የኢትዮጵያ መንግስት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኤርትራ ላይ ጥሎት የነበረውን ማዕቀብ በማንሳቱ የደስታ መልዕክት አስተላለፈ። የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ ተመድ በኤርትራ ላይ ጥሎት የነበረውን ማዕቀብ በማንሳቱ ለኤርትራ መንግስትና ህዝብ የደስታ መልዕክቱን አስተላልፏል።
ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ መንግስት በ2002 ተጥሎ የነበረው ማዕቀብ እንዲነሳ ጥያቄ ማቅረቡ የሚታወስ ሲሆን፥ ይህንን ጥያቄ ተከትሎም ተመድ ለሰጠው ምላሽ መንግስት ምስጋናውን አቅርቧል፡፡
እንዲሁም የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) አባል ሀገራት ማዕቀቡ እንዲነሳ ላበረከቱት አስተዋጽኦም አድናቆቱን ገልጿል፡፡
የማዕቀቡ መነሳት በአፍሪካ ቀንድ ለሚታየው መረጋጋትና ሰላም ዘለቄታዊነት ብሎም የቀጠናውን ሀገራት ግንኙነት ለማጠናከር የላቀ ሚና ይጫወታል ተብሏል፡፡
መንግስት የማዕቀቡ መነሳት በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል በአዲስ መልክ የተጀመረውን የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ባህላዊ ትስስር የበለጠ እንደሚያጠናከረውም አስታውቋል።
በመጨረሻም የኢትዮጵያ መንግስት ለቀጠናው ሰላም፣ ልማትና ትብብር ከኤርትራና ከሌሎች ጎረቤት ሀገራት ጋር አብሮ ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑንም የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ አመላክቷል።