በደቡብ ምዕራብ ታንዛኒያ ውስጥ ስድስት ህጻናት ተገድለው ጆሯቸውና ጥርሳቸው ከአካላቸው ላይ ተወስዶ መገኘቱን ባለስልጣናት ተናገሩ።

የተገደሉት ህጻናት ዕድሜያቸው በሁለትና ዘጠኝ ዓመት ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ከአካላቸው ላይ እጅና እግራቸው ተቆርጦ እንደተወሰደም ተነግሯል።

“ይህ ድርጊት በሙሉ ከባዕድ አምልኮት ጋር የተያያዘና በጥንቆላ አንዳች ድጋፍ ለማግኘት የተደረገ መሆኑን በርካቶች ያምናሉ” ሲሉ የአካባቢው አስተዳዳሪ ሩት ምሳፊሪ ተናግረዋል።

ፖሊስ ከወንጀሉ ጋር በተያያዘ የአንድ ቤተሰብ አባል የሆኑና ከተገደሉት መካከል ለሦስቱ ህጻናት የቅርብ ዝምድና አለው የተባለን አንድ ተጠርጣሪን በቁጥጥር ስር አውሏል።

ባለፉት ሦስት ወራት ውስጥ ጆምቤ በተባለው አካባቢ አስር ልጆች መጥፋታቸው የተነገረ ሲሆን ከመካከላቸውም አራቱ በህይወት ተገኝተዋል።

የጠፉት ህጻናት ወላጆቻቸው በምሽት ምግብ ለመሸጥ ወደ ገበያ በሄዱበት ጊዜ ከቤታቸው እንደተወሰዱም ተነግሯል።

ዘጋቢዎች እንደሚሉት በአካባቢው የሚገኙ ጠንቋዮች የሰው ልጅ የአካል ክፍሎች ሃብትና መልካም ዕድልን የሚያስገኝ ለየት ያለ ኃይል እንዳላቸው እንደሚናገሩ ገልጸዋል።

ይህንን ተከትሎም የአካባቢው አስተዳዳሪ ለቢቢሲ እንደተናገሩት “ወላጆችና አሳዳጊዎች ነገሮችን በንቃት እንዲከታተሉና ለልጆቻቸውም በዙሪያቸው ካሉ እንዲህ አይነት ወንጀል ፈጻሚዎች እራሳቸውን እንዴት እንደሚጠብቁ ማስተማር አለባቸው” ሲሉ መክረዋል።

BBC Amharic

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *