TAMRU HULISO – አዲስ አበባ ይህን ዓመት የጀመረችው በመራር ለቅሶ ነበር። የኦነግ አመራሮች አዲስ አበባ መድረሳቸውን ተከትሎ በተነሳ ግርግር አክራሪ የኦሮሞ ብሄርተኞች ቡራዩና አካባቢው ላይ በርካታ የድሃ ልጆችን በዘግናኝ ሁኔታ ገደሉ፤ሊሎች ወንጀሎችንም ፈጸሙ። ግድያው ለሶስት ተከታታይ ቀናት ሲካሄድ፤ተጎጂዎቹ ብቻ ሳይሆኑ የመሃል አዲስ አበባ ሰው “እረ በህግ አምላክ ድረሱላቸው “ እያለ ሲጮህ ነበር። ብዙዎቹም በወቅቱ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር የነበሩት ግለሰብ የእጅ ስልክ ላይ እየደወሉ ሲወተውቱ ነበር። የሆነው ሆነው የሶስት ቀኑ ግድያ በበቃኝ ከቆመ በኋላ፤ የክልሉ ፖሊስ አዛዥ ለምን ለተጎጂዎቹ በጊዜው አልደረሳችሁም ሲባሉ የሰጡት ምላሽ ብዙውን ህዝብ በሃዘንና አግራሞት እጁን አፉ ላይ ያስጫነ ነበር። የፖሊስ አዛዡ ተጎጂዎች የነበሩበት ቦታ ለመኪና ለማስገባት የማይመችና ለፖሊሶች አስቸጋሪ ነበር ሲሉ ገለጹ።
የከተማው ህዝብና ተጎጂዎች በዚህ ካለፈና ሰላም ከመጣ ይሁን በሚል ነገሩን ጥቂት ጊዜ ተጯጩሆ ተወው። በወቅቱ ጉዳዩን የዘር ጭፍጨፋ ብዙ ምልክቶች አሉት ያሉ ሰዎች ብሄር ከብሄር ሊያጋጩ የመጡ የሰላም ጸሮች የሚል ስም ተሰጣቸው። የዚህ ድርጊት ሰለባ የነበሩ የደቡብ (በተለይ ጋሞዎች) ከዚያ ወዲህ አካባቢውን ለቀው እንደወጡ ይነገራል። መጤዎችና ወራሪዎች የሚል ተደጋጋሚ ስም እየተሰጠው በተለያዩ አካባቢዎች ይህን መሰል ድርጊቶች በመጠን አነስተኛ ሆነው የቀጠሉ ቢሆንም፤ሰሞኑን ደግሞ በለገጣፎ ላይ እጅግ በርካታ ኢትዮጵያውያንን በህጋዊነት ሰበብ ረጅም ዘመን ኖረው ሃብት ካፈሩበት፤ቤተሰብ ከመሰረቱበት ቦታ፤ ክልሉ አፍራሽ ሃይል ከነቡልዶዘር መድቦ ህጻናት እየተቁለጨለጩ መኖሪያቸውን ናደባቸው። የከተማው ከንቲባና የክልሉ የመሬት ልማት አስተዳደር ሃላፊ ይህ አሰቃቂ እርምጃ ህግ የማስከበር ስራ በመሆኑ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና እስከ 12 ሺህ ቤቶች እንደሚፈርሱ ሲናገሩ ነበር። ቤቱ የፈረሰበት ቦታም ለከተማው አረንጓዴ ልማት ማካሄጃ መሆኑን ጨመሩ። ነገሩ ህግ የማስከበር ሂደት ከሆነም፤እርግጥም መሬቱ የተፈለገው በጣም ለማያስቸኩለው አረንጓዴ ልማት ከሆነ፤ነዋሪዎችን ሰፋ ያለ ጊዜ ሰጥቶና አማራጭ ቦታ በማፈላለግ፤ህጻናትንና ሴቶቸን እንዲሁም አዛውንቶችን በማያጎሳቁል መልኩ ህግና ስርዓትን ማስከበር ሲቻል፤ ይህን ኢሰብዓዊ ድርጊት በጥድፊያ መፈጸም የተፈለገበት ምክኛት ለብዙዎቹ እንቆቅልሽ ሆኗል። ኦሮሚያ ክልል በተለይም አዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ ካድሬዎች ላላፉት ሃያ ዓመታት ገበሬውን እያፈናቀሉ መሬት ሲቸበችቡ መኖራቸው ጸሃይ የሞቀው ሃቅ ሆኖ ሳለ፤እንዲሁም አሁንም ምንም ዓይነት አገልግሎት ለመስጠት እጅ እጅ የሚመለከቱ የቢሮ ሰራተኞችን የያዘው ክልል፤ህገወጥነትን ከምንጩ የማድረቅ ስራ ለመስራት ቅንጣት ሙከራ ያላደረገ ክልል፤ የችግሩ ውጤትና ሰለባ በሆኑ ወገኖቻችን ላይ የፈጸመው ይህ ነው ተብሎ የማይገለጽ በደል፤ ድርጊቱ ሌላ ተልዕኮ እንዳዘለና፤ በአክራሪዎቹ የሚመራ የጸረ_ኢትዮጵያዊነት ዘመቻ ነው ብለን እንድናስብ አስገድዶናል።
ለመሆኑ የኢትዮጵያውያን ጥቃት በአዲስ አበባ ዙሪያ ለምን?
አክራሪዎቹ ይህን ዘመቻ በጥድፊያ የሚፈጽሙባቸው ሁለት ምክንያቶች ይታዩኛል። የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊነት የሚባልን የፖለቲካ ትርክትን ጨርሶ ማጥፋትና መዝሃት ሲሆን ሌላኛው ደግሞ የጎሳ ፖለቲካን እየሸሸ አዲስ አበባ የከተመውን ዜጋ ሳይወድ በግዱ ወደ አንድ የብሄር ፖለቲከኛ ቡድን እንዲጠጋ ለማድረግ ነው። ሁለቱንም እንያቸው
1. ኢትዮጵያዊ የሚል ትርክትን ማጥፋት
ወያኔና ኦነግ ወይም አክራሪ የኦሮሞ ፖለቲከኞች አላማቸው ምኑንም ያህል ቢለያይ አንድ በጋራ የሚያቁዋርጡት መስመር ግን አላቸው። እዚያች የጋራ መስመራቸው ላይ ኢትዮጵያ ( ምኒልክ ፈጠሯት የሚሏትን ኢትዮጵያ) የምትባልን አገር ያገኙዋታል። አካሄዳቸው ሲግል በማንኪያ ሲበርድ በእጅ ይሁን እንጂ፤ እጁም ማንኪያውም ያጠራቸው ቀን ትልቁ ድላቸው ይህቺን አገር ስትጠፋ ማየት ነው። በቻሉት ሁሉ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ወደደም ጠላ ወደ አንድ ብሄር ወይም ጎሳ እንዲጠጋና ኢትዮጵያዊነት (ለነሱ አስቂኝ ተረት ነው) የሚባል ነገርን ከአእምሮው እንዲያወጣ የማድረግን ስራ ሳይታክቱ ሞክረውታል። ይህ “ቅድሚያ ኢትዮጵያ” የሚለው ሃይል ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ትግሉ ከወያኔና ከአክራሪው ኦሮሞ ጋር ነበር። ወያኔና አክራሪው ሃይል የመንግስት በጀት ተመድቦላቸውና ህገመንግስታዊ ጥበቃ ተደርጎላቸው ነበር ከግራና ከቀኝ ኢትዮጵያን ያለውን ወገን ሲያጠቁት የነበረው። ሰዉን ካለምንም ሃሳብና አመክንዮ ወደጎጡ እንዲሸሸግ ማድረግ እንደትልቅ ስራ ቆጥረውት፤ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ አንድ የሚያደርግ ሃሳብ ተሸክመው ሲንገዳገዱ የነበሩ የአንድነት ሃይሎችን “መሬት ወርደው ድጋፍ ማሰባሰብ አቃታቸው” በማለት፤ጃዋር ሞሃመድ ደጋግሞ ሊያላግጥ ሞክሯል። አንድ ያልተረዳው፤ወይም ቢረዳውም እንዳልተረዳው የሚሆንበት ነገር ግን፤ ጎጠኝነትን በበጀት የሚደግፍ መንግስት በነበረባት ኢትዮጵያ፤ሰዎችን ቁስል ፈጥሮላቸው ቁስላቸውን እየነካኩ በጎጥ መሰብሰብ ሳምንት የማይወስድ የሰነፍ ስራ መሆኑን ነው። ኢትዮጵያን የሚሉ ሃይሎች ቢያንስ ሃሳብ ይዘውና ብሄርና ጎሳ ዘለል ሆነው ህዝብና ህዝብን ለማቀራረብ፤ይህን አጥብቆ ከሚቃውም ጉልበተኛ መንግስት ጋር እየታገሉ ሃያ ሰባት ዓመታት እየተንገዳገዱም ቢሆን እዚህ ደርሰዋል።
የሆነው ሆኖ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመንግስት በኩል የሚታይ የሚመስል ኢትዮጵያዊነትን የሚያጎለብት እርምጃ ብዙውን ኢትዮጵያዊ የሚያማልል ነበር። በመሆኑም የኢትዮጵያዊነት ሃይሉ በአዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር የሚሰበከውን አዲስ ትርክት አምኖ ተቀብሎ ሳይሰስት ከልጅ እስካዋቂ “ለውጥ” ለመሰለው ነገር ላይ ድጋፍ እያደረገ ቆይቷል። ይህ ደግሞ ለወያኔና ለአክራሪው ኦሮሞ ትልቅ ራስ ምታት ነበር። ለምን ቢባል የሚጠሏትን ኢትዮጵያ መልሶ የሚያመጣ ስለመሰላቸው፤እነሱ ትመለሳለች የሚሏት ብለው ሰሚዎቻቸውን የሚያስፈራሩባት ኢትዮጵያም ቢያንስ በዚህ ጊዜ ልትመለስ የማትችል መሆኑን ቢያውቁም፤በቻሉት ሁሉ የኢትዮጵያዊነት ሃይሉ ላይ ጥቃት ሊያሳርፉ ሲሞክሩ ይታያል። ወያኔ አቅሙን ነስቷት በሩቁ ሆና ህገመንግስቱ ተናደ እያለች ስታለቅስ፤አክራሪው ሃይል ደግሞ ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ ያሚያምነውን ሃይል ለማጥፋት ከአንድም ሁለት ጊዜ በአዲስ አበባ ዙሪያ ግዙፍ የሆነ ሰብዓዊ ቀውስ የፈጠሩ ሙከራዎችን አድርጓል።ከዚህ ቀደም በቡራዩ አካባቢ በርካታ የሆኑ ኢትዮጵያውያንን ገድሎ ጠያቂ ያጣው ቡድን አሁን ደግሞ በለገጣፎ በህግ ማስከበር ስም የሶስት ቀን አራስን በላይዋ ላይ ቤት ሲንድባት የሚያመላክቱ ዜናዎችን ሰምተናል።
አካሄዱ ግልጽ ነው። ይሄው ዘመቻ ወደ ኢትዮጵያዊነት መናኅሪያዋ አዲስ አበባ መሃል ከመምጣቱ በፊት ዙሪያውን ያሉ ኢትዮጵያውያንን በመከራ፣እንግልትና ሞት ኢትዮጵያዊነት ላይ ተስፋ እንዲቆርጡ ማድረግ ነው የተያዘው። ጃዋር ሁሉንም ነገር በአግባቡ ተዘጋጅተንበት አቅደንበት ነው እየሰራን ያለነው በማለት ሲነግረን ከርሟል። ከዚያ በኋላስ? አክራሪዎቹ ከተሳካላቸው ኢትዮጵያዊነትን የሚያስቀድሙ ዜጎችን በእንዲህና መሰል ድርጊቶች በማስጨነቅ ወደ አንድ የብሄር አቁማዳ ካስገቡ ትልቁ ድላቸው ነው። ወዴት እንደሚገቡላቸውም ቢያንስ መገመት አያቅታቸውም።
2. ኢትዮጵያዊያንን አብን ውስጥ ማግኘት?
እንደብዙዎቹ አክራሪ ኦሮሞዎች አስተሳሰብ ሰው ሰው ለመሆን የሆነ ብሄር ውስጥ መግባት አለበት። እንደነሱ ከሆነ ሸዋ ላይ በተለይም አዲስ አበባ ላይ የነገሰው ኢትዮጵያዊነትም ቢፈለቀቅ ውስጡ “አማራ” ነው። አክራሪው ሃይል ይህን ኢትዮጵያዊነት አማራ ሆኖ በግላጭ እንዲያገኘው በጣም ይፈልጋል። ለዚህ ማስረጃ የሚያስፈልግ ከሆነም ጃዋር ባህርዳር ሄዶ አማራው የበለጠ ብሄርተኛ እንዲሆን የለመነበትን ጉዞውን ማስታወስ ይበቃል። ዛሬ የአንድነት ሃይሉ በወሬ “ተታሎ” ወይም ተዳክሞ መገኘቱ፤ ጃዋር አማራን “ኢትዮጵያዊነትህን ተወው አላዋጣህም” የሚል የባለጌ ምክር እንዲለግስ አድርጎታል። ወዲያውም ደግሞ አብን የሚባል ፓርቲ ተመስርቷል። ለጃዋርና ለመሰሎቹ ትልቁ ፍላጎታቸው ኢትዮጵያ የሚል ሃይል ጠፍቶ ሁሉንም በየ|ጎሬው ማግኘት ነው። ስለዚህ በአዲስ አበባ ዙሪያ ያለውን ኢትዮጵያዊ በመግደልና በማፈናቀል፤ መሃል አዲስ አበባ ላይ ያለውን ዜጋ ስጋት ውስጥ መክተትና መግቢያ ማሳጣት አንዱ ዓላማው ይሆናል። አዲስ አበባ ላይ ባለው የአማራ ህዝብ ብዛት ምክንያት፤ ብዙው የአዲስ አበባ ህዝብ “አንድነት” የሚያቀነቅኑ የፖለቲካ ሃይሎች ተዳክመው ሲያይና ተስፋ ሲቆርጥ ሮጦ ሊጠጋ የሚችለው ወደ አማራ ወይም አብን ነው ተብሎ የተገመተም ይመስላል።የአዲስ አበባ ህዝብ ጎራውን ከለየ በኋላ ያለው ነገር “እዳው ገብስ” ነው የሚል ስሌት የተሰራም ይመስለኛል። ብዙው ሰው አዲስ አበባ ላይ ወደ አብን ሄደ ማለት ደግሞ እንደጃዋርና መሰሎቹ ግምት የውጊያ ሜዳው ይጠራል። “እስከዛሬ ኢትዮጵያዊ ነኝ እያለ የኖረው ህዝብ ይኅው በተግባር አማራ ነው” ብሎ ሳምንት የማይፈጅ የሰነፍ ቅስቀሳውን እንዲጀምር ያግዘዋል። በዚህም አገሪቱን ወደለየለት ትርምስና እልቂት የመክተት የረጅም ዘመን ምኞቱ እውን ይሆናል። ኢትዮጵያ የምትባልና ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚል በሌለበት የደካሞች ጫወታ ደግሞ አሸናፊው እኔ ነኝ የሚል ድጋሚ የሰነፍ ሂሳብም ሰርቶ የተቀመጠ ይመስለኛል። ባላፈው ሳምንትም ጃዋር ለዋልታ በሰጠው ቃለ መጠይቅ ላይ የአድስ አበባ ህዝብ ድምጹን ሲሰጥ ቀጥሎ የሚመጣውን የእኛን የበቀል በትር ግምት ውስጥ አስገብቶ መሆን አለበት ሲል ነበር። አትዮጵያዊነት ግን ሲገፉት ተመልሶ ይመጣል።አዲስ አበቤዎችም ይህ ሁሉ መንገድ ያዋጣዋል ወይ ብለን እንጠይቀውና ይህንም እንጋብዘዋለን ጃዋርን
እኔ ያርበኛ ልጅ ነኝ፤ ጆሊ ባር ጊርጊሮ
ፈርቶ አይሞት አራዳ፤በማተቡ ኖሮ
ጽሁፉ የዝግጅት ክፍሉን አመለካከት አይወክልም፣ የጸሃፊው ብቻ ነው

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ሰበር ዜና – ትህነግ በዲፕሎማሲ ዘመቻ ቀውስ ገጠመው፤ “ በሃሰት መረጃ አሳፈራችሁን ” የቅርብ አጋሮቻቸው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *