ከጀርመን ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ በሐምሌ 8/1979 እንደተመለሥኩ ለአራት ወራቶች ብቻ አዲሥ አበባ እንድቆይ ከተደረገ በሁዋላ ደሤ ላይ ሠሜን ምሥራቅ እዝ መምሪያ ሢቋቋም ቀጠናውን ሥለምታውቀው ሂድ ተባልኩ፡፡ተምሮ ላፈር ይሏችሁዋል ይሄ ነው፡፡የእዙ አዛዥ ሜጀር ጀነራል አለማየሁ ደሥታ ነበሩ፡፡ያሁኑ ሜጀር ጀነራል ያንጊዜ ሻምበል አለምሸት ደግፌ የዩኒቨርሥቲ ትምህርቱን እንዲያቋርጥ ተደርጎ በረዳት ዘመቻ መኮንንነት ከአለቃው ከኮለኔል ለገሠ ዳኜ ጋር ከአአ ወደጢጣ ጦር ሠፈር ከትመዋል፡፡አለቃዬ ኮ/ላቀው ወ/ሠንበትም የእዙ ፖለቲካ መምሪያ ሐላፊ በመሆን እዙን መሥርቷል፡፡

ጀነራል አለማየሁ ደሥታ ደልዳላና ብሥል ቀይ ሢሆኑ የተረጋጉ ፂማቸውን ከአፍንጫቸው ሥር ወደ ከንፈራቸው በጣም ዝቅ አርገው የሚላጩ፡በአፍንጫቸውና በላይኛው ከንፈራቸው መሐከል ቢያንሥ አንድ ሤ/ሜ ያህል የሚተዉና ከርዳዳ ፀጉራቸው ደግሞ ከፊት ለፊት ተፈጥሮ ይሁን ቀለም እርግጠኛ አይደለሁም ግማሽ ነጭ ሆኖ ግርማ ሞገሥ አላብሥአቸዋል፡፡እሣቸው ባለፉበት ቦታ ወይም ከጨበጡህ የሚጠቀሙት ውድ ሽቶ ሙሉ ቀን ከምትሥበው አየር ጋር ተሥማምቶ መአዛው በቀላሉ የማይተው ሢሆን እርጋታቸው የሚገርም ነው፡፡

ጀነራል አለማየሁ በራሣቸው አለም ውሥጥ ብቻ የሚኖሩ እንደሌሎች አቻ ጀነራሎች የኢሠፓ ማእከላዊ ኮሚቴ አባልም ሆነ ተለዋጭ አባል ያልነበሩ፡በመንግሥቱ ኃ/ማ ጭምር የአድሀሪ ቤተሠብ ተብለው ይፈረጁ የነበሩ፡ ለይሥሙላ ግን የኢሠፓ ተራ አባል ሆነው በእዝ አዛዥነት የተመደቡ አብዛኛውን ያገልግሎት ጊዜያቸውን በውጭ በመከላከያ የተለያዩ የሥራ ዘርፎች ያሣለፉ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ወሎ የተመደቡ አዛዣችን ነበሩ፡፡

ኢሠፓ በመዋቅርና ያሥፈልጉኛል የሚላቸውን ግለሠቦች የፓርቲው ሀላፊዎች በግምባር እየቀረበ የማርክሢሥት ሌኒንሥቱ የፓርቲ አመለካከት የሀይማኖት ተከታዮችን ማቀፍ ባይፈቅድም ጀነራል አለማየሁ ይጠየፉት የነበረውን ሥርአትና ፓርቲ በግድ እየተገፉ እንዲያገለግሉ ተፈርዶባቸው ከደቡብ ወሎና ከሠሜን ወሎ የፓርቲ ተጠሪዎች ጋር እየተላተሙ ለሥርአቱ አልመች አሉ፡፡የክፍለሐገሩ ኢሠፓ ፅ/ቤት በፀጥታ ጉዳዮች ሥብሠባ ሢጠራቸው ምን አገባችሁ፡ ይሄ የሠራዊቱ ጉዳይ ነው፡፡ጦር ከሢቢል ጋር ሆኜ አልመራም አይመለከታችሁም ሥለሚሏቸው ከሢቢል ሕ/ሠብ ሊገኙ የሚገባቸው ተጨማሪ የመረጃ ግብዓቶች ነጠፉ፡፡
እኔ ከምድብ የርእዮተ አለም ሐላፊነቴ በተጨማሪ የእዙ መ/ድ አንደኛ ፀሐፊ ሆኜ ተመርጬ እየሠራሁ ሥለነበር ወርሐዊ ሥብሠባ ላይም እያረፈዱ ሥለሚመመጡ ባንድ ወቅት ተሠብሣቢው በሙሉ ለምን በሠአቱ አይገኙም በሚል የእለቱ የሥብሠባ አጀንዳ በሚያውክ መልኩ ጉዳዩ አሁኑኑ እልባት ያግኝ በሚል አዳራሹ ተናጋ፡፡እኔም በመጀመሪያ ጀነራል ለመንግሥትም ለፖርቲም ሥራ ከፍተኛ ሐላፊነት ተሠጥቶት እኛን እየመሩ ያሉ ሠዉ ኖት፡፡በፓርቲው ድርጅታዊ መመሪያ ሕግ ደግሞ መሠረታዊ ድርጅቶች ቁልፍ የፓርቲው የአባላት የግንኙነት መድረኮች ናቸው፡፡

የእርሦንም ሐላፊነት የሚያግዝ መዋቅር ሠአት ለማክበር ያጋጠሞት ችግር ምንድን ነው ግልፅ ያድርጉልን ብዬ በአክብሮት ለሥብሠባው መልሥ እንዲሠጡ ጠየኳቸው፡፡የመለሡት መልሥ ግን የኔና የናንተ ሠአት አጠቃቀም ላይ ችግር ካልኖረ በቀር በሠአቴ ነው የመጣሁት ብለው ደመደሙ፡፡በሣቸው አመራር ምቾት ያጡ መኮንኖችም ሹሞችም ወታደሮችም ያልተገባ የቃላት ምልልሥ እንዳይፈፅሙ ነገሩን መዝጋት ሥለነበረብኝ ጓዶች በመጀመሪያ ይሄን ጉዳይ በኮሚቴ አይተን በአጀንዳ አሥፈላጊም ከሆነ ለበላይ አካል አሥፈቅደን አሥቸኳይ ሥብሠባ ጠርተን እንወይበታለን፡፡በተረፈ ጓድ ጀነራል በኛና በርሦ መካከል ይሄን ያህል የሠአት መለያየት ካለ በወታደራዊ የግዳጅ አፈፃፀም ላይም ችግሩ ከፍተኛ ይሆናል፡፡

አቶትን በብዙሀኑ ልክ ያሥተካክሉ ወይም በእርሥዎ እዝ ሥር በኮንትሮባንድ ተይዘው የተቀመጡ ሠአቶች በወታደራዊ መደብር ውሥጥ ሥላለ አንዱን ቢጠቀሙ ችግር አይኖረውም ብዬ ተሣሥቀን የእለቱን አጀንዳ ተወያይተን ጨርሠን ወጣን፡፡የክ/ሐገሩ የኢሠፓ ኮሚቴ በሁዋላ ጀነራል ግርማ ንዋይ አየተመራ ሪፖርት ወደ ማእከላዊ ኮሚቴ የይነሡልን ጥያቄ በማብዛቱ ጀነራል አለማየሁ ደሥታ በአዲሡ ብ/ጀነራል አበበ ኃ/ሥላሤ ተተኩና ሌላው ድራማ ተተካ፡፡ እቀጥላለሁ፡፡

– ከሻለቃ ላቀው መንግስቴ ትክክለኛ የቀድሞውን የጤርሜዳ ውሎዎቻቸውን የጻፈትን ነው ለእናተ ሼር አደረኩት እባኮዎ ያንብብት !!!

የቀድሞው የተረሳነው ጦር

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *