በውብሸት ሙላት

በአገራችን የተከሰቱና እየተከሰቱ ያሉ የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጥያቄዎችን መፍትሔ ለማበጀት ይረዳ ዘንድ ኮሚሽን እንዲቋቋም አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ፀድቋል፡፡ በኮሚሽኑ ሥልጣንና ኃላፊነት ዙሪያም የተለያዩ ጥያቄዎች በተለያዩ መድረኮች በመነሳት ላይ ናቸው፡፡ ይህ ጽሑፍ አዋጁ በሚመለከት የተወሰኑ ነጥቦች በማንሳት ከሕገ መንግሥትና ሌሎች ሕጎች አንፃር ፍተሻ ለማድረግ ይሞክራል፡፡

አዋጁ በአጭሩና ምጥን ማብራሪያ

አዋጁ ሃያ አንድ አንቀጾችን ይዟል፡፡ እንዲቋቋም የተፈለገው ኮሚሽን በዋናነት በሁለት ጎራ ሊከፈሉ የሚችሉ ችግሮችን እልባት ለመስጠት ነው፡፡ አንዱ የአስተዳደር ወሰን ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ የማንነት ጉዳይ ነው፡፡ ወደ ውስጥ ጠለቅ ብሎ ላስተዋለው ግን የአስተዳደር ወሰን ነው ትኩረቱ፣ የማንነት ጥያቄዎችን ታክኮ ነው የሚያልፋቸው፡፡ ስለሆነም ማንነትን መሠረት ያደረጉ የአስተዳደር ወሰን ጥያቄዎች ዓብይ አጀንዳው ነው ማለት ይቻላል፡፡ ይህ አዋጅ እንዲዘጋጅ ምክንያት የሆነው በክልሎች መካከል የአስተዳደር ወሰን ጥያቄዎች በመነሳታቸው፣ ራስን በራስ ማስተዳደርና በማንነት ጥያቄዎች ዙሪያ በተደጋጋሚ የሚታዩ ችግሮች እየተበራከቱ ስለመጡ አገራዊ በሆነና ዘላቂ በሆነ መልኩ መፍታት አስፈላጊ ስለሆነ እንዲሁ በመግቢያው ላይ ተገልጿል፡፡ በወሰን ጉዳይ የብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝቦች መካከል ቅራኔ እየተፈጠረ ስለሆነ በገለልተኝነትና ሳይንሳዊ በሆነ ዘዴ መፍትሔ መስጠት ስለተፈለገ ነው፡፡

ከመግቢያው ባለፈም አንቀጽ አራት የኮሚሽኑን ዓላማ ይናገራል፡፡ በተለይ ጥያቄዎቹ የሚፈቱበትን ሥልት በሚመለከት አሳታፊ፣ ግልጽ፣ አካታችና ሳይንሳዊ እንዲሆን የግጭቶቹን መንስዔያቸውን በመተንተን የመፍትሔ ሐሳቦችንም ለተለያዩ አካላት ማቅረብ ነው፡፡ በዚህም መሠረት  ለሕዝብ፣ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ለአስፈጻሚው አካል  የመፈትሔ ሐሳብ ያላቸውን ያቀርባል። ከዓላማው እንደምንረዳው የአማካሪነት እንጂ የወሳኝነት ሥልጣን አይኖረውም፡፡

ትርጓሜዎችን ባስቀመጠበት በአንቀጽ ሁለት ላይ  ለአስተዳደር ወሰን ትርጉም የሰጠው ‹‹ራስን በራስ ማስተዳደር፣ ከማንነት ጥያቄና ከሌሎች ተመሳሳይ ክስተቶች ጋር በተያይዘ የሚነሱ የወሰን ጉዳዮች ነው፤›› በሚል ነው፡፡ ኮሚሽኑ የራሱ ጽሕፈት ቤትና ሠራተኞች የሚኖሩት ሲሆን፣ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚሆን በአዋጁ ላይ ሰፍሮ እናገኘዋለን፡፡ አዋጁ አንቀጽ አምስት ላይ የኮሚሽኑን ሥልጣንና ተግባር ዘርዝሯል፡፡ ሥልጣንና ተግባር የተባሉትም  ከአስተዳደራዊ ወሰኖች አከላለል፣ ራስን በራስ ማስተዳደር እንዲሁም ከማንነት ጥያቄ ጋር የተገናኙ ማናቸውንም ችግሮችንና ግጭቶችን ከነመንስዔያቸው በጥናት ለይቶ አማራጭ የመፍትሔ ሐሳብ ማቅረብ፣ በሕዝቦች መካከል እኩልነትና አንድነት እንዲሰፍን የሚረዱ ምክረ ሐሳብ ማቅረብ፣ አስተዳደራዊ ወሰኖች የሚለወጡበትና የሚወሰኑበትን ሁኔታ በማጥናት መፍትሔ ማቅረብ፣ ጎልተው ለወጡ ችግሮች የውሳኔ ሐሳብ ማቅረብ፣ በአጎራባች ክልሎች መካከል ያሉ ግንኙነቶችን ለማሻሻልና ለማጠናከር የተለያዩ ዘዴዎችን ማመቻቸት፣ በወሰን አካባቢ አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን ልማትና ንግድን ማፋጠን ይቻል ዘንድ የፖሊሲ ሐሳቦችን ማመንጨት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ እነዚህን ተግባራት ለመወጣት ጥናት ማከናወን፣ ከሕዝብና ከፖለቲካ ቡድኖች እንዲሁም ከሌሎች አካላት መረጃና አስተያየት ይሰበስባል፡፡

ከላይ የተገለጹት የኮሚሽኑ ተግባራት ናቸው፡፡ በራሱ መወሰን የሚችልባቸው ሥልጣናት የሉትም፡፡ የተጣሉበት ኃላፊነት ለውሳኔ የሚረዱ የመፍትሔ ሐሳብ ማቅረብ እንጂ በራሱ ውሳኔ ማሳለፍ ስለማይችል ሥልጣን አለው ማለት አይቻልም፡፡ በኮሚሽኑ ተጠንቶ የሚቀርቡት የመፍትሔ ሐሳቦች አግባብነት ያላቸውን ሕጎች መሠረት በማድረግ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ቀርቦ እልባት እንደሚሰጣቸው አዋጁ ይገልጻል፡፡ ውሳኔ ሰጪ አካሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው፡፡ እዚህ ላይ አንድ ተቃርኖ እናስተውላለን፡፡ የኮሚሽኑ ተጠሪነት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሆኖ ኮሚሽኑ አጥንቶ በሚያቀርበው ውጤት ውሳኔ የሚሰጠው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥር ያለ መሥሪያ ቤት የሚሠራው ግን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት መሆን ያልተለመደ አወቃቀር ነው፡፡ ወይ ተጠሪነቱ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ወይም የውሳኔ ሐሳብ የሚሰጠው በጠቅላይ ሚኒስትሩ መሆን ምክንያታዊ አወቃቀር ይሆናል፡፡

የኮሚሽኑን አባላት ብዛት መንግሥት (አስፈጻሚው አካል) ይወስንና በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይፀድቃል፡፡ ኮሚሽኑ ሰብሳቢና ምክትል ይኖሩታል፡፡ ጽሕፈት ቤትም ያደራጃል፡፡ የጽሕፈት ቤቱ፣ የሰብሳቢውና የምክትሉም ተግባራት ተለይተዋል፡፡ ኮሚሽኑ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ማንኛውም አካል የመተባበር ግዴታ እንዲኖርበትም ተፈልጓል፡፡ ሳይተባበሩ ቢቀሩ ምን እንደሚሆኑ ግን የቅጣት አንቀጽ የለውም፡፡ ለኮሚሽኑ ቃሉን የሰጠ ሰውም ጥቃትና ጉዳት እንዳይደርስበት ጥበቃ እንደሚደረግ እንዲሁ አዋጁ ይገልጻል፡፡

ኮሚሽኑ ገለልተኛ እንደሚሆንም አዋጁ ላይ ተጽፏል፡፡ ገለልተኛ እንዴት እንደሚሆን ግን ምንም ፍንጭ የለም፡፡ ኮሚሽኑ እንደተቋም ገለልተኛ ነው እንዳይባል ገለልተኛ የሚሆነው ከማን ነው? ከአስፈጻሚው አካል እንዳይባል ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትር (ለዋናው አስፈጻሚ) ነው፡፡ ደንብ እንዲያወጣ ሥልጣን የተሰጠውም ይኼው አስፈጻሚው አካል፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ነው፡፡ የኮሚሽኑ አባላት ከባለጉዳዮች ገለልተኛ እንዲሆኑ ተፈልጎም ከሆነ በአባላትና በባለጉዳዮች መካከል የጥቅም ግጭት በሚኖርበት ጊዜ ምን መደረግ እንዳለበት እንዲሁም የጥቅም ግጭት አለ የሚያሰኙ መለኪያዎችን ማስቀመጥ ይገባል፡፡ የኮሚሽኑ አባላት ብሔራቸውና ጥያቄ ከቀረበበት ማንነትን መሠረት ያደረገው የአስተዳደር ወሰን የሚመለከተው ብሔር ውስጥ በሚሆኑበት ጊዜ በጉዳዩ እንዳይሳተፉ ለማድረግ ታስቦም ከሆነ እንዲሁ መግልጽ ይገባል፡፡ ኮሚሽኑ ገለልተኛ የሚሆነው ከማን ነው የሚለው በግልጽ መቀመጥ ይጠበቅበታል፡፡ ካልሆነ ገለልተኛ ነው በማለት ብቻ ገለልተኛነት አይመጣም፡፡

እንግዲህ አዋጁ በአጭሩ ምጥን አስተያየትን ጨምሮ ይኼን ይመስላል፡፡ የኮሚሽኑ ኃላፊነት አስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ስለሚመለከት እነዚህን ሁለት ጉዳዮች መሠረት ያደረጉ ችግሮች በሚከሰቱበት ጊዜ የሚፈቱበትን አግባብ አጠር አድርገን እንቃኝ፡፡ የሚፈቱበት ሥርዓት ካለ የኮሚሽኑ ሚና ምን ሊሆን እንደሚችል ለመገንዘብ ይረዳል፡፡

የድንበር ጥያቄ አፈታት

ኢትዮጵያ እልባት ያላገኙ በርካታ የድንበር ጉዳዮች አሉባት፡፡ ከአዋሳኝ አገሮች ጋር ብቻ ሳይሆን በውስጥም በክልሎችና ከዚያ በታች በሚገኙ አስተዳደራዊ እርከኖች ላይ የድንበር ጉዳይ አሁንም ቢሆን እየቆየ የሚነሳ ወይም ደግሞ የሚያገረሽ ግጭትን እያስከተለ ይገኛል፡፡ ኢትዮጵያ እንደ አንድ ሉዓላዊ አገር ከሁሉም አዋሳኞቿ ጋር ያላለቀ የቤት ሥራ አለባት፡፡ በመሆኑም በውጭም በውስጥም ግጭት ያስነሱ ወይም ሊያስነሱ የሚችሉ በርካታ ሁኔታዎች አሉ፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ ክልል ከክልል ጋር ያላለቁ የድንበር ወይንም ወሰን ጉዳዮች አሉ፡፡ ግጭት ያስነሱና አሁንም በግጭት ውስጥ ያሉ አሉ፡፡ ክልሎቹ እንደ አንድ የመስተዳድር መዋቅርና እንደ መንግሥት ግጭት ውስጥ ባይሆኑም እንኳን የብሔር ግጭቶች ግን አሉ፡፡ በወልቃይት የሚኖሩ አማሮች የክልል ለውጥ በማንሳታቸው ግጭት ተከስቷል፡፡ በአማራና በአፋር፣ በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በኦሮሚያና በሶማሌ እንዲሁም በኦሮሚያና በደቡብ (ከሲዳማ፣ እንዲሁም ከጌዴዮ ብሔሮች ጋር) በተለያዩ ጊዜያት በተነሱ ውዝግቦች ንብረት ወድሟል፣ የሰው ሕይወት ጠፍቷል፡፡

የፌደራሉ ሕገ መንግሥት አንቀጽ ሁለት ላይ እንደተገለጸው የአገሪቱ የግዛት ወሰን (ድንበር) የክልሎቹ ወሰን ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ሲረቀቅ ይኼ አንቀጽ በዚህ መልኩ መደንገግ እንደሌለበት፣ ኢትዮጵያም እንደሌሎች ሉዓላዊ አገሮች ሁሉ፣ የራሷ የሆነ ዳር ድንበርና አዋሳኞች ሊኖሯት እንደሚገባ ክርክር እንደነበር ከተለያዩ ሰነዶች መረዳት ይቻላል፡፡ የኢትዮጵያ ድንበር ሳይቀር የሚወሰነው በክልሎች ሕግጋተ መንግሥት ነው እንደማለት ነው፡፡ በዚህ መሠረት ሁሉም ክልሎች አዋሳኞቻቸውን ብሎም ድንበራቸውን የደነገጉ ቢሆንም የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሕገ መንግሥት ግን የክልሉ ወሰን የዞኖቹና የወረዳዎቹ ነው በማለት ደንግጓል፡፡ ይሁን እንጂ እንኳንስ ወረዳና ዞን ይቅርና ክልሎችም ከሌሎች ሉዓላዊ አገሮች ጋር ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን መዋዋል ስለማይችሉ ይህ ዓይነቱ በክልል፣ በዞንና በወረዳ የኢትዮጵያን የግዛት ወሰን በተለይም ከሌሎች ሉዓላዊ አገሮች ጋር የምትዋሰንባቸውን ድንበሮች መለየት ለአፈጻጸምም አስቸጋሪ ነው፡፡ ክልሎቹ ከሉዓላዊ አገሮችና ከሌሎች ክልሎች ጋር ይዋሰናሉ፡፡ ከሌሎች አገሮች ጋር በሚዋሰኑበት ጊዜ ጉዳዩ ዓለም አቀፍ ሲሆን፣ ከሌላ ክልል ጋር በሚዋሰኑበት ድንበር ምክንያት የሚነሱት ጉዳዮች ደግሞ የፌዴራል ይሆናሉ፡፡ ከዚህ በተቃራኒው ድንበርን በተመለከተ ጥቅልል አድርጎ የክልል ማድረግ ተጠየቃዊ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ እንደ ፌዴሬሽን ግዛቷ (Territory)  የክልሎቹ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ነገር ግን፣ የግዛት ወሰኗ ደግሞ በጥቅሉ የክልሎቹ ሳይሆን ክልሎቹ ከሌሎች ሉዓላዊ አገሮች ጋር ያላቸው ድንበር (Border or Boundary) ነው፡፡ ስለሆነም፣ ክልሎቹ ከሌሎች አገሮች ጋር የሚዋሰኑበትን የድንበር አከላለልና ተያያዥ ጉዳዮች በፌዴራሉ መንግሥት ሥልጣን ሥር እስካልሆኑ ድረስ ሁኔታዎቹን የበለጠ ውስብስብ ያደርጋቸዋል፡፡

በክልልና በክልል መካከል የሚነሱ የድንበር ውዝግቦች ለመፍታት የሚረዱ የተለያዩ ሕጋግትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በቀዳሚነት ሊነሳ የሚችለው የፌዴራሉ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 48 ነው፡፡ በዚህ አንቀጽ መሠረት የድንበር አለመግባባት በሁለት ክልሎች መካከል ሲፈጠር በቀዳሚነት ክልሎቹ በስምምነት እንዲጨርሱ ነው የተደነገገው፡፡ በራሳቸው መስማመት ካልቻሉ በፌዴሬሽን ምክር ቤት አማካይነት ውሳኔ ይሰጣል፡፡ የፌደሬሽን ምክር ቤት ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ እንደተገለጸው ምክር ቤቱ በብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝቦች መካከል አንድነትና መፈቃቀድ እንዲያድግ ኃላፊነት አለበት፡፡ በክልሎች መካከል አለመግባባት ሲፈጠር ውሳኔ የመስጠት ሥልጣኑም የእሱው ነው፡፡ በሁለት ክልሎች መካከል ውዝግብ አለኝ የሚል ክልል ለሌላው ክልል በጽሑፍ እንዲያውቀው ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ መጥሪያው የደረሰው ክልልም በ45  ቀናት ውስጥ ለውይይት ዝግጁ መሆኑን ማሳወቅ ይጠበቅበታል፡፡ ድርድሩንም ወይም ውይይቱን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ይከታተለዋል፡፡ በዚህ ሁኔታ መፍተሔ ካልተገኘ ወይም አንዱ ክልል ለውይይት ዝግጁ ካልሆነ ለምክር ቤቱ አቤቱታ ማቅረብ ይቻላል፡፡ ምክር ቤቱም ለጊዜው ተገቢ የመሰለውን ትዕዛዝ ሊሰጥ ይችላል፡፡ በተለይ ግጭቶች ካልቆሙ ለማስቆም የሚያስችል ተገቢ የሆነ ጊዜያዊ ውሳኔ/ዕርምጃ የመስጠት ሥልጣን አለው፡፡ የመጨረሻ ውሳኔ ለመስጠት ግን ማስረጃዎችን መመርመርና መልስ ከሌላው መቀበል ይጠበቅበታል፡፡ ይህ በድንበርም ወይም በሌላ ምክንያት ለሚነሳ አለመግባባት በጥቅሉ የተቀመጠ አሠራር ነው፡፡ 

የድንበርን አለመግባባትን በተመለከተ ተጨማሪ ድንጋጌዎች አሉ፡፡ ይኼውም  ከውሳኔ በፊት የሕዝቡን አሰፋፈር ማጥናትና ፍላጎታቸው ምን እንደሆነ ማወቅ ግድ ነው፡፡ በሕዝቡ አሰፋፈር ብቻ መወሰን የሚቻል ከሆነ በዚያው ያልቃል፡፡ በዚህ የሚቋጭ ካልሆነ ግን ወደ ሕዝቡ ፍላጎት መሄድ ሁለተኛው ደረጃ ነው፡፡ የሕዝቡን ፍላጎት ለማረጋገጥ ደግሞ በቀበሌ ደረጃ በሚከናውን ሕዝበ ውሳኔ በምርጫ ቦርድ አማካይነት ይፈጸማል፡፡ ድምፅ ለመስጠት የሚችለው በአካባቢው የሚኖረው ሕዝብ ሲሆን፣ በግጭቱ ምክንያት የተፈናቀለ ሰው ግን ድምፅ ሊሰጥ ይችላል፡፡ በውጤቱም መሠረትም አካባቢው የማን እንደሆነ ይለያል፡፡

የማንነት ጥያቄ አፈታት

በ2009 ዓ.ም. ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር)፣ የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ሥራቸውን ሲጀምሩ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ላይ ትኩረት ካደረጉባቸው ነጥቦች ውስጥ አንዱ ያልተመለሱ የማንነት ጥያቄዎችን የሚመለከት ነው፡፡ ከእሳቸው በተጨማሪም በእዚያ ዓመት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝም ስለዚሁ ጉዳይ በተደጋጋሚ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ የፕሬዚዳንቱም ይሁን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ያደረጓቸው ንግግሮች ዋቢነታቸው የማንነት ጥያቄዎች መኖራቸውን ብቻ ሳይሆን በአንድ በኩል ማንነትን በሚመለከት በርካታ ያፈጠጡ ኢፍትሐዊ ተግባራት መኖራቸውን፣ በሌላ በኩል እነዚህ ችግሮች እየተፈቱ አለመሆናቸውንና መንከባለላቸውን መቀጠላቸውን እንዲሁም እየጨመሩ መሄዳቸውን ያሳያሉ፡፡ ማንነት ላይ የተመረኮዙ ጥያቄዎች እየጨመሩ እንጂ ሲቀንሱ አልተስተዋሉም፡፡ ይባስ ብሎም በመሠረታዊነት የማንነት ያልሆኑ ጥያቄዎቹን ማንነታዊ ቅርፅ መስጠት እየተዘወተረ ነው፡፡ ጥያቄዎቹም ግጭትን መጥራት የተለመደ ፀባያቸው እየሆነ ነው፡፡

በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ውስጥ የሚኖሩ ብሔሮች ማንነታቸውን መነሻ በማድረግ የክልልነት ጥያቄ እያነሱ ነው፡፡ በዚሁ ክልል ውስጥ የሚኖሩ ሌሎች ብሔሮች እንዲሁ ማንነታቸውን መለያ በማድረግ የልዩ ወረዳ ወይም የልዩ ዞን  ምሥረታ ጥያቄ አንስተው የተመለሰላቸውም ያልተመለሰላቻውም አሉ፡፡ ከዚህ በመለስም እንደ ብሔር የመታወቅ ጥያቄ አንስተው ምላሽ ሳያገኙ ዓመታት ያሳለፉም አሉ፡፡

በሌሎች ክልሎች (ለምሳሌ በትግራይ) የሚኖሩ ደግሞ አሁንም ማንነታቸውን መነሻ በማድረግ ወደ አማራ ክልል እንካለል በማለት ጥያቄ ካነሱ ውለው አድረዋል፡፡ ግጭትም በማስከተላቸው ሰብዓዊና የንብረት ጉዳትም ደርሷል፡፡ እንዲህ ዓይነት ጥያቄዎች እየተበራከቱ በመሄዳቸው ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እልባት መስጠት አስፈላጊ መሆኑ አጠያያቂ አይደለም፡፡ ይሁንና ልዩ ትኩረት በመስጠት መፍትሔ ለመሻት የተለያዩ አማራጮች ሊኖሩ ስለሚችሉ ከእነሱ የተሻለውን መምረጥ ይገባል፡፡ የማንነት ጥያቄዎች በክልል በኩል መፍትሔ ማግኘት ካልቻሉ የመጨረሻ እልባት እንዲሰጥ በሕገ መንግሥቱ የተቋቋመው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ስለሆነ ይኼው ተቋም አሁን ባለበት አወቃቀር ምላሽ እንዲሰጥ መሞከር አንዱ ሲሆን፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በራሱ የተለያዩ አጋዥ ተቋማትን በማደራጀት ሲንከባለሉ የኖሩትንም አዳዲስ ጥያቄዎችን በፍጥነት መልስ መስጠት ደግሞ ሌላው አማራጭ ነው፡፡ በአዋጁ ላይ እንደቀረበው ያለ መሥሪያ ቤት (ኮሚሽን) በማቋቋም ለችግሩ መፍትሔ ለመስጠት በአማራጭነት ወይም በተጨማሪነት መሞከርም ሌላው ነው፡፡

እንግዲህ የማንነት ጥያቄዎችን በሚመለከት ስለኮሚሽኑ ተገቢነት አስተያየት ለመስጠት በቀዳሚነት የማንነት ጥያቄ አፈታትን በሚመለከት በሕግ የተቀመጠውን ሥነ ሥርዓት በአጭሩ እንመልከት፡፡

የማንነት ጥያቄ ያለው ቡድን ጥያቄውን ለማን ነው የሚቀርበው? ወይም በሌላ አገላለጽ የማንነትን ጥያቄ የመጨረሻ ወሳኙ ራሱ የማኅበረሰቡ አባላት ቢሆኑም ጥያቄው መቅረብ ያለበት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ወይስ ለክልል ነው? የሚል ነው፣ ሕገ መንግሥቱ ግልጽ የሆነ መልስ ስለሌለው የፌዴሬሽን ምክር ቤት የማንነት ጥያቄ ዞሮ ዞሮ ዋና ዓላማው ራስን ማስተዳደር ስለሆነ ይህን ጥያቄ የመፍታት ሥልጣን በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 52(2)(ሀ) መሠረት የክልል ምክር ቤት ነው በማለት ወስኗል፡፡

የማንነት ይታወቅልኝ ጥያቄ ብሔርን መሠረት ያደረገ አስተዳደራዊ ተቋማት ከመመሥረት እንዲሁም ክልል ከማቋቋምም ይቀድማል፡፡ እነዚህን ጉዳዮች የመወሰን ሥልጣን የክልል ከሆነ የማንነትማ ወደ ፌዴራል ተቋማት በቀጥታ ሊሄድ አይችልም፡፡ ይሁን እንጂ በክልሉ ምክር ቤት ውሳኔ ወይም በሚሰጣቸው ምላሾች ቅር የተሰኘ ወገን የመጨረሻ መፍትሔ ለማግኘት ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ሊሄድ ይችላል፡፡ ይህንን በስልጤ ጉዳይ ከተሰጠው ውሳኔም ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 62(3) ማለትም ‹‹የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል መብትን በተመለከተ በሚነሱ ጥያቄዎች ላይ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ይወሰናል፤›› ከሚለው መረዳት ይቻላል፡፡

የኮሚሽኑ ሕገ መንግሥታዊነት

የድንበርና የማንነት ጉዳዮችን በሚመለከት የመጨረሻ ውሳኔ የሚሰጠው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው፡፡ ኮሚሽኑ ውሳኔ መስጠት እንደማይችል አዋጁ ግልጽ አድርጓል፡፡ የሚቋቋመው ኮሚሽን የአማካሪነት ሚና ኖሮት ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሆነ የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ሚና አልተካም ማለት ነው፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤትም ከዚህ ኮሚሽን የጥናት ውጤት ሊጠቀም ይችላል እንጂ የሚገደድበት አግባብ የለም፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የተጣለበትን ኃላፊነት በአግባቡ ባለመወጣቱ እነዚህ ችግሮች እልባት እያገኙ እንዳልሆነ የተገነዘበው አስፈጻሚው አካል አገሪቱን ለማስተዳደር ስለተቸገረ በራሱ በኩል የመፍትሔ ሐሳቦችን ለማቅረብ የሚያግዘውን ተቋም ቢመሠረት የሚከለክለው ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ የለም፡፡ ስለሆነም ኮሚሽኑ ቢኖርም ባይኖርም የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕግ የተጣለበትን ኃላፊነት ይዞ ይቀጥላል፡፡

አሁን ላይ ያጋጠሙ ችግሮችንም ለመፍታት ያስችሉኛል ያላቸውን ዘዴዎች ተግባራዊ ከማድረግ የሚከለክለው የለም፡፡ ውሳኔ ካላሳለፈ፣ በእሱ ሥር እንዲሆን ካልተደረገ ሚናው በዋናነት ለአስፈጻሚው አካል ግብዓት የሚውል የመፍትሔ ሐሳብ ማቅረብ ነዉ፡፡ ለፌዴሬሽን ምክር ቤትም ያቀርባል ከፈለገ ይጠቀምበታል፡፡ ካልፈለገም አይጠቀምበትም፡፡ ስለሆነም ሕገ መንግሥታዊ አይደለም የሚያሰኘው ምክንያት የለም ማለት ይቻላል፡፡

የኮሚሽኑ አስፈላጊነት

የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጥያቄዎችን በሚመለከት ኮሚሽን ማቆም ተገቢነት በሚመለከት ከጥያቄዎቹ ብዛትና ለአገራዊ ህልውና ተግዳሮት እየሆኑ ከመምጣታቸው አኳያ ኮሚሽን ማቋቋሙ ተመራጭ ሊሆን ይችላል፡፡ በተለይ የወሰን ጉዳይን በሚመለከት የኮሚሽን መቋቋም ተገቢ ይመስላል፡፡ አንድ አገር በተለይ ከአሃዳዊነት ወደ ፌዴራል ስትዋቀር ቀድሞ የሚነሳው የፌዴሬሽኑ አባላት የሚሆኑት፣ ክልልም ይባሉ ሌላ፣ እንዴት እንደሚካለሉና እንደሚዋቀሩ  መሥፈርቶቹን  የመለየት ጉዳይ ነው፡፡ መሥፈርቶቹን ከለዩ በኋላም የሚነሱ ሁለት ተግባራት አሉ፡፡ የክልሎቹን ድንበር በወረቀት ማለትም በካርታና በስምምነት ማስቀመጥ (Delimitation) እና በወረቀት ላይ የተቀመጡትን በተግባር ወደ መሬት በማውረድ የማስመርና ማካለል ወይም ድንበር መደካት (Demarcation) ሥራዎች ናቸው፡፡

አገሮች አስቀድመው የድንበር ኮሚሽን በማቋቋም ስንት ክልሎችና ወሰናቸው የሚያርፍበትን ቦታ ጭምር ለይተው በማቅረብ የሕገ መንግሥቱ አካል እንዲሆኑ ያደርጋሉ፡፡ ደቡብ አፍሪካ ለዚህ ምሳሌ ናት፡፡ ከበርካታ የሙያ ዘርፍ የተውጣጡ የፖለቲካ ሹመኞች ሆነው የማያውቁ ሰዎች የተካተቱበት አንድ ኮሚሽን በማቋቋም ስንት ክልሎች እንዲሁም ምን ምን ጉዳዮችን መሥፈርት በማድረግ እንደሚዋቀሩ ባቀረቡት አስተያየት መሠረት አገሪቱ ከእንደገና ተዋቀረች፡፡ በተለይም ዘርን፣ ቀለምንና ብሔር ጋር የተያያዙትን እንዲቀሩ አሳሳበ፡፡

ሕገ መንግሥታቸው ከፀደቀም በኋላ ቢሆን በሕገ መንግሥቱ ስለድንበር ለውጥና አከላለል እንዲሁም ስለድንበር ኮሚሽን ያካተቱም አሉ፡፡ ናሚቢያን ብንወስድ፣ እንደምን በማድረግ ክልል መዋቀር እንዳለበት፣ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ የሚመራ ኮሚሽን አቋቁማ በተለይ ዘርን ለፖለቲካ አስወግደው ከእንደገና በተሳካ ሁኔታ አገራቸውን አካልለዋል፡፡ የክሎቹን ብዛት እንዲሁም ዋና መሥፈርቱ አገራዊ የልማትና ማኅበራዊ ትስስር መሆን እንዳለበት ባስቀመጠው መሠረት ተፈጸመ፡፡ ናይጄሪያ ደግሞ በተለያዩ ጊዜያት የድንበር ለውጦችና ክልሎችን እንዲካለሉ አድርገዋል፡፡ ከሦስት ወደ ሰላሳ ስድስት ሲያድጉ ብዛታቸውንም ድንበራቸውንም በሕገ መንግሥቱ በሌሉ ነገር ግን በተለያዩ ጊዜያት በተቋቋሙ ኮሚሽኖች አሳክተዋል፡፡ ከደቡብ አፍሪካና ናሚቢያ በተለየ የናይጄሪው በአንድ ክልል ውስጥም ይሁን በፌዴራል ደረጃ የብሔር የበላይነትና የበታችነት እንዳይኖር ተግተው በመሥራት አቃለውታል፡፡ በግብነት ይዘውት የነበረውም ኢኮኖሚያዊ ልማትን ማፋጠን፣ አሳታፊ ዴሞክራሲ፣ የተመጣጠነ ውክልና ያለበትና የተረጋጋ የፌዴራል መንግሥት፣ የብሔር የበላይነትና የበታችነትን ማስወገድ ዋናዎቹ ነበሩ፡፡ በተለይ በአንድ ወቅት በብሔሮች መካከል የነበረው ጥላቻና ጥርጣሬ ስላደገ  እሱን ለመቀነስና ለመቅረፍ ተጠቅመውበታል፡፡

ቀድሞ የተለያዩ አገሮች ኋላ ላይ በፌዴሬሽን ሲዋሃዱ ብዙ ጊዜ ችግር አይከሰትም፡፡ ቢሆንም ግን፣ በክልሎች መካከል የሚነሳን የድንበር ውዝግብ ለመቅረፍ ሲባል የፌዴራል መንግሥቱ ሥልጣን እንዲሆን አድርገዋል፡፡ የድንበር ውዝግብ የአንድ ክልል ጉዳይ ብቻ ስላልሆነ በስምምነት ከሚፈታው በመለስ ላለው ጉዳይ ኃላፊነቱ የፌዴራል መንግሥት ስለሆነ ሕግ ማውጣትም መቆጣጠርም መከታተልም ይጠበቅበታል፡፡ የአሜሪካ ሕገ መንግሥት ለዚህ ጥሩ ዋቢ ነው፡፡ዓለም አቀፍ ልማዱ ይኼን ከመሰለ በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥቱ ከመጽደቁ በፊት ክልሎቹ ተስማምተው ነፃና ገለልተኛ ድንበር ኮሚሽን ተቋቁሞ ወሰናቸውን ስላልለዩ ወይም ደግሞ ወሰናቸውን ለይቶ የሚያሳውቅ ኮሚሽን ሕገ መንግሥቱ ሲፀድቅ ባለመወሰኑ ቀድሞ ያልተሠራውን ተግባር የሚሠራ ኮሚሽን ቢቋቋም ለአገር ይጠቅማል፡፡

ይሁን እንጂ በአዋጁ ላይ የተመለከተው ኮሚሽን የአስተዳደር ወሰንን በሚመለከት ውሳኔ መስጠት አይችልም፡፡ በዚያ ላይ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው፡፡ አባላቱን የሚመለምለው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚያፀድቀው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው፡፡ የአስተዳደር ወሰን ጉዳይ ግን የክልሎች ነው፡፡ ክልሎች በስምምነት መፍታት ከቻሉ ይፈቱታል፡፡ ካልሆነ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ይወስናል፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዳለ ሆኖ ክልሎች ተስማምተው አንድ ኮሚሽን ሊያቋቁሙ ይችላሉ፡፡ በክልል ሕገ መንግሥት የክልልን ድንበር በመወሰን ረገድ ከሌላ ክልል ጋር የመስማማት ሥልጣን ያላቸው አካላት በጋራ ወይም ደግሞ የወሰን ችግር ያለባቸው ተነጥለው ኮሚሽን ሊያቋቁሙ ይችላሉ፡፡ ይህን ለማድረግ ግን በክልል አመራሮች ዘንድ ቅን ልቦናና የትብብር መንፈስ መኖር አለበት፡፡ የፌዴራል መንግሥቱም ይህ ዓይነት ኮሚሽን እንዲቋቋም ማስተባበር ይጠበቅበታል፡፡ በእንዲህ ዓይነት ኮሚሽን የሚሰጡትን ውሳኔዎች አስገዳጅ እንዲሆኑ ክልሎች ሊስማሙ ይችላሉ፡፡ 

ለማጠቃለል ያህል በአዋጁ ላይ የተገለጸው ኮሚሽን በአገሪቱ እያጋጠሙ ያሉ የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጥያቄዎችን በዘላቂነት ለመፍታት ይቻል ዘንድ ምን መደረግ እንዳለበት የመፍትሔ ሐሳቦችን ሊያቀርብ ይችላል፡፡ ኮሚሽኑ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በመሆኑ፣ ሚናውም የአማካሪነት ስለሆነ የፌዴሬሽን ምክር ቤትን የሚተካ አይደለም፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤትም የኮሚሽኑን ግኝት እንዲጠቀምና ሥራ ላይ እንዲውል የሚያስገድድ የሕግ ማዕቀፍ የለም፡፡ ስለሆነም የኮሚሽኑ መቋቋም በጎ ቢሆንም ከዚህ በተሻለ መፍትሔ ሊያስገኝ በሚችል ሁኔታ ቢቋቋም የበለጠ ለአገር ይበጃል፡፡

አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው wuobishett@yahoo.com ማግኘት ይቻላል፡፡

Reporter Amharic

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *