የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለልማት ፕሮጀክቶች በብድር የሚያቀርበው የገንዘብ መጠን በዓመት 100 ቢሊዮን ብር መድረሱን አስታወቀ፡፡አጠቃላይ ካፒታሉም 481 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር የሆኑት አቶ በልሁ ታከለ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፣ በባንኩ ፕሮግራም መሰረት ቅድሚያ የገንዘብ አቅርቦት የሚመቻችላቸው የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሆነው በወጪ ንግድ፣ በአምራች ዘርፍና በግብርና የተሰማሩ ተቋማት ናቸው፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ፣ ወደ ውጭ የሚላኩ እቃዎችን በጥራትና በብዛት ማሳደግ ሀገሪቱ ከግብርና መር ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ ለምታደርገው ግስጋሴ ወሳኝ ነው፡፡ ትኩረት ተሰጥቶ በአምራች ተቋማት ላይ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ ከተቻለ፣ ከውጭ የሚገቡትን ምርቶች በሀገር ውስጥ መተካት ይቻላል፡፡ በመሆኑም በሁሉም መስክ ላሉ አምራቾች፣ ላኪዎችና አቅራቢዎች ትኩረት ተሰጥቶ ይሠራል፡፡

አቶ በልሁ ጨምረው እንዳስታወቁት፤ የባንኩ አጋር የሆኑና በጥሩ አፈፃፀም እውቅና ለተሰጣቸው ድርጅቶች በቅርቡ ለ105 ለሚሆኑ ድርጅቶች ሽልማት ሰጥቷል፡፡ እነዚህ ሽልማቱን ያገኙ ድርጅቶችም በወጪ ንግድና በገንዘብ አዘዋዋሪ ሥራ በመሰማራት በ2017/18 በጀት ዓመት ከ1 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ማስገኘት የቻሉ ናቸው፡፡

ባንኩ ካለፉት ስድስት ወር ጀምሮ በትልልቅ የገቢ ማሰባሰቢያ የገንዘብ ምንጮች ላይ እየተሳተፈ የገቢ ምንጩን እያሳደገ ይገኛል፡፡ በዚህም መሰረት ያልተጣራ ከ9 ቢሊዮን ብር በላይ ትርፍ ማግኘት ችሏል፡፡ ባንኩ ከ29 ቢሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ መሰብሰብ የቻለ ሲሆን፣ አጠቃላይ ካፒታሉንም 481 ቢሊዮን ብር ማድረሱንም ጠቁመዋል፡፡

የውጭ ምንዛሪ አንዱ የገቢ ማሰባሰቢያ አካልና ለባንኩ የተሰጠው የሥራ ኃላፊነት ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ባንኩ 4ነጥብ3 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ከተለያዩ የውጭ ምንዛሪ ምንጮችና ከውጭ ትርፍ ማግኘቱን ተናግረዋል፡፡ በተደራሽነት ዙሪያ ባንኩ 55 ቅርንጫፎችን ከላይ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ መክፈት የቻለ ሲሆን፣ በመላው ሀገሪቱ ያለውን አጠቃላይ ቅርንጫፉንም 1ሺ346 ማድረሱን አስታውቋል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የህዝቡን ብዛትና የአሰፋፈር ሁኔታን ከግምት በማስገባት ብዙ የቁጠባ አማራጮችን እያቀረበ እንደሚገኝ፣ እንዲሁም ኤሌክትሮኒክስ የገንዘብ መገበያያ ዘዴዎችንም እንደ ተጨማሪ አማራጭ በማቅረብ ላይ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

አዲስ ዘመን የካቲት 9 ቀን 2011

ሞገስ ፀጋዬ

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *