መቀሌ የመሸጉት በኢትዮጵያ ምድር የሲኦልን በር በርግደው የከፈቱት የደደቢት ደቂቃን በዛሬው እለት ከ44 ዓመታት በፊት ለግድያና ቅሚያ ያቋቋሙትን የፋሽስት ድርጅታቸውን ልደት ሲያከብሩ ጫካ የወረድነው ፊውዳሊዝምን ለማጥፋት፤ ሰላም፣ ዲሞክራሲና በኢትዮጵያ «ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች» መካከል በእኩልነት ላይ የተመሠረተ አንድነት ለመፍጠር ነው ብለው ተናገሩ አሉ። ይገርማል! እንደዚህ አይነት ቅጥ ያጣ የነውረኞችን ድፍረት ስሰማ ሁልጊዜ ትዝ የሚለኝ አቶ ታዲዮስ ታንቱ በአንድ ወቅት ያቀረቡትና የማልረሳው ጽሑፋቸው ነው።

ከአራት ዓመታት በፊት ይመስለኛል የወላይታው ልጅ አቶ ታዲዮስ ታንቱ አብረን እንጽፍበት በነበረው አዲስ ታይምስ መጽሔት ላይ እንዲህ ብለው ጽፈው ነበር [የማስታውሰውን ስለሆነ የምጽፈው አቶ ታዲዮስ ቃል በቃል የጻፉትን ላልጠቅሰው እችላለሁ ]፤

«ምኒልክ ድሮ በሕይወት እያሉ ከነበሯቸው የውጭ ጠላቶች በላይ በአሁኑ ወቅት በርካታ የአገር ውስጥ ጠላቶች አሏቸው። አክሱም ሆቴል ውስጥ ለመቁጠር የሚታክቱ በርካታ ምኒልክን የሚሰድቡ መጽሐፍቶች ተመርቀዋል። የምኒልክን ታሪክ ለማንቋሸሽ ብዙ እየተሰራ ነው። ይህን ለመከላከልም ታሪካችንን ማወቅ አለብን። ታሪካችንን ሰው እንዳይሰርቀን መጠበቅ አለብን።

ታሪካችንን ለልጆቻችን ካላስተማርን ከ80ና 90 አመት በኋላ ታሪክ አልባው ሕወሓት አድዋን ያሸነፈው መለስ ዜናዊ ነው ብሎ የታሪክ ባለቤት ለመሆን እንደማይሞክር እርግጠኛ መሆን አይቻልም። ይኼው ዛሬ አባይን የደፈረው መለስ ዜናዊ እንደሆነ እየነገሩን ነው። የድሮዎቹ መሪዎች አባይን ማንም ሳያግደን እንገድባለን ብለው ጊዜ ሲጠብቁ ቆይተዋል። ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በአባይ ወንዝ ላይ አንድ አይደለም አስር የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ለመገንባት ጥናት አስጠንተው ነበር። ከተጠናው መካከል ፊንጫን ጨምሮ የተወሰኑትን ገንብተዋል። መንግሥቱ ኃይለማሪያምም አባይን ለመገደብ ትልቅ ጥረት አድርጓል። እንዲያውም የድሮዎቹ መሪዎች ገና ክራባት እንዳሰሩ የግብጽ ገዢዎችን እግር ስመው ‹‹እባክህን አባይን ልገድብ›› ብለው እንደመለስ ዜናዊ አልጠየቁም።»

አቶ ታዲዎስ ታንቱ እውነት አላቸው። የአቶ ታዲዮስ ንግርት ዛሬ በኛ ዘመን እየተተረጎመ እንደሆነ እያየነው ነው። ከታሪካችን ስለማንማር፣ ትዝታና ትውስታችን አጭሮ ስለሆነ ይኼው ዛሬ የደደቢት ነውረኞች ሕወሓት ብለው የሚጠሩትን የሌብነት፣ የግድያና የአፈና ማኅበር ያቋቋሙበትን 44ኛ ዓመት ሲያከብሩ በጭካኔ ክብረ ወሰን የተቀዳጁበትን ድርጅት ለሰላም፣ ለዲሞክራሲና በእኩልነት ላይ የተመሠረተ አንድነት ለመፍጠር እንደመሰረቱት እየነገሩን ነው።

ለነውረኞቹ የፈጠራ ትርክት መስካሪና መጽሐፍ እየደረቱ የታሪክ ካባ ለመጫን የሚዳዱ ምሑራን ነን የሚሉ እንደ ገብሩ ታረቀና ባሕሩ ዘውዴ አይነት የዘመን ተጋሪዎቻቸው የሆኑ የግራ ፖለቲከኞችም አይጠፉ።

ለመሆኑ ፋሽስት ወያኔ የታገለው ፊውዳሊዝምን ለማጥፋት ነው ወይንስ ፊውዳል ለመሆን? ፋሽስት ወያኔዎችና ያ ትውልድ ባጠቃላይ ፊውዳል በሚሏቸው አርበኞች ቤት ከያንዳንዳችን የተዘረፈ ሀብትና ንብረት፣ ከያንዳንዳችን የነጠቁን መሬት ካርታና ፕላን፣ እንዲሁም የግል እስር ቤት አይገኝም ነበር። የደርጉ ሃምሳ አለቃ ለገሰ አስፋው በሰጠው ምስክርነት የፊውዳል ምልክት ተደርገው በቀረቡት ፀሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሃብተወልድ ቤት ደርጎቹ ሲሄዱ ተሰቅሎ ካገኙት የስራ ሱፍና ክራባት፤ እንዲሁም ከተደረደሩ መጽሐፍቶቻቸው በስተቀር ያገኙት አንዳች ቤሳ ቤስቲ ነገር በተወረሰው ቤታቸው ውስጥ እንዳላገኙ ነግሮናል። አብዮተኛ ነን ባሉት በፋሽስት ወያኔዎች ቤትና ቤተ ዘመድ ጓዳ ቤሄዱ ግን ከያንዳንዳችን የተዘረፈውን ሀብትና ንብረት፣ ከያንዳንዳችን የነጠቁን መሬት ካርታና ፕላን፣ እንዲሁል የግል እስር ቤት ሳይቀር ታገኛላችሁ።

ከዚህ በተጨማሪ ፊውዳሊዝም የየራሳቸው ጦር ያላቸው፣ ያሻቸውን መሬት የሚነጥቁ፣ የግላቸውን ግብር የሚጥሉና ተጠያቂ የሚያደርግ የበላይ አካል ወይንም ሕግ የማያውቁ ጉልበተኞች ስርዓት ነው። ከዘመነ መሳፍንት በኋላ የራሳቸው ጦር ያላቸው፣ ያሻቸውን መሬት ባሻቸው ጊዜ ድሃ እያፈናቀሉ የጎሳቸው አባላት ለሆኑ ቱጃሮች መድለቢያ የሚሰጡ፣ የግላቸውን ግብር የሚጥሉና ተጠያቂ የሚያደርግ የበላይ አካልም ሆነ ሆነ ሕግ የሌለባቸው ፊውዳሎች ፋሽስት ወያኔዎች ብቻ ናቸው። በኢትዮጵያ ሰራዊት ስም ሲጠራ የኖረው ጦር የኢትዮጵያ ሳይሆን የሕወሓት የገበሬ ወታደር ነው። ይህ የሕወሓት ጦር የፊውዳል ወያኔዎች ቅልብ ነፍሰ ገዳይ እንጂ የአገር መከላከያ ሰራዊት አይደለም። በፓርቲ አባልነት ስም የግዴታ የጎሳ ግብር የሚጥሉ፣ ለሚገዙት ሕዝብ ቅንጣት ታህል ክብር የሌላቸውና ከሕግ ሁሉ የበላይ ሆነው የግፍ ክብረ ወሰን የሰበሩ ነውረኛ ፊውዳሎች አሁንም ፋሽስት ወያኔዎች ብቻ ናቸው።

ሆኖም ግን ጭነውብን የኖሩት የመከራ አገዛዝ ሸክም ክብደት መጠን ግፋቸው እንዳይሰማን ራሳቸው ዋነኞቹ ፊውዳሎች ሆነው ሳለ «ፊውዳሊዝምን ተዋግተን ነጻ ልናወጣችሁ ጫካ ገባን» እያሉ ዛሬ ባገራችን ፊውዳል እንደሌለ፣ እነሱም ፊውዳሎች እንዳልሆኑ አድርገው በፕሮፓጋንዳቸው ስላደነቆሩን ወያኔን ከሕግ በላይ የሆኑ የትግራይ ፊውዳሎች አገዛዝ አድርገን በባህሪው ልክ እንዳንገነዘበው አድርጎናል ። በዛሬዎቹ ግፈኞች ጨለማ ተደርጎ የሚቀርበው የነ አክሊሉ ሃብተወልድ ስርዓት ግን «በሕግ አምላክ» የሚለውን የሞራል ሥልጣኔ ባህል አድርጎ የተከለ፣ ሕዝብን የሚያከብር፣ ንጉሠ ነገሥቱ ሳይቀር ሕዝብን ለማክበር ሲሉ የዙፋን ችሎት ሙሉውን ቆመው የሚያስችሉ፣ ሕዝብንና ባለሞያን የሚያከብሩ የኢትዮጵያ አገልጋዮች ነበሩ።

ለምን ይዋሻል ወያኔም ሆነ የትግራይ ሕዝብ ከፈለ እየተባለ የሚደሰኮረው መስዕዋትነት የከፈሉት አማራን አጥፍተው «ቅኝ ገዢ» ከሚሏት ኢትዮጵያ ነጻ ወጥተው የታላቋ ትግራይን ሪፑብሊክ ለመመስረት ነው። ይህንን አላማ ትግል ሲጀምሩ በጻፉትና እስከ ኢሕአዴግ ምስረታ [1981ዓ.ም.] ድረስ ወያኔን ያስተዳድሩበት በነበረው ፍኖተ መርህ [manifesto] ላይ በግልጽ አስቀምጠውታል። የወያኔ የነፍስ አባት የሆነው ኢሳያስ አፈወርቂም በ1990 ዓ.ም. ባደረገው ንግግር ወያኔ ለዚህ አላማ እንደተፈጠረ ነግሮናል።

ወያኔ ከ1967—1981 ዓ.ም. በተዳደረበት የትግል ማኒፌስቶ ሲገለበጥ «የትግራይ ብሔራዊ ጭቆና እና በደል አስቆጥቶ ጭቆናውንና በደሉን ከሥሩ ለመንቀል የፖለቲካና የትጥቅ ትግል መጀመሩን» ያትትና የትግራይ ህዝብ የትጥቅ ትግል የመጀመረበትን አላማ ፤«የትግራይ ህዝብ ብሔራዊ ትግል ፀረ-የአማራ ብሔራዊ ጭቆና፣ ፀረ-ኢምፐርያሊዝም እንዲሁም ፀረ-ንኡስ ከበርቴያዊ ጠጋኝ ለውጥ ነው። ስለዚህ የአብዮታዊው ትግል ዓላማ ከባላባታዊ ሥርዓትና ከኢምፐርያሊዝም ነፃ የሆነ የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ሪፖብሊክ ማቋቋም ይሆናል።» ሲል ይነግረናል።

ስለዚህ ወያኔና የትግራይ ሕዝብ ከሕወሓት ጋር ጫካ ወርዶ

ፊውዳሊዝምን ለማጥፋት፤ ሰላም፣ ዲሞክራሲና በኢትዮጵያ «ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች» መካከል በእኩልነት ላይ የተመሠረተ አንድነት ለመፍጠር የከሰከሰከው አጥንትና ያፈሰሰው ጠብታ ደም የለም! ፋሽስት ወያኔም ሆነ ናዚ ኦነግ ጫካ የወረዱት ፊውዳሊዝምን ለማጥፋት ፤ ሰላም፣ ዲሞክራሲና እኩልነት ለማምጣት ሳይሆን በኢትዮጵያ ምድር ሰላምን፣ እኩልነትና ዲሞክራሲን ለመቅበር፤ በ1966 ዓ.ም. ከጠፋ 120 ዓመታት ያስቆጠረውን ፊውዳሊዝምን መልሰው ለመትከልና ራሳቸው ከብረ ወሰን የተቀዳጁ የእድሜ ዘመን ቱጃር ፊውዳሎች ሆነው ሲገዘግዙን ለመኖር ነበር። የሆነውም ይኼው ነው!

Achamyeleh Tamiru

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *