የብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጀኔራል ክንፈ ዳኘው ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርበዋል። በዛሬው ዕለት በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 10ኛ የጊዜ ቀጠሮን በሚመለከተው የወንጀል ችሎት ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘውና ጋዜጠኛ ፍጹም የሽጥላን ጨምሮ 8 ተጠርጣሪዎች ቀርበዋል። ከዚህ ውስጥ ሁለቱ በሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲሆን ስድስቱ ደግሞ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው የቀረቡ ናቸው።

በመዝገብ ቁጥር 225258  በቀዳሚነት በአንደኛ ተጠርጣሪነት ከወንድማቸው ከሁለተኛ ተጠርጣሪ ከአቶ ኢሳያስ ዳኘው ጋር ለቀረቡት ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው፥ ተጠርጣሪው በቁጥጥር ስር የዋሉበትን ጉዳይ መርማሪ ፖሊስ ለችሎቱ አስረድቷል። በተለይም ሃላፊነታቸውን ተጠቅመው በርካታ የግዢ ውሎችንና መመሪያን ባልተከተለ መልኩ ግዢ መፈጸማቸው ተጠቁሟል።

ከ28 አመት በላይ ያገለገሉና መንግስት አዋጪ አይደሉም ብሎ አምኖባቸው በውዳቂ ብረታ ብረት ኮርፖሬሽኑ እንዲረከብ ያደረጋቸውን ሁለት መርከቦች፥ በስልጣናቸው ያለምንም ጨረታ ወደ ንግድ ስራ እንዲገቡ በማድረግ ከ6 ወር በላይ በጅቡቲ  እንዲቀመጡ መደረጉንም ፖሊስ አስታውቋል።

ለመርከቡ ነዳጅ ወጪ በውጭ ምንዛሬ ወጪ እንዲደረግ በማድረግ ፣ ለመርከብ ስራ 26 ሰራተኞችን የምግብ ፍጆታ ከመንግስት ወጪ እንዲከፈል በማድረግ ፣መርከቦቹን ወደ ዱባይ በመላክ እዛው በሚገኝ እያዩ የመርከብ ጋራዥ በውድ ዋጋ ለአንድ አመት ጥገና በማቆየት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ወደ ውጭ ማሸሻቸውንም አስታውቋል።

መርከቡን ያለ ጨረታ ለተለያዩ ድርጅቶች በመሸጥ 10 በመቶ ኮሚሽን እንዲታሰበ በማድረግ እና 7 በመቶ ደግሞ እራሳቸው ለሚፈልጓቸው ግለሰቦች ያለአግባብ እንዲከፈል አስደርገዋል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ማሪታይምን የመርከቦቹ የእንቅስቃሴ እድሳት እንዲታደስ ማስገደዳቸውን እንዲሁም የንግድ ስራ እንዲሰማሩ ማስደረጋቸውም ተጠቅሷል፤በአጠቃላይ ለመርከቡ 29 ሚሊየን ዶላር ወጪ ተደርጓል ነው የተባለው።

ከዚህ ባለፈም ለያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ የመሳሪያ ግዢ ሳይፈጸም ክፍያ እንዲሰጥ አድርገዋል ያለው ፖሊስ፥ የፋብሪካው አፈር እንዲሸሽ 30 በመቶ የሲቪል ስራው በባለሙያ እንዲጠና መደረግ ሲገባው፣ ሳይጠና 3ኛ ወገንን ለመጥቀም በማሰብ ከፍተኛ ክፍያ በመፈፀም 2 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ለፋብሪካ ስራ በሚል ክፍያ ተፈጽሟል ብሏል።

በተጨማሪም ፖሊስ ተጠርጣሪው የአቪየሽን ስልጣን ሳይኖራቸው ስድስት አውሮፕላኖችን ግዢ በመፈጸም ያለአገልግሎት በደጀን አቪየሽን እንዲቀመጡ አድርገዋልም ነው ያለው።

ለአየር ሃይል አገልግሎት የማይውሉ አሮጌ ሄሊኮፕተሮችን ጀርመን ሃገር ከሚገኝ ኩባንያ በመግዛት ያለ አገልግሎት መቆማቸውም ተጠቁሟል።

እንዲሁም ለነዳጅ ምርት ነዳጅ እናመርታለን በማለት ለእቃ ግዠ የሰባት ሚሊየን ዩሮ ግዥ በመፈጸም 150 ሊትር ነዳጅ ሳይመረት መቅረቱን ተናግረዋል።

በተጨማሪም በማይመለከታቸው የሆቴል ግዢ ላይ በመሰማራት ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ ወጪ ማድረጋቸውንም ነው ፖሊስ ያስታወቀው።

ለታላቁ የህዳሴ ግድብ የምንጣሮ ስራ በአግባቡ ሳይሰራ ለተለያዩ ድርጅቶች ገንዘብ ከፍሏል በዚህ  ምክንያትም ግድቡ እዲዘገይ መደረጉ ተጠቁሟል።

ተጠርጣሪዎቹ ቁርጥራጭ ብረቶችን ከተለያዩ የልማት ድርጅቶች ተረክበው በመሸጥና ለግል ጥቅማቸው በማዋል እንዲሁም ከስኳርና ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ብር መባከኑን እና ፕሮጀክቱ በወቅቱ እንዳይጠናቀቅ ማድረጋቸው ተገልጿል።

በሁለተኛ ተጠርጣሪነት የቀረቡት  የኢትዮ ቴሌኮም ሰራተኛ ወንድማቸው አቶ ኢሳያስ ዳኘው፥ ኢትዮ ቴሌኮም ሲሰሩ ለኮርፖሬሽኑ ያለ አግባብ በተሰጠ የፓወር ተከላ ስራ ፕሮጀክት እንዲሰጥ በማድረግ፣ በአግባቡ ፓወር ተተክሎ ለህዝብ አገልግሎት ላይ እንዳይውል  ባማድረግ እና ተገቢ ያልሆነ ሃበት አከማችተው መገኘታቸውን ፖሊስ ለችሎቱ አስርድቷል።

በመጨረሻም እስካሁን የአጣሪ የምርመራ ቡድን መደራጀቱን እና ከ20 በላይ ምስክር መሰማቱን  በመግለጽ ቀሪ የምርመራ ስራ ለማከናወን 14 ቀን ይሰጠኝ ሲል ፖሊስ ፈርድ ቤቱን ጠይቋል።

ሜጀር ጀኔራል ክንፈ ዳኘው “ወርሃዊ ገቢዬ በጡረታ የማገኘው 4 ሺህ ብር ብቻ በመሆኑ፥ አቅም ስለሌለኝና የዘመድ እጅ እንዳላይ መንግስት ተከላካይ ጠበቃ እንዲያቆምልኝ” በማለት ቃለ መሃላ ፈጽመዋል።

በተመሳሳይ ወንድማቸው 2ኛ ተጠርጣሪ  ወራዊ ደሞዜ 8 ሺህ ብር በመሆኑ ጠበቃ ማቆም አልችልም ብለው ምለዋል።

በችሎቱ የመከላከያ ጠበቆች ሊገኙ ባለመቻላቸውም ፍርድ ቤቱ ለነገ ከሰዓት በኋላ 8 ሰዓት ሌላ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በሁለተኛ መዝገብ የቀረቡት የቀድሞውን የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ምክትል እና የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀኔራል አቶ ያሬድ ዘሪሁንን አስመልጠዋል በሚል የተጠረጠሩት የነብስ አባቱ አባ ሃይለማርያም ሃይለሚካኤል እና ሾፌራቸው  አሸናፊ ታደለን ጉዳይ  ፍርድ ቤቱ የተመለከተ ሲሆን፥ ፖሊስ ግለሰቡን አሽሽተዋል ሰነድም በተመሳሳይ ሰውረዋል ሲል የተጠረጠሩበትን ጉዳይ ተናግሯል።

ተጠርጣሪው የነፍስ አባት ብቻ መሆናቸውን በመጠቆም ስለግለሰቡ ወንጀለኝነት የማውቀው ነገር የለም፣ ግለሰቡንም ለመሸሸግ አልሞከርኩም ሲሉ በመሃላ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል።

ሹፌር የተባለው ተጠርጣሪም ሹፌር አይደለም፣ ከእኔጋር ገዳም ሲሄድ ነው የተያዘው ሲሉ ገልጸዋል። ገዳም ከማሰራት ውጪ ገቢ የለኝ ሲሉም መንግስት ጠበቃ እንዲያቆምላቸው ጠይቀዋል።

ፍርድ ቤቱም ተጠርጣሪውን ለመያዘ ግለሰቦችን ይዞ ማፈላለግ ተገቢ አለመሆኑን በመጠቆም፥ ነገር ግን ተሰወረ የተባለው ሰነድ ማጣራት አስገላጊ ሆኖ መገኘቱን በማመን ሰነዱን ፖሊስ በ10 ቀን ውስጥ አጣርቶ ምላሽ እንዲያቀርብ በማለት ለህዳር 17 ቀን 2011 ዓ.ም ከሰአት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በሶስተኛ መዝገብ የተመዘገቡት እና ፍርድ ቤት የቀረቡት ትግስት ታደሰ ተማሪ በመሆኔ መንግስት  ጠበቃ ያቁምልኝ ያለች ሲሆን ፥ ጋዜጠኛ ፍጹም የሺጥላ ፣ ቸርነት ሞላልኝ  እንዲሁም በሰባዊ መብት ጥሰት የተጠረጠሩት አያልነህ ሰፋና ሳሙኤል ኡርጌሳ ጠበቃ ለማቆም ተማክረን እንቅረብ ማለታቸውን ተከትሎ ችሎቱ በተመሳሳይ ለነገ ከሰአት ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል።

FBC

በታሪክ አዱኛ

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *