#ይገርመኃል_ሸዋ – via Isho Birhan –
ሚኒሊክ ልትጠላዉ ትችላለህ ፤ ደግሞም ልትወደዉ ትችላለህ ። ነገር ግን ሚኒሊክ ተራ ስብዕና እንዳልነበረ ለመረዳት አይከብድም ። ሚኒሊክ ዉስብስብ ሰዉ ነዉ ። ረቂቅ ነዉ ። ደግሞ አድማጭ ነዉ ።
ሚኒሊክ እንደ ገሞራ እሳት የሚፋጅ ነዉ ። ደግሞ እንደ ምንጭ ዉሃ ገር ነዉ ። ሚኒሊክ ሀገር መመስረት ፣ ግዛት ማስተዳደር ያዉቃል ። ተራ የታሪክ ሰዉ አይደለም ። ጉልህ ነዉ ።
የሚኒሊክን ነገር ለማጉላት ብዬ ከሌሎች ማወዳደር አልፈልግም ። ዳግሞም ማሳነስ ሊሆን ይችላል ።
ዉጫሌ ዉል የአድዋ ጦርነት መነሻ ነዉ ይላሉ ። ፈፅሞ ስህተት ነዉ ። የአደዋ ጦርነት መነሻ የበርሊን የቅኝ ገዢዎች ዉል ነዉ ። አዉሮፓ አፍሪካን ለመቀራመት የተስማማዉ በበርሊን ስምምነት ነዉ ። ያን ለማስፈፀም አዉሮፓዉያን በዉድም ፣ በዉልም ፣ በግድም አድርገዉታል ። በዉል ወደ ቅኝ ግዛት የገቡ ብዙ ናቸዉ ።
ጣሊያን ለሚኒሊክ የዉጫሌን ዉል ስታቀርብለት ፣ ሚኒሊክ ሳይገባዉ ቀርቶ ፣ ተሸዉዶ ፣ ወይ ገር ሆኖ ነዉ ማለት ደካማ የታሪክ ተማሪ ከመሆን የመጣ ነዉ ።
የዉጫሌ ዉል የተፈረመዉ አፄ ዮሓንስ በሞቱ በ 10 ቀናት ዉስጥ ነዉ ። የኣደዋ ጦርነት የተካሄደዉ አፄ ዮሓንስ ከሞቱ ከ 5 ዓመት በሗላ ነዉ ።
ሚኒሊክ የዉጫሌን ዉል በመፈረም የራሱን ጉልበት እስኪያጠናክር ግዜ መግዣ ነዉ ያደረገዉ ። ሚኒሊክ ከፍ ለማለት ዝቅ ማለትን ያዉቃል ።
እንደ ጣይቱ የሚፋጅ እሳት ፣ እንደ ልብ ወዳጁ ራስ መኮንን የረጋ ዉሃ ብቻ ቢሆን ፣ ሀገርም አይሰራም ፣ መንግስቱንም አያፀናም ነበር ።
ዉጫሌ በተፈረመበት ወቅት ሚኒሊክ ፣ ብዙ ጠላቶች ነበሩት ። ተጨማሪ ጠላት ጣሊያንን ማድረግ ስላልወደደ የፈረመዉ ነዉ ። የዉጫሌ ዉል ኖረ አልኖረ ፣ ጣሊያን ኢትዮጵያ ን መዉረሯ እንደማይቀር የሚታወቀዉማ ፣ የትግራይና ኤርትራ መኳንንት ጥሩ አድርጋ ስትክድ በማየት ነዉ ። ሚኒሊክ ግን ጦርነቱን ቢያንስ እሱ በመረጠ ግዜ እንዲሆን ማድረግ ችሏል ።
ሚኒሊክ ሁሉን ያዳምጣል ። በቅንም ይረዳል ። ዓላማዉን አይስትም ። ብልሃተኛ ነዉ ።
የአምባላጄ ጦርነት ፣ የመቀሌ ከበባ በአሸናፊነት ሲያልፍ ፣ በሚኒሊክ ዉሳኔ የሚቆጡ ብዙ ነበሩ ። ጣሊያኖችን ቢማርክም መልሶ እንደዉም ከመጋዣ (ፈረስና በቅሎ ) ጋር ላካቸዉ እያሉ የሚወቅሱት ነበሩ ። ሚኒሊክ ግን ጦርነት የሚገጥምበትን ቦታ እየመረጠ ነበር ። የሱ መኳንንት የሚያዉቁትን ሚኒሊክ ጠፍቶት አይደለም ።
ከባድ ስትራቴጂስት ስለነበረ ነዉ ።
ሚኒሊክ ያሰለፈዉን ሓይል ያዉቀዋል ። ከቴድሮስ እስከ ራስ ዉቤ ፣ ወርቂትና ተዋበች ፣ እስከ ዮሓንስና ጎበና የነበሩ ጦርነቶችን ፣ በአይኑ ያየና የሰለጠ ንጉስ ነዉ ። ጦርነት አዋቂ ነዉ ።
የቻይናዉ ታዋቂ የጦር ጀነራል – ሱን ሱ ” ሓይል እንዳለህ ስታዉቅ ፣ ደካማ ምሰል ” ያለዉን ሚኒሊክ ፈፅሞታል ።
ጣሊያን አደዋ ላይ የዘልዓለም ዉርደት እስክትከናነብ ፣ በዚህ የሚኒሊክ ብልጠት ተሸዉዳለች ። ሚኒሊክም ኣደዋ እስኪደርስ ድረስ የሚፋጅ ነብር መሆኑን ደብቆ ቆይቷል ።
አምስት ወር የተደረገ ጉዞ ፣ የስምንት ሰዓት አጭር ጦርነት የሆነዉ ፣ በዚህች አስደናቂ የሚኒሊክ ብልሃት ነዉ ።
ሚኒሊክ ያደረጋቸዉ ነገሮች ፣ የፈፀማቸዉ ታሪኮች ፣ የሰበሰባቸዉ ሸንጎዎች ፣ የወሰናቸዉ ዉሳኔዎች በእርግጠኝነት የሚሊክን ልህቀት የሚያገኑ ናቸዉ ።
ኣደዋ – በሚኒሊክ ተመርጦ ፣ በሚኒሊክ ታቅዶ ፣ በሚኒሊክ ተመርቶ ፣ የተፈፀመ ጀብዱ ነዉ ።
ለዚያም ነዉ ሚኒሊክ የሀገር መሪ ብቻ ሳይሆን ሀገር መስራች የሚባለዉ ።
ከዚህ መለስ ስላለዉ የታሪክ ፋይዳ ፣ ዉጤት ፣ ጥቅምና ጉዳት እንነጋገር እንጂ ሁነቱ ዳግም ላይመለስ ፣ በሚኒሊክ ተፈፅሟል ።
***
ይገርምሃል ሸዋ !!!