንበረ ሥልጣኑ ከመጡ ወዲህ በርካታ ለውጦች ተመዝግበዋል፡፡ ይሁን እንጂ ለውጡ በየት አቅጣጫ እየሔደ እንደሆነ በርግጠኝነት መናገር የሚያስችል ፍኖተ-ካርታ ወይም ሰነድ አልተዘጋጀም ነበር፡፡ በዚህ ሳምንት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥር የተዋቀረው የፕሬስ ሴክሬታሪ አንድ ነገር ይዞ ብቅ ብሏል፡፡ ይኸውም የመንግሥትን የለውጥ መንገድ የሚያሳይ “ኢትዮጵያ፤ አዲሲቷ የለውጥ አድማስ” የሚል ባለ አንድ ገጽ ፍኖተ ካርታ ወይም በእነርሱ አጠራር “የዕቅድ ሰሌዳ” ነው፡፡ 
የዕቅድ ሰሌዳው በርካታ የኢኮኖሚ እርምጃዎች እንደታቀዱ ሲያመለክት “የዴሞክራሲ እና ፍትሕ ግንባታ” እንዲሁም “የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ” ላይ ጥቂት ነገሮችን አስቀምጧል፡፡ በዕቅዱ መሠረት በ2011 ዓ. ም.  ሊፈፀሙ የታቀዱ 32 የድርጊት መርሐ ግብሮች እና ለ2012 ዓ. ም. ይደር የተባሉ ደግሞ 34 የድርጊት መርሐ ግብሮች ተዘርዝረውበታል፡፡ ከነዚህ ሁሉ ግን ትኩረቴን የሳበው ለ2011 ዓ. ም. የታቀደው “የፀረ-ጥላቻ ንግግር የወንጀል ሕግ ማውጣት እና ተግባራዊ ማድረግ” የሚለው ነው፡፡ ነገሩ በጥቅምት ወር አጋማሽ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለፓርላማ ባደረጉት ንግግር ወቅት የተነሳ ቢሆንም፣ የለውጥ አጀንዳው አካል ሆኖ በዕቅድ ሰሌዳው ላይ መቅረቡ ግን የተለየ ትኩረት እንደተሰጠው ያሳያል፡፡ 
የጥላቻ ንግግር ምንነት እና እንዴት መከላከል ይቻላል የሚለው ጉዳይ አስማሚ ማዕቀፍ የለም፡፡ በተለይም ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አዋጆችን ለዴሞክራሲያዊ መብቶች ማፈኛ የማድረግ የቀደመ ታሪክ ያላቸው አገራት፣ የፀረ-ጥላቻ ንግግር ሕግን ማውጣት የራሱ የሆነ ጥንቃቄን ይጠይቃል፡፡ ነገር ግን ዕቅዱ ከተዋወቀ በኋላ እምብዛም ሕዝባዊ አስተያየቶች አልተደመጡበትም፡፡ 
ሕጉ ለምን ያስፈልጋል?
በርካታ ኢትዮጵያውያን ስለ ጥላቻ ንግግር ሲያስቡ ቀድሞ የሚመጣባቸው በማኅበራዊ ድረገጾች ላይ የሚስተናገዱ ክርክሮች፣ ትችቶች፣ ግላዊ አስተያየቶች እና እንዲሁም እርስ በርስ መነቋቆሮች ናቸው፡፡ “እነዚህ በርግጥ የጥላቻ ንግግሮች ናቸውን? ኢትዮጵያስ የፀረ ጥላቻ ንግግር ሕግን ማውጣት የለውጥ አጀንዳዋ አካል መሆን ይኖርበታል?” ለሚሉት ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ማግኘት ይቸግራል፡፡ 
የመጀመሪያው ምክንያት ከላይ እንደተጠቀሰው በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ አዋጆች እና ሕግጋት ነጻነትን ለማፈን መሣሪያ ሆነዋል፡፡ እናም የጭቆና መሣሪያ ሆነዋል የተባሉት አዋጆች እና ሕግጋት እየተከለሱ ባሉበት ወቅት የጥላቻ ንግግርን ለመከላከል በሚል “የሚወጣው አዋጅ ምን ያህል ከቀድሞዎቹ የመናገር ነጻነት ላይ ማዕቀብ ከጣሉ አዋጆች የተሻለ ይሆናል?” የሚለው ቅሬታ አንዱ እና ዋነኛው የሕጉን ወቅታዊነት አጠያያቂ ምክንያት ነው፡፡
የጥላቻ ንግግር በኢትዮጵያ ያለበትን ደረጃ የሚያመላክቱ ጥናቶች እምብዛም አልተሠሩም፡፡ ይሁን እንጂ እንደ ጎርጎሮሳዊው በ2016 ዓ. ም.  በኦክስፎርድ እና አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ምሁራን ጥምረት “መቻቻል” በሚል ርዕስ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተሠራ ጥናት አለ፡፡ ይህ ጥናት ከአንድ ሺሕ በላይ የፌስቡክ ገጾችን እና 13 ሺሕ ገደማ የፌስቡክ ጽሑፎችን መነሻ አድርጎ የተሠራ ነበር፡፡ በውጤቱም በኢትዮጵያ ማኅበራዊ ሚዲያ ምኅዳር ላይ ከጥላቻ ንግግር ይልቅ እርስ በርስ መነቃቀፍ እንደሚበረክት ተመላክቷል፡፡ በአጥኚዎቹ ድምዳሜ መሠረት፣ የጥላቻ ንግግር ደረጃ ከአንድ በመቶ አይበልጥም፡፡ 
የጥናቱ መሪ የሆኑት ኢግኒዮ ጋገሊያርዶን እንደሚሉት “የፖለቲካ ተቃዋሚዎች እርስ በርስ የጥላቻ ንግግር እያደረጉ ነው በሚል ይወቃቀሳሉ፤ ነገር ግን በቅጡ ስናጤነው፣ አብዛኛዎቹ ንግግሮች ተራ ፖለቲካዊ ዘለፋዎች ናቸው፡፡” በእርግጥ ይህ ጥናት ከተደረገ በኋላ ያለው ሁኔታ በርካታ ፈጣን ለውጦችን ያስተናገደ እንደመሆኑ ዛሬ ላይ ተመሳሳይ ውጤት ላይሰጥ ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ፣ የጥላቻ ንግግርን ለማስቆም በሚደረገው ሙከራ ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት ላይ አፈና እንዳይደረግ አሁንም ያሰጋል፡፡ 
የቅቡልነት ጉዳይ
የፀረ-ጥላቻ ንግግር ሕግ ሊገጥመው ከሚችሉ ፈተናዎች ሌላው የቅቡልነት ችግር ነው፡፡ “ወቅቱ ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሽግግር የሚደረግበት ነው” በመባሉ ብቻ ሕዝባዊ ይሁንታ ያገኘ መሆኑ ብዙም አያነጋግርም፡፡ በመሆኑም የሚደረጉት የአዋጅ ማሻሻያዎች የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስፋት እና ጨቋኝ አዋጆችን ለመሻር ብቻ እስከሆነ ድረስ ነው በቀላሉ ቅቡልነት የሚያገኙት፡፡ ነገር ግን በንግግር ነጻነት ላይ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ተፅዕኖ የሚኖረውን ሕግ ማውጣት የተቀባይነት ችግር ስለሚያስከትል የፀረ-ጥላቻ ንግግር ሕግ ለማውጣት ይህ ትክክለኛው ጊዜ አይመስልም፡፡ 
የጥላቻ ንግግር በዓለም አቀፍ ደረጃ አስማሚ ትርጉም የሌለው፣ በተለይም ደግሞ ዴሞክራሲያዊ ቢሮክራሲ በሌለበት የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት ላይ ማዕቀብ ለመጣል ሰበብ ሆኖ የሚያገለግል ከመሆኑም ባሻገር በኢትዮጵያ ሕዝባዊ ተሳትፎ ለማድረግ የሚያስችል የተረጋጋ ሁኔታ ሳይኖር እና ቅቡልነት ያለው ምክር ቤት ሳይቋቋም በፊት ከላይ ወደታች በሚደረግ ግፊት ብቻ የፀረ-ጥላቻ ሕግ ሕዝቡ ላይ መጫን አደገኛ ይሆናል፡፡ 
ስለሆነም፣ እንደአማራጭ የሲቪል ማኅበራትን እንዲያብቡ በማበረታታት፣ እንዲሁም ብዙኃን መገናኛዎችን በመጠቀም ዜጎች በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የጥላቻ ንግግሮችን እንዳያደርጉ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ መሥራት መቅደም ይኖርበታል፡፡ ሕጉን ማውጣት አስፈላጊ መሆኑ ቢታመንበት እንኳን፣ ጥድፊያው ቀርቶ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ አዲስ ምክር ቤት ከተመሠረተ በኋላ ጉዳዩ ወደ መድረክ ቢመጣ ሕጋዊም፣ ሞራላዊም ተቀባይነት ይኖረዋል፡፡ አለበለዚያ ሌላ የመጨቆኛ መሣሪያ እንዲሁም የውዝግብ መንስዔ የመሆን ዕድሉ ሰፊ ይሆናል፡፡ 

በዚህ አምድ የቀረበው አስተያየት የጸሀፊው እንጂ የ« DW»ን አቋም አያንጸባርቅም።

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *