አቶ በረከት ስምኦን እና አቶ ዳደሰ ካሳ ለ2ኛ ጊዜ ፍርድ ቤት ቀርበው የአማራ ክልል ጸረ ሙስና ኮሚሽን ምርመራዬን አልጨረስኩም በማለቱ ፍርድ ቤቱ 14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል፡፡

የአማራ ክልል የስነ-ምግባርና ፀረሙስና ኮሚሽን በተከሳሹቹ ላይ አገኘዋቸው ያላቸውን የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን ለፍርድ ቤቱ አሰምቷል፡፡

ኮሚሽኑ በተከሳሾቹ ላይ ማስረጃ አሰባሰቢያለው ቢልም አሁን ላይ ምርመራዬን ባለማጠናቀቄ ተጨማሪ የ14 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ይሰጠኝ በማለት ፍርድ ቤቱን ጠይቆ ተፈቅዶለታል፡፡

የኮሚሽኑ መርማሪ ካቀረባቸው የሰው እና የሰነድ ማስረጃ ውስጥ የዳሸን ብራ ፋብሪካ በሽያጭ ‹‹ሎየት›› ለተባለ የብሪታኒያ ኩባንያ ሲተላለፍ መረጃዎቹ በአንድ ቦታ ተደራጅተው መቀመጥ ሲገባቸው ተከሳሾቹ የወንጀሉ አፈፃፀሙ እንዳይታወቅና መረጃው እንዳይገኝ አድርገዋል ብሏል፡፡

የዳሸን ቢራ ፋብሪካ ከሽያጩ ጀምሮ የኦዲት ስራው ያልተጠናቀቀ በመሆኑ አሁንም ተጨማሪ ስራ ያስፈልገኛ በሚል መርማሪው ተጨማሪ ቀጠሮ ይሰጠኝ ብሎ ጠይቋል፡፡

ተከሳሾቹ ሲመሩት በነበረው የጥረት ኮርፖሬት የተሟላ መረጃ ባለማግኘቱ የምርመራው ስራ ውስብስብ እንዳደረገበት ገልጿል፡፡
ከጉዳዮ ጋር በተያያዘ የሚያስረዱ ሰዎች በቋሚነትና በህክምና ውጪ ሀገር ያሉ እና ተቋማቸውን የለቀቁ በመኖራቸው አድራሻቸውን የማፈላለግ ስራ ይቀረኛ ብሏል መርማሪው፡፡

ሲዊዘርላንድ በሚገኝ በርክሌይ ባንክ ውስጥ 90 ሚሊዮን ዶላር በግለሰብ ስም እንደተቀመጠ የገለፀው መርማሪው የወንጀል ምርመራውን የበለጠ ውስብስብ ስለሚያደርገው በትኛው ግለሰቡ ስም ገንዘብ እንደተቀመጠ አላስረዳም፡፡

ተከሳሾቹ በበኩላቸው የተፈቀደውን የ14 ቀን ጊዜ ቀጠሮና የቀረበባቸውን ክሶችን በመቃወም መቃወሚያቸውን አሰምተዋል፡፡

በክልሉ ውስጥ ምቹ ሁኔታ የሌለ በመሆኑ ለእኛ የሚሆን ጠበቆችን ማግኘት ባለመቻላችን ኮሚሽኑ ያቀረበው የጊዜ ቀጠሮ ተገቢነት የለውም ብለዋል ተከሳሾቹ፡፡

ኮሚሽኑ ለተጠረጠርንበት ወንጀል ለመታሰር የሚያበቁ ምክንያቶችን በግልጽ አላቀረበልንም፤ በየትኛው የህግ አንቀጽ እንደተከሰስን ክሱ አያሳይም ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ጥረት የሚተዳደረው በፌዴራል መንግስት ተመዝግቦ በመሆኑ የክልሉ የስነምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን እኛ ለመክሰስ ህጋዊ መሰረት የለውም፤ ክሱ ሊታይ የሚገባው በፌዴራል ዐ/ህግ ሊሆን ይገባል በሚል ተከሳሾቹ ተከራክረዋል፡፡

የኮሚሽኑ መርማሪ በበኩሉ እኛ ክስ አልመሰረትንም ግን የህዝብ ሀብት ላይ ወንጀል በመፈፀሙ ምርመራ የማድረግ መብት አለን በሚል ተናግሯል፡፡

የግራ ቀኙን ሀሳብ የመረመረው ፍርድ ቤቱ መርማሪው በ14 ቀናት ውስጥ ቀረኝ የሚለውን መረጃ እንዲያጠናቅቅ የጊዜ ቀጠሮውን ፈቅዷል፡፡

ተከሳሾቹ ቤተሰብ ለመጠየቅ ተቸግረናል ለማንበብና ለማፃፍ ኢንተርኔትና ኮምፒውተር በሚል ለችሎቱ ያቀረቡ ሲሆን ፍርድ ቤቱ በበኩሉ ጥያቄው በጽሁፍ እንዲቀርብለት አዟል፡፡

በስመኘው ይርዳው (ከባህርዳር)/EBC

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *