ዩጎዝላቪያ አንድ ወቅት አውሮፓ ውስጥ ታላቅ ከሚባሉት አገሮች አንዷ ነበረች። የፊልድ ማርሻል ጆሴፍ ቲቶ፣ የማዜር ቴሬዛ አገር። ስድስት ክፍለ ሃገራት የነበሩበት የፊዴራል ስርዓት ነበራት። ክፍለ ሃገራቱ ሰርቢያ፣ ሞንቴኔግሮ፣ ቦዝኒያ ሄርዞጊቪና፣ ማሳዶኒያ፣ ክሮዊሺያና ስሎቬኒያ ነበሩ። በሰርቢያ ክፍለሃገር ውስጥ ደግሞ ኮሶቮና ቮጅቮይዳና የሚባሉ የራስ ገዝ አስተዳደሮችም ነበሩ።

ከሁለተኛ አለም ጦርነት በኋላ ዩጎዝላቪያን ሲገዙ የነበሩ ጆሴፍ ቲቶ ከሞቱ በኋላ በአገሪቷ ብሄረተኝነት ማቆጥቆጥ ጀመረ። ከዚያም የተነሳ ወደ አስር አመታት ገዳማ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ አገሪቷ ተዘፈቀች። ፌዴረሺኑ ፈረሰ። ከአንዲቷ ዩጎዝላቪያ ሰባት ትናንሽና ደካማ አገሮች ተፈጠሩ።

በቀዳሚነት ከፊዴረሽኑ የወጣችሁ ጀርመን ድንበር ላይ ያለችው ስሎቪኒያ ነበረች። ስሎቬኒያ በብዛት ስሎቬኒያዉያን የሚኖሩባት ስለነበረች፣ መጀመሪያ አካባቢ ከፌዴራል መንግስቱ ጋር ከነበሩ የአሥር ቀናት ጦርነት ውጭ ብዙ የከፋ ቀውስ አላጋጠማትም። የሕዝብ መፈናቀል፣ የዘር ማጽዳት ተግባራትም ብዙ አልታዩም። በሞንቴነግሮም ብዙ ጦርነት አልተከሰተም። በሰርቢያ፣ በክሮዌሺያ፣ በቦስኒያ ሄርዞጎቪናና በማሳዶኒያ ግን አንድ ዘዉግ ብቻ የሚኖሩባቸው አካባቢዎች ስላልነበሩ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሊፈጠሩ ችለዋል።

በክሮዊሺያ እጅግ በጣም ብዙ ሰርቦች ይኖሩ የነበረ። በቦዚያን ሄርዞጎቪና ደግሞ ከቦስኒያኖች ጎን ሰርቦችና ክሮዊሺያኖችም፣ በሰርቢያ ከሰርቦች በተጨማሪ ቁጥራቸው እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ የኮሶቮ አልቤኒያኖች የነበሩ ሲሆን፣ በማሳዶኒያ ደግሞ አንድ አራተኛ የሚሆነው ነዋሪ አልቢኒያኖች ነበሩ። ክፍለ ሃገራቱ የተለያዩ ማህበረሰባትን ያቀፉ እንደመሆናቸው፣ በክፍለ ሃገራቱ የተከሰተው ብሄረተኝነት አንዱን ከሌላው በማላተም ፣ ምን አልባትም ከሁለተኛ አለም ጦርነት በኋላ ፣ በአዉሮፓ አህጉር፣ የከፋ የሚባል፣ የደም መፈሰስ፣ የሕዝብ ጅምላ እልቂትና የዘር ማጻዳት እንዲከሰት አድርጓል።

እንደ አዉሮፓዊያን አቆጣጠር ከ1991 እስከ 2000 ዓ.ም ባለው ጊዜ በዩጎዝላቪያ በተከሰተው ዘር ተኮር ጦርነቶች በክሮዊሺያ ሁለት መቶ አርባ ሺህ ክሮዊሺያኖች እና ከሶስት መቶ ሺህ በላይ ሰርቦች፣ በቦዝኒያ ሄርዞጎቪና አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ቦስኒያኖች፣ አራት መቶ ዘጠና ሺህ ክሮዌሺያኖችና አምስት መቶ አርባ ሺህ ሰርቦች፤ በሰርቢያ ራስ ገዝ ስር በነበረችው ኮሶቮ፣ ከአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን በላይ የኮሶቮ አልቤኒያኖች እና መቶ አርባ ሺህ ሰርቦች፣ በሌላዋ የሰርቢያ ራስ ገዝ አስተዳደር ቮጅቮዲና ሰላሳ ሺህ ክሮዊሺያኖችና አርባ ሺህ ሰርቦች በግፍና በጭካኔ ከቅያቸው ተፈናቅለዋል። በክሮዊሺያ ክራጂና የሚባል ሰፊ ግዛት ነበር፣ ሰርቦች በብዛት የሚኖሩበት። ያ አካባቢ አሁን የዘር ማጽዳት ተፈጽሞበት ሰርቦች አይኖሩበትም። በቦስኒያ ሄርዞጎቪና እንደ ሰብረኒሻ ያሉ ምስራቃዊ አካባቢዎች የሚኖሩ ቦስኒያኖች ላይ የዘር ማጽዳት ወንጀል ተፈጽሟል። በቦስኒያ ደቡብ ይኖሩ የነበሩ ክሮዎሺያኖች ተመሳሳይ እድል አጋጥሟችዋል።

በዩጎስላቪያ ከአስር አይበልጡም የነበሩትን ብሄረሰቦች። አገራችን ኢትዮጵያ ከሰማኒያ በላይ ብሄረሰቦች አሉ። ልዩነቶቻችን እንደ ዉበታችን በመቁጠር እንደ አንድ ሕዝብ ተያይዘን፣ ተከባብረን መኖር ካልቻልን ወደ ኋላ መቅረት ብቻ ሳይሆን ከዩጎዝላቪያ በባሰ እልኩ፣ እንደ ሕዝብ እንጠፋለን። እንጠፋለን ብቻ ሳይሆን መጠፋት ጀምረናል። ብዙ አሳዛኝ ቀውሶችን እያየን ነው። ኦሮሞነትን፣ ትግሬነትን፣ አማራነትን፣ ሶማሌነትን… መቀንቀን ስለመጣ፣ ለራስ ዘዉግ/ዘር ብቻ መቆም ስራችን ስለሆነ፣ ይሄ የኛ ነው ብለን ሌላውን እንደ መጤ እየቆጠርን፣፣ የአግላይና ሌላዉን የሚጠላ ብሄረተኝኘት ሰለባዎች እየሆንን ፍጻሚያችን እርስ በርስ መተላለቅ እየሆነ ነው።

በዩጎዝላቪያ ነጮች ስለሆኑ፣ እነ አሜሪካ ጣልቃ ገብተው ጦርነቱ እንዲቆም አደረጉ። እኛ በጎሳና በዘር መፋጀት ከቀጠለ እንተላለቃለን እንጂ ማንም እኛን ለማዳን አይመጣም። እንደውም ደስ ነው የሚላቸው። ለምን እኛ ስንተላለቅ በግርግር መሬታችንን ይወስዱታል።

እኛ አገር፣ ይኸው ላለፉት ሃያ ስምንት አመታት፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባዬ፣ ኢሰመጉ፣ በተለያዩ ጊዚያት በስፋት ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ በዘርና በማንነት ላይ የተመሰረቱ ግጭቶች መከሰታቸውን መረጃ ላይ በመደገፍ ሪፖርት አድርጓል። የብዙ ወገኖች ሕይወት ጠፍቷል። ከፍተኛ የንብረት ዉድመትና የዜጎች መፈናቀል ተከስቷል። ከኢሰመጉ ሪፖርት ጥቂቶቹን እንደሚከተለው ተዘርዝረዋል።

1. አማርኛ ተናጋሪዎች በአርሲ አስተዳደር ፣ በአርባ ጉጉ፣ በመርቲ፣ ደጁ፣ በጎለልቻ ወረዳዎች በርካታ ሰዎች ተገድለዋል።

2. በአርሲ ነገሌ ወረዳ ቁጥራቸው በርክታ በሆኑ የአማራና የከምባታ ብሄረሰቦች ተወላጆች ላይ ግድያ ተፈጽሟል። ንብረት ወድሟል

3. በበደኖ ከተማ በሰላማዊ ዜጎች ላይ አሰቃቂ ግድያ ተፈጽሟል።

4. በከፋና በኢሊባቡር አስተዳደር አካባቢዎች በጉራጌ ማህበረሰብ አባላት ላይ ከመኖሪያ የማፈናቀል ኢሰብዓዊና ሕገ-ወጥ ድርጊት ተፈጽሟል።

5. በኦሮሚያ ጂማ ዞን የየም ብሄረሰቦች ወደ ደቡብ ክልል ለመቀላቀል ጥያቄ በማቅረባቸው በኦሮሚያ ታጣቂዎች ተቀድለዋል

6. በሶማሌ ክልል የሚኖሩ የሬርባራባ የዱቤ ጎሳዎችም ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ጠይቀው በሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ ተደብድበዋል፤ ተገድለዋል።

7. በደቡብ ክልል በሲዳማ ዞን ወንዶ ገነት ወረዳ ነዋሪዎች የሆኑ የጉጂ ብሄረሰብ አባላት ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ በማንሳታቸው ምክንያት በሲዳማ ዞን በሚኖሩ የሲዳማ ብሄረተኞች ብዙ ዜጎች ተገድለዋል።

8. በወልቃይት ጠገዴ ተደራጅተው፣ ሰላማዊ በሆነ መንገድ የማንነት ጥያቄ ያነሱ ዜጎች ወደ ወህኒ ተወስደዋል።

9. በመተከል አስተዳደር ከግንቦት ወር 1983 ዓ.ም ጀመሮ በበርካታ የአማርኛ ቋንቋ ታናጋሪ ዜጎች ላይ አሰቃቂ ግድያ ተፈጽሟል።

10. በኦሮሚያ ዞን ጊጂ፣ አዶላ ወረዳ ሸኮሶና በቦሬ እና በደቡብ ክል በጌእዶ የተፈጸሙ የጎሳ ግቶች ከፍተኛ እልቂት ፈጥረዋል።

11. በኦሮሚያና በቤኔሻንጉል ጉሙዝ ብሄራዊ ክልሎች መካከል ባሉ አዋሳኝ ቀበሌዎች ነዋሪዎች በሆኑ የኦሮሞና የጉሙዝ ብሄረሰቦች ተወላጆች መካከል በተቀሰቀሰ ግጭት በርካታስ ስዎች ተገድለዋል።

12. በደቡብ በሚኖሩ የኮይራ ብሄረሰብ አባላትና በአዋሳኙ በኦሮሚያ ክልል የሚኖሩ የጉጂ ብሄረሰብ አባላት መካከል በተከሰተ ግጭት የሰው ሕይወት ጠፍቷል።የንብረት ዉድመት ደርሷል።

ከኢሰመጉ ሪፖርት አለፍ ብለን፣ ኢሰመጉ ከዘረዘራችው ዘር ተኮር የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በተጨማሪም፣ ባለፉት ሁለት አመታት ብቻ ቀላል የማይባሉ በመቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ዜጎች የተፈናቀሉበት አሳዛኝ ክስተቶች ተፈጽመዋል። ላለፉት አንድ አመት በአገራችን እየሆነ ያለውን ብቻ እንኳን ብንምለከት ብሄረተኝነት ምን ያህል እንደ አገርና እንደ ሕዝብ ወደ ትልቅ ጥፋት እየወሰደን እንደሆነ መረዳት እንችላለን። ላለፉት አንድ አመት ብቻ ከተፈጸመ አሳዛኝ ክስተቶች የሚከተሊት ይገኙበታል፡

1. ሶማሌዎችና ኦሮሞዎች ለዘመናት በጋር በሚኖሩባቸው እንደ ሚኤሶ፣ ጉርሱም፣ ባቢሌና ሞያሌ ባሉ አካባቢዎች የኦሮሞ ነው የሶማሌ ነው በሚል ግጭቶች ብዙ ዜጎች ሞተዋል ተሰደዋል። ወደ ስድስት መቶ ሺህ የሚሆኑ ኦሮሞዎች ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ ሲሆን ቁጥራቸው ከአራት መቶ ሺህ በላይ ሶማሌዎችም ከኦሮሚያ ተፈናቅለውል። በሺሆች የሚቆጠሩ ተገድለዋል። በአወዳይ ከተማ ብቻ በአንድ ቀን ከአምሳ በላይ ሶማሌዎች ታርደዋል።

2. በኢሊባቡር “መጤና ናችሁ” በሚል ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ኦሮሞ ያልሆኑ ኢትዮጵያዉይን በዋናነት ከአማራው ማህበረሰብ በገጀራ ተጨፍጭፈዋል።ብዙዎች ተፈናቅለዋል።

3. በቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል በአማራ ማህበረሰብ አባላት ላይ በተቃጣው ጥቃት ብዙዎች በገጀራ፣ በቀስትና በእሳት አልቀዋል።ብዙዎች ተፈናቅለዋል።

4. በአርሲ ነገሌ በጉራጐዎችና በአማራዎች ንብረት ላይ ጥቃት ተፈጽሟል።

5. በመቀሌ ከተማ በመቀሌ ከነማና በባህር ድር ከነማ የእግር ኳስ ክለቦች መካከል ይደረግ በነረበው ጨዋታ ወቅት በተፈጠረው ግጭት በርካታ የባህር ዳር ከነማ ደጋፊዎችና ተጨዋቾች ድብደባ ተፍጽሞባቸዋል።

6. በነቀምቴ የትግራይ ተወላጆች በጠራራ ጸሃይ በድንጋይ ተወግረው ተገድለዋል።

7. በወልዲያ የመቀሌ ከነማ ከወልዲያ የእግር ኳ ቡድን ጋር ጋር ሊያደርግ በነበረው የእግር ኩስ ውድድር ምክንያት የተፈጠረው ግጭት ዘር ተኮር ሆኖ ዘጎች የተጎዱ ሲሆን የብዙ ወገኖችም ንብረት ጠፍቷል። የብዙ የትግራይ ተወላጆ ንብረት ተቃጥሏል።

8. በመቱ ዩኒቨርሲቲ የትግራይ ክልል ተወላጆች ዩኒቨርሲቲዎች እንዲለለቁ ተገደዋል። የአማራ ክልል ተወላጆች ደግሞ የተወሰኑቱ ዩኑቨርሲቲዉን ጥለው ወደ ወላጆቻቸው ሲመለሱ፣ የቀሩትን እየተማሩ ያሉ በፍርሃት ውስጥ ነው።

9. በአዲግራት ዩኒቨርሲቲ በተከሰተው ዘር ተኮር ግጭቶች ብዙዎች የተደበደቡ ሲሆን አንድ ተማሪ ከፎቅ ላይ ተወርዉሮ እንደተገደለ በስፋት ተዘግቧል።

10. በወለጋ ዩኒቨርሲቲ የትግራይ ተማሪዎች ከፎቅ ላይ ተወርወረዉ ተገድለዋል።

11. የኦነግ ታጣቂዎች ባስነሱት ግጭት በኦሮሞ ክልልና በቤኒሻንጉል ክልል ከማዝ ወረዳ ከጉሙዞች ጋር በተነሱ ግጭት ከመቶ አምሳ ሺህ በላይ አብዛኞቹ ኦሮሞዎች ተፈናቅለዋል።

12. በኦሮሞ ክልል ጉጂ ዞን የሚኖሩ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ጌዴዎኦች ተፈናቅለዋል።

13. የኦሮሞ ጽንፈኛ ቄሮዎች በቀሰቀሱት ሽብር ወደ ሰማኒያ ሺህ የሚጠጙ ዜጎች ፣ በዋናንተ ጋሞዎች በግፍና በጭካኔ ተፈናቅለዋ፤ ብዙዎች ተገድለዋል።

14. በምስራቅ ሸዋ ፈንታለ ወረዳ የአማራ ገበሬዎች በአክራሪ ኦሮሞው ተፈናቅለኣል። የተገደሉን ብዙ አሉ።

15. በአማራ ክልል ምእራብ ጎንደር ዞን፣ በርካታ የትግራይ ተወላጆች ለሕይወታቸው ስለሰጉ ወደ ሱዳን ተፈናቅለዋል።

16. ከአዋሳ ከተማ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ሲዳማ ያልሆኑ ዜጎች በተለይ ወላይታዎች ተገድለዋል፣ ተፈናቅለዋል

ይሄ ሁሉ የሚያመላክተው አገራችን ትልቅ አደጋ ላይ እንዳለች ነው። እንደ ሕዝብ ፣ እንደ አገር እንድንቀጥል ከተፈለገ ትግሬ፣ አማራ፣ ኦሮሞ የማንባባልበት፣ ማንኛውም ዜጋ በማንኛውም የአገሪቷ ክፍል የመኖር ዋስታናው የተረጋገጠበት አገር ሊኖረን ይገባል። ለዚህም ነው “ አሁን ያለው በዘር ላይ የተመሰረተው ፖለቲካና ፌደራል አወቃቀር መቀየር አለበት። ጎሳችንና ዘራችን ላይ ከማተኮር ስብእና ዚገነት ላይ ማተኮር መጀመር አለብን” የምንለው።

ይሄንን ትልቅ አደጋ ለመከላከል፣ የመንግስት ባለስልጣናት የችግሩን ዋና ምንጭ ወይ አልተረዱትም አሊያም ተረድተው መፍትሄ ለመፈለግ ድፍረት ያጡ ነው የሚመስሉት። አንዳንድ ባለስልጣናትማ እነዚህ ሁሉ ችግሮች የተፈጠሩት ከዲሞክራሲ እጦት የተነሳ ነው ነው ይላሉ። በአጼዎቹ ዘመን ይሁን በደርግ ጊዜ ፣ መቼም ዴሞክራሲ ነበር ብሎ የሚከራከር ይኖራል ብዬ አላስብም። በኢሕአዴግ ዘመን እንዳየነው የዘር ግጭቶች መፈናቅሎችን ስለማየታችን በነዚያ ዘመናት ስለመፈጸሙ የተጻፈ ነገር የለም። ያ ማለት መፈናቀሉ ከዲሞክራሲ እጦት ጋር የተገናኘ አለመሆኑን ነው።

መፈናቀሉ፣ የጎሳና፣ የዘዉግ ግጭቶች ዋና ምክንያትና ምንጭ፣ የጎሳና የዘዉግ፣ እኛና እናንተ የሚለው ከፋፋይና ዘረኛ ፖለቲካ፣ ሕግ መንግስትና ስራዓት ነው። ያንን ማስተካከል ካልተቻለ፣ ማስታገሻ በመስጠት ብቻ ይሄንን በሽታ ማዳን አይቻልም።
አሁን ያለው ፌደራል አወቃቀር አንድን አካባቢ ለአንድ ብሄረሰብ፣ ሌላውን አካባቢ ለሌላው ብሄረሰብ ስለሰጠ ከአንድ በላይ ብሄረሰቦች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ሰላም ሊያሰፍን አልቻለም። ያ ብቻ አይደለም፣ አንድ ዜጋ ለርሱ ብሄረሰብ ከተመደበው አካባቢ ውጭ የመኖር ዋስትና የለውም። አገሩ እንዳልሆነ ነው የሚቆጠረው። የአማራ ክልል ካለ አማራ ያልሆነው በአማራ ክልል ከአማራ እኩል ሊታይ አይችልም። ኦሮሞ ክልል እያለ ኦሮሞ ያልሆነው ከኦሮሞ እክሉ ሊታይ አይቻልም። የጉራጌ ዞን እስካለ ጉራጌ ያልሆነ በጉራጌ ዞን እኩል ሊታይ አይችልም። አሁን ያለው አከላለል ቀጥሎ ዜጎች እኩል ይታያሉ ማለት አሳ በመሬት ላይ ይሄዳል ማለት ነው።

በመሆኑም ፌዴራል አወቃቀሩ ቋንቋንም ከግምት ማስገባት ያለበት ቢሆንም፣ ከቋንቋ በተጨማሪም፣ ኢኮኖሚን፣ የአስተዳደር አመችነትን ፣ ጂዮግራፊን፣ የሕዝብ ፍላጎትን እና የአካባቢው ሕብረ ብሄራዊነት መጠኑንም ከግማት ባስገባ መልኩ መዋቀር አለበት።

(ግርማ ካሳ)

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *