የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 10ኛ የወንጀል ችሎት ሜጄር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው መንግስት የመደበላቸውን መከላከያ ጠበቃ በማንሳት በራሳቸው ጠበቃ እንዲያቆሙ ብይን ሰጠ።

ሜጄር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው ገቢዬ በጡረታ ማገኘው 4 ሺህ ብር ብቻ በመሆኑ መንግስት ጠበቃ ያቁምልኝ ማለታቸውን ተከትሎ በዚህ ጥያቄያቸው ላይ ፖሊስ ተቃውሞውን ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል።

መርማሪ ፖሊስ ለፌደራል ፀረ ሙስናና ስነ ምግባር ኮሚሽን ያስመዘገቡትን ሀብት፣ 80 ሺህ የሚያወጣ ተሸከርካሪ እና ቢሾፍቱ ከተማ ላይ መኖሪያ ቤት እንደዚሁም የተለያዩ የአክሲዮን ድርሻዎች እንዳላቸው በማስረጃነት አቅርቧል።

በተጨማሪም በአዋሽ ባንክ እስከ ህዳር 5 ቀን 2011 ዓመተ ምህረት ድረስ ያላቸውን ተቀማጭ ሂሳብ አቅርቧል። ፍርድ ቤቱ የባንክ ሂሳባቸው ሲታይ በፈረንጆቹ በ24/10/2018 100 ሺህ ብር አስገብተው በ29/10/2018 100 ሺህ ብር ወጪ ማድረጋቸውን ተመልክቷል።

መርማሪ ፖሊስም ይህ ሀብታቸውን ለማሸሽ ጥረት ሲያደርጉ እንደነበር ማሳያ ይሆናል ብሏል። ግራና ቀኙን የተመለከተው ፍርድ ቤቱ ገቢ እና ወጪ ያደረጉበት የቀን ልዩነት ያላቸው ሀብት ለመጥፋቱ ማሳያ ስለማይሆን መንግስት የመደበላቸው የመከላከያ ጠበቃ እንዲነሳ ሲል ብይን ሰጥቷል።

ሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘው በበኩላቸው በግላቸው ሌላ ጠበቃ ለመቅጠር ያቀረቡትን ጥያቄ ችሎቱ ተቀብሎ ጉዳዩን በቀጣይ ለመመልከት ለህዳር 10 ቀን 2011 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

ተጠርጣሪው ፍርድ ቤቱን ቤተሰቦቼ መጥተው እንዲመለከቱኝ ይፍቀድልኝ የሚል ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን፥ ፍርድ ቤቱም ጥያቄውን ለመፍቀድ መርማሪ ፖሊስ የቤተሰቦቻቸውን ህጋዊነት እና ተገቢነት አጣርቶ እንዲቀርብ ትእዛዝ ሰጥቷል። ጋዜጠኛ ፍጹም የሺጥላ ባቀረበችው ጥያቄ መሰረት የመንግስት ተከላካይ ጠበቃ ቆሞላታል።

ፖሊስ ለፍርድ ቤት እንዳብራራው፥ ሜቴክ የጋዜጠኛ ፍጹም ንብረት ለሆነው ፍፁም ኢንተርቴይንመንት ለተባለ ድርጅት ባልተገባ ስፖንሰርሺፕ ብር 954 ሺህ 770 ብር የህዝብ ገንዘብ መስጠቱን እና ተጠርጣሪዋም ባልተገባ መልኩ መቀበሏን እና ማሸሿን እንዲሁም ይህን ገንዘብ በመጠቀም ሀብት ማፍራቷን ገልጿል።

ተጠርጣሪዋ በስፖንሰርሺፕ ያገኘሁት ገንዘብ ህጋዊ ነው፤ ይህም በወንጀል አያስጠይቀኝም፤ አራስ በመሆኔም ጉዳዩን ውጭ ሆኜ እንድከታተል ይፈቀድልኝ ስትል ጠይቃለች።

ሌላኛዋ ተጠርጣሪ ትእግስት ታደሰ የህብረት ማኑፋክቸሪንግ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ሀላፊ ከሆነ እና በቁጥጥር ስር ካልዋለ ተጠርጣሪ ጋር በመመሳጠር ያልተገባ ጥቅም አግኝተዋል፤ የህዝብ ገንዘብን ተቀብለው ሰውረዋል ሲል መርማሪ ፖሊስ ጠርጥሯቸዋል።

በምርመራ ወቅትም ከተጠርጣሪዋ መኖሪያ ቤት የመኪና ሊብሬ እና የቤት ካርታ ተገኝቷል ብሏል። ከዚህ ባለፈም ገና በማስረጃ የሚረጋገጥ በርካታ ንብረት መሰወራቸውን ነው ለፍርድ ቤቱ የተናገረው።

ተጠርጣሪዋ ወይዘሪት ትእግስት ታደሰ ከግለሰቡ ጋር በሚባለው ልክ ግንኙነት የለንም የሰወርኩት ንብረትም የለም፤ ተማሪ በመሆኔ በዋስትና ወጥቼ ጉዳዩን እንድከታተል ይፈቀድልኝ ሲሉ ጠይቀዋል።

ሌላኛው ተጠርጣሪ ቸርነት ዳና በድርጅታቸው ዋይቲኦ በኩል ከሜቴክ ያልተገባ ጥቅም አግኝተዋል፤ ህጋዊ የድለላ ፍቃድ ሳይኖራቸው ያለጨረታ ግዢ እንዲፈፀም አድርገዋል፤ ጥራት የሌላቸው ትራክተሮች እንዲገባ አድርገዋል ሲል የተጠረጠሩበትን ጉዳይ ልፍርድ ቤቱ አስረድተዋል።

ተጠርጣሪው ቸርነት ዳና በበኩላቸው ትራክተር የማቅረቡን ስራ ከሜቴክ ጋር የሰራሁት ከአራት ዓመት በፊት ነው በወቅቱም ተገቢው ቃለመጠይቅ ተደርጎና ተወዳድሬ ነው ስራውን የሰራሁት ብለዋል።

ባለቤቴ የስምንት ወር ነፍሰ ጡር በመሆኗ እና የሶስት ልጆች አባት በመሆኔ የዋስትና መብት ይፈቀድልኝ ሲሉ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።

በሶስቱም ተጠርጣሪዎች ላይ የቀረበው የዋስትና ጥያቄ ሊፈቀድላቸው አይገባም ሲል መርማሪ ፖሊስ የወንጀሉን ውስብስብነት በማስረዳት 14 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት ጠይቋል።

የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው ፍርድ ቤቱም የዋስትና ጥያቄያቸውን ውድቅ በማድረግ ለፖሊስ የ10 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል።

በባሃሩ ይድነቃቸውና ታሪክ አዱኛ – FBC

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   Ethiopia’s transition misrepresented. Reply to Obang Metho

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *