በትምህርት ዘመኑ ከ1 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት አለመግባታቸውን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ገለጸ፡፡ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ትምህርት መምሪያ ደግሞ ከ140 ሺህ በላይ የቅድመ መደበኛና የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ አይደለም ብሏል፡፡

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በሚገኙ 1ሺህ 47 የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በትምህርት ዘመኑ 544 ሺህ 408 ተማሪዎች እንደሚማሩ ቢታቀድም የተጠበቀውን ያክል ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤቶች አለመምጣታቸውን ከዞኑ ትምህርት መምሪያ ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡

የዞኑ ትምህርት መምሪያ ዕቅድ ዝግጅት ክትትል እና ግምገማ ቡድን መሪ አቶ በየነ መረሳ እንደተናገሩት ከመስከረም 14 ጀምሮ ትምህርት በሁሉም የዞኑ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እየተሰጠ ነው፤ ነገር ግን በትምህርት ዘመኑ ይማራሉ ተብለው ከታቀዱት ውስጥ 54 ሺህ 420 የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎች እስካሁን ወደ ትምህርት ቤት አመለመምጣታቸው ታውቋል፡፡

በተመሳሳይ 122 ሺህ 644 የቅድመ መደበኛ ተማሪ ሕጻናትን ለማስተማር ታቅዶ በትምህርት ገበታቸው የሚገኙት 35 ሺህ 813 ሕጻናት ብቻ መሆናቸውን አቶ በየነ ነግረውናል፡፡ በዚህ መረጃ መሠረት 86 ሺህ 831 ተማሪዎች ትምህርታቸውን የማይከታተሉ ናቸው፡፡

ዕድሜአቸው ለትምህርት የደረሱ፣ የነገ ሀገር ተረካቢ ሕጻናትን ወላጆች ወደ ትምህርት ተቋማት ከመላክ ይልቅ ማኅበራዊ ሥራዎችን እንዲሠሩ ቅድሚያ መስጠታቸው የችግሩ መንስኤ መሆኑንም ቡድን መሪው ነግረውናል፡፡ 
የትምህርት ሥራ የበርካታ አካላትን ቅንጅት የሚጠይቅ ቢሆንም አጋር አካላቱ ተገቢውን ክትትልና ግንዛቤ ፈጥረው ልጆቹ እንዲማሩ አለማድረጋቸውም ሌላኛው ምክንያት እንደሆነ አቶ በየነ አብራርተዋል፡፡

በአማራ ከልል 5 ሚሊዮን 853 ሺህ 888 ሕጻናት በመጀመሪያ ደረጃና በቅድመ መደበኛ መርሐ ግብሮች ይማራሉ ተብሎ ታቅዶ ነበር፤ ነገር ግን ከአንድ ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት አለመምጣታቸውን የቀድሞዋ የቢሮው የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ወይዘሮ አስቴር በርሄ ነግረውናል፡፡ እንደ ዳሬክተሯ ገለፃ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ትምህርት መምሪያን ጨምሮ አብዛኞቹ የክልሉ ትምህርት ተቋማት ላለፉት አራት ዓመታት በየዞኑ ‹‹ይማራሉ›› በማለት ሲያስተላልፏቸው የነበሩት መረጃዎች የተጋነኑ በመሆናቸው ቅሬታ ሲያነሱ ቆይተዋል፡፡

ትምህርት ቢሮው ‹‹በዓመቱ ትምህርት ማግኘት ያለባቸውን የክልሉ ተማሪዎች ቁጥር የሚወስነው ከክልሉ ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ቢሮ በሚያገኘው መረጃ መሠረት ነው፡፡ መረጃው ግን በተባለው መሰረት ላይገኝ ይችላል፡፡ በመሆኑም የክልሉ የሕዝብ ቆጠራ በትክክል ተቆጥሮ እንደገና እስካልመጣ ድረስ ቢሮው ይህን ዕቅድ በሚቀጥለው ዓመትም መጠቀሙን ይቀጥላል›› ብለውናል ወይዘሮ አስቴር፡፡

ቢሮው ይህን ይበል እንጂ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ብቻ በ2011 የትምህርት ዘመን ለመማር ከተመዘገቡ 587 ሺህ 894 የቅድመ መደበኛ እና የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ውስጥ 62 ሺህ 92 የሚሆኑት እየተማሩ አይደለም፡፡ በመሆኑም በዕቅድ እና በአፈጻጸም ላይ ከፍተኛ ልዩነት መኖሩን ታዝበናል፡፡

ዘጋቢ፡- ኃይሉ ማሞ – (አብመድ)
ፎቶ፡- ከድረ-ገጽ

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ሰበር ዜና – ትህነግ በዲፕሎማሲ ዘመቻ ቀውስ ገጠመው፤ “ በሃሰት መረጃ አሳፈራችሁን ” የቅርብ አጋሮቻቸው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *