በኦሮሚያ ክልል ህዝቡና የፀጥታ አካላት ባደረጉት ቅንጅታዊ ከ1 ሺህ የሚበልጡ የኦነግ ሰራዊት አባላት ትጥቅ በመፍታት ወደ ስልጠና መግባታቸውን የክልሉ መንግስት አስታወቀ።

የኦሮሚያ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ አቶ አድማሱ ዳምጠው በዛሬው እለት በሰጡት መግለጫ፥ ባለፈው አንድ ወር በክልሉ በተሰራው ስራ የክልሉ ሰላም እና መረጋጋት መሻሻል ማሳየቱን ገልፀዋል።

አቶ አድማሱ ዳምጠው በመግለጫቸው፥ ሰላም እና መረጋጋት ርቋቸው በነበሩ የክልሉ አንድ አንድ አካባቢዎች የክልሉ ህዝብ እና የፀጥታ አካላት በትብብር በሰሩት ስራ ነው የክልሉ ሰላም እና ፀጥታ መሻሻል ያሳየው ብለዋል።

በተለያዩ አካባቢዎች ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ከ1 ሺህ በላይ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ሰራዊት አባላትም ትጥቅ በመፍታት ወደ ስልጠና መግባታቸውንም አቶ አድማሱ አስታውቀዋል።

በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች በነበሩ አለመረጋጋቶች ተቋርጠው የነበሩ የአገልግሎት መስጫ ተቋማትም ወደ መደበኛ አገልግሎታቸው እየተመለሱ መሆኑን ገልፀዋል።

በተለይም ትምህረት ተቋርጦባቸው የነበሩ አካባቢዎች አብዛኛው ወደ መደበኛ የመማር ማስተማሩ ስራ እየተመለሱ መሆኑንም ነው አቶ አድማሱ የገለፁት።

የተቃጠለውን የምትህርት ጊዜ ለማካካስም መምህራን እያሳዩት ላለው ቁርጠኝነት በክልሉ መንግስት ስም ምስጋና አቅርበዋል።

በቀጣይም የክልሉ መንግስት የክልሉን ሰላም እና ፀጥታ ለማስጠበቅ እንዲሁም መደበኛ የልማት ስራዎች በፍጥነት እንዲጠናቀቁ ከክልሉ መንግስት እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን እንደሚሰራም ገልፀዋል።

በኦሮሚያ ክልል የሀሳብ የበላይነት ብቻ አሸናፊ እንዲሆን ሁሉም የሚመለከተው አካል በትብብር እንዲሰራም አቶ አድማሱ ዳምጠው ጥሪ አቅርበዋል።

በምስክር ስናፍቅ

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *