በመርሐ ፅድቅ መኮንን ዓባይነህ

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩን እንወዳቸዋለን፣ እንሳሳላቸዋለንም፡፡ እንዲያውም አንዳንዶቻችን በሰላም ውሎ ማደራቸው ሳይቀር አብዝቶ ያስጨንቀናል፡፡ በዚያ ሰሞን ከጎንደር ከተማ ነዋሪዎች መካከል አንዱ ወዳጄ የሞቀ ወሬያችንን ይበልጥ ለማጋጋል የፈለገ በሚመስል ቅላጼ ያጫወተኝን ፈጽሞ አልረሳውም፡፡ከዕለታት በአንደኛው ቀን አመሻሹ ላይ ጓደኛቸው ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መኖሪያ ቤት ስልክ ደውሎ  ስልኩን ያነሳችለትን እመቤት ‘እባክሽን እህቴ ዓብይ ገብቶ ይሆን እንዴ?’ ብሎ ጠየቃት አሉ፡፡ ተጠያቂዋ ወይዘሮም ‘እንግዶች አሉበት መሰለኝ እስካሁን ገና አልገባም’ ማለት፡፡ ይኼንን ጊዜ ምን ቢላት ይሻላል መሰላችሁ? ‘ኧረ በጊዜ ግባ በይውማ እታለም’፣ ‘ባይገርምሽ’ ‘እሱ ከሚያመሽ ሚስቴ ውጭ አድራ ጠዋት ብትመለስ ይሻለኛል’ አላት ይባላል፡፡

አስቡት እንግዲህ፣ ይኼንን አለ የተባለው ጀግና “በእናት አገርና በሚስት የለም ዋዛ” እያለ ሌት ተቀን አንጎራጉሮ የማይጠግበው የጎንደር ሰው መሆኑ ነው፡፡ ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ያን ያህል የምንወዳቸውና የምናንቆለጳጵሳቸው የአገሪቱ ወጣት ጠቅላይ ሚኒስትር ስለሆኑ አይደለም፡፡ አቶ መለስም እኮ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ሲሰየሙ ከእሳቸው ባነሰ የዕድሜ ደረጃ ላይ እንደነበሩ አንዘነጋውም፡፡ ቁም ነገሩ እዚያ ላይ አይደለም፣ ሊሆንም ከቶ አይችልም፡፡ ዓብይ ከቀደምት አቻዎቻቸው በብዙ መንገድ ይለያሉ፣ ቅን ሐሳባቸው ይገዛናል፣ ቀጥተኛነታቸው ይማርከናል፣ አንደበተ ርቱዕነታቸው ይቆጣጠረናል፣ ለተጨነቁና ለተጎዱ ግፉአን ወገኖች የሚያሳዩት ርህራሔ ስለጥልቅ ሰብዕናቸው አንዳች ሚስጥር ይነግረናል፣ ትህትናቸው ፈጽሞ ወደር አይገኝለትም፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ አገራቸውን ኢትዮጵያን ከልባቸው የሚወዱ መሪ መሆናቸው በእጅጉ ያስቀናናል፡፡

‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ በወንጀል መጠርጠሩ በይፋ ታውጆ ያልታሰረ ሰው የሌለ ሲሆን የራሱን የመንቀሳቀስ ነፃነት በራሱ የገደበውም ቢሆን መንግሥት ተከታትሎ አይሰረው እንጂ ራሱን በራሱ አስሯል፡፡ ልዩነቱ መንግሥት በቁጥጥር ሥር አውሎ የሚቀልበው ወይም ራሱን በራሱ አስሮ የሚቀልብ መሆኑ ላይ ነው፤›› ባሉ ጊዜ ስለእሳቸው በትንሹም ቢሆን ተሸማቅቄ እንደነበር አልደብቅም፡፡ በእኔ አስተያየት ይህ የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ አነጋገር ከመስመር የወጣና በትምህርተ ስላቅ ውስጥ መቀመጥ ያለበት መስሎ ይሰማኛል፡፡ ዓይነተኛ መሳለቂያ የሆነው አካልም ሌላ ሳይሆን፣ ራሱ ምክር ቤቱ ነው ብዬ እስከ መተቸት እደፍራለሁ፡፡

በዚህ የተነሳ አብዛኞቻችን ልባዊ ድጋፋችንን ሳንቆጥብ ቸረናቸዋል፡፡ የኢሕአዴግ መሪ መሆናቸውን እንኳ ከቁብ ሳንቆጥረው አክብረናቸዋል፣ ጥላ ቢስእንዳያያቸው እንደየ እምነታችን ፀልየንላቸዋል፡፡ እንዲያም ሆኖ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መልዓክ ሳይሆኑ ሰው ናቸው፡፡ አልፎ አልፎ ሲሳሳቱ ወይም ሲደነቃቀፉ መመልከታችን አልቀረም፡፡ ያን ጊዜ ደግሞ የምንወዳቸውን ያህል ሳንሸማቀቅ ፈጥነን እንድናርማቸውና እንድናቃናቸው መፍቀድ ይኖርባቸዋል፡፡ ይልቁንም ፈጣሪ አብዝቶ የሚገስጻቸው የሚወዳቸውን ወገኖች ነውና እኛም ይህንኑ ወርቃማ መርህ በብርቅየው መሪያችን ላይ ተፈጻሚ ለማድረግ ብንደፋፈር የሚደንቅ አይሆንም፡፡

በአገራችን ውስጥ ከፍተኛውን የአስፈጻሚነትና የአስተዳደራዊ የመንግሥት ሥልጣን ከተረከቡ አንድ ድፍን ዓመት እንኳ ያልሞላቸው ጠቅላይ ሚኒስትራችን፣ በተፈጥሮ ብሩህ አዕምሮና ስሉጥ አንደበት የተሰጣቸውን ያህል በተለያዩ ጊዜያት ሐዲድ ሲስቱ ዓይተናቸውና ታዝበናቸው እናውቃለን፡፡ ይሁን እንጂ ተስፋ በሰነቁ ንግግሮቻቸው አከታትለው በወሰዷቸው መልካም የማሻሻያ ዕርምጃዎች ስለተሸፈኑ፣ ብዙዎቹን እዚህ ላይ አጉልቶ ማንሳቱ ሰውየውን ያላግባብ ማሳቀቅና ኢሞራላዊ ይሆናል፡፡

በቅርቡ ማለትም ጥር 24 ቀን 2011 ዓ.ም. በሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ልዩ ስብሰባ ላይ ተገኝተው የምክር ቤት አባላቱ ካነሱላቸው አያሌ ጥያቄዎች መካከል ለአንዳንዶቹ የሰጡት የግብር ይውጣ ምላሽ ግን ደረጃውን ያልጠበቀ ብቻ ሳይሆን፣ ለኃላፊነታቸው የማይመጥንና ተጠሪ ለሆኑለት አካልም ቢሆን የሚገባውን ክብር የነፈገ ነበር እላለሁ፡፡ በሥልጣን ላይ በቆዩባቸው ጥቂት ወራት ለሕግ ልዕልና ጥብቅና በመቆም ድምፃቸውን በእየ አደባባዩና ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ከፍ አድርገው ሲያሰሙና ቃላቸውን በገቢር ለማዋል በርትተው ሲጥሩ እንደቆዩ አብዝተን የምንመሰክርላቸው ምርጥ መሪ፣ በከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀል በሚገባ ተጠርጥረው ሳለ በአገር ውስጥ የራሳቸውን ምሽግ ቆፍረው የፍርድ ቤት መያዣ ወጥቶባቸው እንኳ ሊያዙና ሕግ ፊት ሊቀርቡ ስላልቻሉ ግለሰቦች ምክር ቤቱ ላቀረበላቸው ጥያቄ የሰጡት መልስ አይሉት ማብራሪያ በጣም አስቂኝ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ በወንጀል መጠርጠሩ በይፋ ታውጆ ያልታሰረ ሰው የሌለ ሲሆን የራሱን የመንቀሳቀስ ነፃነት በራሱ የገደበውም ቢሆን መንግሥት ተከታትሎ አይሰረው እንጂ ራሱን በራሱ አስሯል፡፡ ልዩነቱ መንግሥት በቁጥጥር ሥር አውሎ የሚቀልበው ወይም ራሱን በራሱ አስሮ የሚቀልብ መሆኑ ላይ ነው፤›› ባሉ ጊዜ ስለእሳቸው በትንሹም ቢሆን ተሸማቅቄ እንደነበር አልደብቅም፡፡ በእኔ አስተያየት ይህ የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ አነጋገር ከመስመር የወጣና በትምህርተ ስላቅ ውስጥ መቀመጥ ያለበት መስሎ ይሰማኛል፡፡ ዓይነተኛ መሳለቂያ የሆነው አካልም ሌላ ሳይሆን፣ ራሱ ምክር ቤቱ ነው ብዬ እስከ መተቸት እደፍራለሁ፡፡

እዚህ ላይ በኃይለኛው ማንሳት ያለብኝ ብርቱ ጉዳይ አለ፡፡ በሕግ መሠረት የፍርድ ቤት የእስር ማዘዣ እንደወጣበት እያወቀ ራሱን ደብቆ የተቀመጠ ይቅርና መፈለጉን አውቆ፣ በራሱ ፈቃድ እጁን ለሕግ አስከባሪ የሰጠ ተጠርጣሪ እንኳ ራሱን ያሰረ ነው ተብሎ አይሟረትበትም፡፡ የወንጀል ፍትሕ አስተዳደርና አፈጻጸሙን በዚህ ደረጃ አቃሎ ማየቱ በፖለቲካ ረገድም ቢሆን አትራፊ አይደለም፡፡ የሕግ ተጠያቂነትን እስከዚያ ድረስ መስተሃቀሩ የፖለቲካ ሀሁን እንዳለመቁጠር ሊወሰድም ይችላል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይኼንን በተናገሩ ጊዜ የተከበሩት እንደራሴዎቻችን እንደለመዱት የሚያዝናና ሳቅ ሲስቁላቸው አስተውለናል፡፡ በሁኔታው አንገታችንን የደፋን አንዳንድ ወገኖችም አንታጣም፡፡ በእርግጥ ያ ሳቅ የሚያስተላልፈው ጠንካራ መልዕክት ቢኖር ምናልባት ምክር ቤቱ ሥራውን የምር አድርጎ አለመሥራቱን ሊሆን ይችላል፡፡ በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ ጦር በሰላም ማስከበር ስም ሶማሊያ ውስጥ ከቀድሞው እስላማዊ ፍርድ ቤቶችም ሆነ ከአልሻባብ ጋር ሲዋጋ ምን ያህል የሕይወት መስዋዕትነት እንደተከፈለ ይገልጹላቸው ዘንድ፣ ቀደምት የምክር ቤቱ አባላት ሟቹን ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊን ጠይቀዋቸው ነበር፡፡ ያኔ አቶ መለስ የሰጡት መልስ ግድ የለሽነት የተጠናወተውና ንቀት የታከለበት እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ‹‹ሠራዊታችን ለጦርነት እንጂ ሠርግ ተጠርቶ አልነበረም የሄደው፣ ምን እንድነግራችሁ ትጠብቃላችሁ? እንዲያውም እንዲህ ያለውን ጥያቄ የመመለስ ግዴታ ያለብኝ አይመስለኝም፤›› የሚል ሲሆን፣ ፓርላማው ታዲያ ያኔም እንደ ዛሬው በሳቅ ነበር የፈረሰው፡፡ ከዚህ አልፎ በሰጡት ምላሽ በመበሳጨት ቆፍጣናውን ጠቅላይ ሚኒስትር ለምንና እንዴት ብሎ ለማፋጠጥ ይቅርና በመጠኑ እንኳ ለመገዳደር የሞከረ እንደራሴ ፈጽሞ አልነበረም፡፡

እንደ እውነቱ ከሆነ የምክር ቤቱን የኋላ ታሪክ በትንሹም ቢሆን በማስታወስ ከአሁኑ ጋር በመጠኑ ያለውን አስገራሚ ግጥምጥሞሽ ለማሳየት ብዬ እንጂ፣ የሁለቱ ጠቅላይ ሚኒስትሮች አቀራረብም ሆነ የንግግር ድምፀት መመሳሰል ይቅርና ጨርሶ የሚገናኝ ሆኖ አይደለም፡፡ በአንደበተ ርቱዕነታቸው እምብዛም ባይታሙም የአቶ መለስ ንግግር ክፉኛ ለጆሮ ይሻክር ነበር፡፡ መሬቱ ይቅለላቸውና አቶ መለስ ሰውን የማስቀየም፣ የማሳዘን ወይም የማጣጣል ልዩ ችሎታ ነበራቸው፡፡ ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ግን ከዚያ በተቃራኒው አዕምሯቸውን የመናገር ብቻ ሳይሆን የቅርብም ሆነ የሩቅ ታዳሚዎቻቸውን ትኩረት በቀላሉ የመሳብ፣ የማቆየትና አንዳንዴም አፍ አስከፍቶ የማማለል ተሰጥኦአቸው ዘይገርም የሚያሰኝ መሆኑን መካድ አይቻልም፡፡ እንዲህ ያለው ሰው ታዲያ ሆን ተብሎም ይሁን በቸልተኝነት አንድ ቀን ያልተጠበቀ የልሳን መንሸራተት ያጋጠመው እንደሆነ የሚደርስበት አበሳ ለግምት የሚያዳግት ይሆናል፡፡ ጉዳዩን በሚመለከት ቀልድ የታከለበት በሚመስል አቀራረብ የቀጠለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ፣ በከባድ ወንጀል ተጠርጣሪዎች ክትትልና አያያዝ ረገድ የክልል መንግሥታት የሚባሉትን ትብብርና የሥራ ድርሻ በሦስት ምድብ ከፍለውታል፡፡

‘ተፈላጊዎችን ይዘው የሰጡ’፣ ‘ገና በመከታተል ላይ ያሉ’ እና ‘ጠፍተውብን ነው እንጂ ይዘን እንሰጣችሁ ነበር’ ያሉ በማለት፡፡ በእያንዳንዱ ምድብ የሚገባውን ወይም የሚካተተውን ክልል ግልጽ ሳያደርጉልን ቀርተዋል፡፡ እጅግ የማከብራቸውን ሰው ከመቼውም ጊዜ በላይ ግልጽነት አጥቼባቸዋለሁ፡፡ ሕገ መንግሥቱ ግን በአንቀጽ 12 ንዑስ አንቀጽ 1 ድንጋጌ ሥር እንኳ ፓርላማን ለሚያህል የአገሪቱ ከፍተኛ የሥልጣን አካል ቀርቦ በይፋ የሚደመጥና ለመላው ዓለም በቴሌቪዥን የሚታይ የአንድ አገር መሪ ንግግር ቀርቶ፣ የትኛውም የመንግሥት ተግባር ግልጽና ተጠያቂነት ባለበት መንገድ መከናወን እንዳለበት በማያሻማ ቋንቋ እንደሚደነግግ ይስቱታል ተብሎ አይገመትም፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስተዋወቁት ምደባ ወይም ፍረጃ ያን ያህል ለጥቅስ የሚበቃ አይደለም፡፡ ቀድሞ ነገር ክልሎች የፌዴራሉ መንግሥት የእስር ማዘዣ ቆርጦ የሚያድናቸውን የወንጀል ተጠርጣሪዎች ክልሎች የመደበቅ ሃሞት ሊኖራቸው የቻለው፣ የፌዴራሉ መንግሥት ራሱ ዳተኝነት ስለታየበት መሆን አለበት፡፡“አያያዙን ዓይቶ ጭብጦውን ቀማው” ይላል ያገሬ ሰው፡፡ ይህ ካጋጠመ ደግሞ መፍትሔው ተባባሪና ዳተኛ ክልሎችን ስም ሳይጠሩ ማሞገስ ወይም መውቀስ ብቻ ለተከበረው የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት አጥጋቢ መልስ ሊሆን አይችልም፡፡ የኋላ ኋላ በየትኛውም የአገሪቱ ክልል ቢሆን ህቡዕ በሆነ መንገድ በየተዘጋጀላቸው ዋሻ የተደበቁትን ወይም የተወሸቁትን ቀንደኛ ተጠርጣሪዎች ከያሉበት ፈልጎና አድኖ በኃይል የመያዙና በሕግ አስከባሪው አማካይነት ሥልጣኑ ለሆነው ፍርድ ቤት የማቅረቡ ዓይነተኛ ኃላፊነት የማንም ሳይሆን፣ የራሱ የፌዴራሉ መንግሥት ፖሊስ እንደሆነ በውል መረዳት ይኖርባቸዋል፡፡ በሥራ ላይ ያለው የአገሪቱ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ እንዲህ ይነበባል፡፡ ቁጥር 25 የተከሰሰውን ወይም የተጠረጠረውን ሰው ስለመጥራት፣ አንድ ሰው የወንጀል ሥራ መፈጸሙን ለማመን መርማሪው ፖሊስ ምክንያት ሆኖ በሚገኝባቸው ሁኔታዎች ሁሉ የተባለው ሰው ቀርቦ እንዲጠየቅ ፖሊስ እንድትቀርብ በሚል በጽሑፍ ትዕዛዝ ሊጠራው ይችላል፡፡ ቁጥር 26 ስለመያዝ፣

  1. የተከሰሰው ወይም የተጠረጠረው ሰው ያልተያዘ እንደሆነ፣ ወንጀሉ በሕግ መሠረት የሚያሲዘው ሆኖ የተገኘ እንደሆነ ወይም በቁጥር 25 በተመለከተው መሠረት የተጠራው ሰው ያልቀረበ እንደሆነ እንዲያዝ መርማሪው ፖሊሰ አስፈላጊ የሆኑትን ጥንቃቄዎች ሁሉ ማድረግ አለበት፡፡
  1. ከፍርድ ቤት የመያዝ ትዕዛዝ ሳይሰጥ ሰውየውን ለመያዝ የማይቻል ሲሆን፣ መርማሪው ፖሊስ በቁጥር 53 በተመለከተው መሠረት የመያዝ ትዕዛዝ እንዲሰጠው ፍርድ ቤቱን ለመጠየቅ ይችላል፡፡

ይሁን እንጂ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን በመላ አገሪቱ ውስጥ ሕግና ሥርዓት መከበሩንና የሕግ የበላይነት በሁሉም ዜጎች ዘንድ ያለ ልዩነት የተረጋገጠ ሆኖ እንዲሠራበት የማድረጉ የመጨረሻ ኃላፊነት የእሳቸው መሆኑን እያወቁ፣ የበዛ ዳተኝነት ከማሳየት አልፈው ሁኔታውን ለመሸፋፈን መሞከራቸው የሚደገፍ አይደለም፡፡ እንዲያውም በዚህ ረገድ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያልተገባ ተለማማጭነትና አንዳንዴም ፍፁም ዓይን አፋርነት አሳይተዋል፡፡ በበኩሌ ይኼንን ከመስመር የወጣ የመለሳለስ አቋማቸውን የበሳል መሪ ትዕግሥትና ሆደ ሰፊነት ነው ብዬ እንደሳቸው ላለባብሰው አልፈልግም፡፡ በእኔ አስተያየት እስከዚያ ድረስ የዘለቀ ተለሳላሽነት ከእውነተኛ ሰላም ፈላጊነት ይልቅ ለተንበርካኪነት የቀረበ መሆኑን ልገልጽላቸው እወዳለሁ፡፡

በ“Common Law” የሕግ ሥርዓት አልፎ አልፎ እንደሚደረገው ከሶ ከማስቀጣት ይልቅ፣ የአስረጂነታቸውን ዋጋ ይበልጥ ለመጠቀም ሲፈለግ ከመካከላቸው በዝቅተኛ ወንጀሎች የተጠረጠሩ ወይም የተከሰሱ ሰዎችን ለይቶ የእያንዳንዱን ጉዳይ ግላዊ ፀባይ በሚገባ መዝኖ መለማመጥ፣ ወይም ከእነሱ ጋር መደራደር እንግዳ ነገር ላይሆን ይችል ይሆናል፡፡ እንደ ሰብዓዊ መብት ረገጣ ባለ ከባድ የወንጀል ድርጊት ተጠርጥረው የሚፈለጉ ወገኖችን ግን በዚህ ደረጃ ማባበሉ ለእነሱም ሆነ በማናህሎኝነት ላስጠለሏቸው አንዳንድ ክልሎች የልብ ልብ ከሚሰጣቸው በስተቀር፣ ማንንም ሊያስተምር ከቶ አይችልም፡፡

ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ከፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የእስር ማዘዣ ወጥቶበት በመፈለግ ላይ ያለውን የቀድሞ የብሔራዊ ደኅንነትና መረጃ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ይዞ ለሕግ ለማቅረብ ሥራው ዳገት እንደሆነባቸው ገልጸው፣ ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከተው ክልል ባለሥልጣናት ጋር በመነጋገር ላይ ቢሆኑም ያ ብቻ በቂ ስላልሆነ ይመስለኛል የምክር ቤቱን ድጋፍ መጠየቃቸውን ሁላችንም በአንክሮ የምናስታውሰው ነው፡፡ የጠየቁትን ድጋፍ ከተከበረው ምክር ቤት ማግኘት አለማግኘታቸው ግን እስካሁን ድረስ በግልጽ የታወቀ ነገር የለም፡፡ የሚታወቀው አንድ ጥሬ ሀቅ ብቻ ሲሆን፣ እርሱም በቁልፍ ተጠርጣሪነት የሚፈለገው ዋና ዳይሬክተር አሁንም እንደተሰወረና በጠቅላይ ሚኒስትራችን ዘይቤያዊ አነጋገር “ራሱን በራሱ አስሮ እንዳስቀመጠ” የመቀጠሉ እውነትነት ብቻ ነው፡፡

እነሆ ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንድ ጥያቄ አለኝ፡፡ ሰውየውን ያስጠለለው ወይም መጠጊያ የሆነው ክልል በየትኛው ምድብ ይካተት ይሆን? ታዳኞችን ይዘው ባስረከቡት? ተከታትለው ለመያዝ እየጣሩ ባሉት? ወይስ ጠፍተውብናል በማለት ማለቂያ የሌለው ሰበብ ይደረድራሉ በተባሉት?

Reporterከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በሕግ ሙያ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በ1981 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞው የሕግ ፋከልቲ ያገኙ ሲሆን፣ በሐምሌ ወር 2001 ዓ.ም. ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በተመድ የሰላም ዩኒቨርሲቲ ጣምራ ትብብር ይካሄድ ከነበረው የአፍሪካ ፕሮግራም በሰላምና በደኅንነት ጥናት የማስተርስ ዲግሪያቸውን ሠርተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በቢሮ ኃላፊ ማዕረግ የርዕሰ መስተዳድሩ ዋና የሕግ አማካሪ ሆነው በማገልገል ላይ ናቸው፡፡ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው clickmerha1@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *