አዲስ አበባ፣ የአፍሪካ መዲና፣ የሁላችንም የኢትዮጵያዊያን-የህብረ ብሄር ኢትዮጵያዊያን፣ የኦሮሞ፣ የአማራ፣ የጉራጌው፣ የጋምቤላው ወዘተ… የጋራ የሁላችንም የሆነች– ርእሰ ከተማችንን አዲስ አበባን የአንድ ብሄር ብቸኛ ርእስት ለማድረግ አሁኑም የሚሯሯጡ ግልሰቦችና ሀይሎች የሚቀሰቅሱት ሰደድ እሳት ሀገርና ራሳቸውንም ሊያቃጥል የሚችል መሆኑን የተገነዘቡ አይመስልም፣

ነገን በሩቁ ማየት የማይችሉ ፣ ከረጅሙ የሀገር ሰላም፣ መረጋጋት፣ የሰከነ ዴሞክራሲያዊ ስራአት፣ የህዝብ አብሮነት ይልቅ እለታዊ የፓለቲካ ቁማርና ትርፍ ያሰከራቸው፡ በጎ ራእይም ሁነ እንወክለዋልን ለሚሉት ብሂር እንኳን ሃላፊነት የማይሰማቸው ግልሰቦች እኩይ ድርጊት ህዝብን በመከፋፈል፣ ስጋት እንዲስፋፋ በማድረግ፣ ስላምና መረጋጋት በኢትዮጵያችን እንዳይነግስ ልዩ ተልእኮ ይዘው የሚንቀሳቀሱ ይመስላል።

በጣም የሚያሳዝነው ይህ አካሄዳቸው ሰላምና ልማት ለናፈቀው የኦሮሞ ህዝብም ሆነ ለመላው ኢትዮጵያ ህዝብ ምንም ሊፈይድ የሚችል አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን ለሌላ ዙር ሀገራዊ ቀውስና ክዚያም በላይ ኪሳራ ሊያድርስ እንደሚችል መንግስትም ሆነ ሃላፊነት የሚሰማቸው ወገኖች ሁሉ በቀላሉ ማየት የማይገባቸው እጅግ አሳሳቢ ጉዳይ ነው።

በዚህ አዲስ አባባ የማን ናት በሚለው በመስከረም ወር የጻፍኩት በድጋሚ አቅርቢአልሁ።

አዲስ አበባ የአዲስ አበባውያን ናት። በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ከሁለት ብሄሮች ወይንም ከዚያ በላይ የተወለዱ የአዲስ አበባ ነዋሪ ኢትዮጵያዊያን የአያት ቅደመ አያቶቻቸው እትብት ጭምር የተቀበረባት ዋና ከተማ ናት። አዲስ አበባ የኦሮሞ፣ የአማራ፡ የጉራጌ፣ የደቡብ ብሄሮች ተወላጅ የሆኑ፣ ወዘተ፣ ኢትዮጵያዊያንም የሚኖሩባት፣ ሁሉም እኩል መብትና ባለቤትነት አላቸው ስንል፣ አይ አይደለም የዚህ ወይንም የዚያ ብሄር የተለየ ባለቤትነት በአዲስ አበባ ላይ አለው የሚሉ የትኛው ዘመን ላይ እንደሚኖሩ ማጠራጠሩ ብቻ ሳይሆን ይህን በብዙ መስዋእትነት የመጣን ለውጥ ከማገዝ ይልቅ እንዲህ አይነት ህዝብን ከስጋት ላይ የሚጥል፣ በማህበረሰቦች መካከል ከአብሮነት ይልቅ መነጣጠልን፡ ከመቀራረብ ይልቅ ጥርጣሬና ቅራኔን የሚያፋፍም ፣ የጋራ መግለጫ ለማውጣት ለምን አስፈልገ የሚል ጥያቄ መጠየቅ የግድ ይላል።

ወቅቱ የሚጠይቀው ስላምን፣ እርቅን፣ ሀገራዊ መግባባትን፣ ብሎም የዶ/ር አብይ መንግስት የጀመረውን ለውጥ ሂደት ማገዝ መሆን ሲገባው፣ እነዚህ ድርጅቶች ይህን መሰል ሰሞኑን የተፈጠረውን አሳዛኝ ሁኔታ የሚያባብስ አቅጣጫ ለመከተል መምረጣቸው በጣም ያሳዝናል። እጅግ አስገራሚም ነው።

የእኛ አቋም ግልጽ ይመስለኛል። በሁሉም አካባቢ ፣ በሁሉም የኢትዮጵያ ማእዘኖች የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዜጋ እኩል መብትና ጥቅም እንደ ዜጋ ይኑረው ስንል ኦሮሞ ኢትዮጵያውያን፣ የደቡብ ኢትዮጵያውያን፣ የሶማሌ ኢትዮጵያዊያን፣ የአማራ ኢትዮጵያውያን፣ ከሁለት ወይንም ከዚያ በላይ የተወለዱ ኢትዮጵያውያን ፣ ብሎም ሁሉም የኢትዮጵያ ዜጎች ሁሉ መብቶች ነጻነቶችና ጥቅም የተረጋገጠባት፣ የክርስቲያን የእስልምና እምነት ተከታዮች የእምነት ነጻነት የተከበረባት፣ አብዛሀነት የተከበረባት፣ የዚህች ምድር ልጆች ሁሉ እንደ ዜጋ እንደ ሰብአዊ ፍጡር፣ ኢትዮጵያዊ በጎንደርም ሆነ በደቡብ፣ በአዲስ አበባም ሆነ በወሎ ፣ በአዋሳም ሆነ፣ በድሬዳዋ እኩል የዜግነት መብቶችና ነጻነቶች የተረጋገጡበት፣ የተከበሩበት ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ማለታችን ነው። ህብረ ብሄራዊ ማንነት ያላቸው (ከሁለት ወይንም ከሁለት በላይ ብሄሮች በላይ ማንነት) ኢትዮጵያውያንም ሆነ ከአንድ ብሄር ወይ ከሌላው ብሄር የተወለዱ ዜጎች በየትኛው አካባቢ እኩል የዜግነት መብቶቻቸው ፣ ጥቅሞቻቸው መከበር፣ መጠበቅ አለበት እያልን ነው።

የብዙ ሚልዮኖች ቤትና ህብረ ብሄራዊ ማንነት ያላትን የሀገሪቱን መዲና አዲስ አበባን የአንድ ብሄር የተለየ ርስት አድርጎ የተለየ የባለቤትነት መብት መስጠት እጅግ ሃላፊነት የጎደለው ነው። ነገ ደግሞ ሌሎች በልዩ ልዩ አካባቢዎች ተንስተው የዛሬ 100 አመት ወይን 500 እመት ይህ የአንተ መሬት አልነበረም፣ “መጤ ነህ፣ ሰፋሪ ነህ” ወዘተ በሚል ህዝቦችን ወደ የማያባራ ትርምስ እንዲያመሩ በለፉት 27 አመታት በየጊዜው የፈነዳውን አሳዛኝና ዘግናኝ የማህበረሰቦች ግጭት የሚያባብስ አካሄድ እንጂ፣ እቺን አሳዛኝ ሀገርና ለመከራ የተፈጠረ ህዝብ በጋራ እንዲኖር፣ መብቱ፣ ነጻነቱና፣ ሰበአዊ ክብሩ የተሟላባት ለሁሉም እኩል ለሆነች ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ምስረታ ሂደት የሚረዳ ጤነኛ አስተሳስብ ሊሆን የሚችል አይደለም።

አሁንም የምንለው ከግል ጥቅም፣ ከትናንሽ ድርጅታዊ የፓለቲካ ትርፍ ስሌት ወጥተን ለሁሉም ዜጎችና ማህበረሰቦች አብሮነት፣ ለጋራ ሀገር ፣ ለጋራ የህዝቦች ጥቅም፣ ለሰላም፣ ለመረጋጋት፣ ልዩነቶች በሰለጠነ የዴሞክራሲያዊ ውይይት የምንፈታበት ለተረጋጋ የፓለቲካ ስርአት ምስርታ በጋራ ብንበረታ፣ ብሎም የለውጡ ሃይል የጀመረውን ሂደት ለማገዝ ብንረባረብ የተሻለ ነው በማለት ዳግም ምክር ለመለገስ እወዳለሁ። ይህ አካሄድ ለማንም የማይጠቅም፣ ማንም አትራፊ የማይሆንበት፣ ሁሉ ተያይዞ ወደ ሁለንተናዊ ኪሳራ፣ ብሎም የማያባራ ገሀነም ሊወስደን የሚችል የጥፋት ጎዳና ነው።

ስለዚህ አዲስ አበባ የኢትዮጵያውያን ሁሉ ናት። የአፍሪካም መዲና፣ ኢትዮጵያ የሁላችንም ናት፣ ማንም የበኩር ወይንም የእንጀራ ልጅ የለም።

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *