‹‹ለጣና ትረስት ፈንድ የተሰበሰበውን ገንዘብ አፈፃፀም ማወቅ ለፈለገ ሁሉ መረጃ ለመስጠት ዝግጁ ነን›› የአማራ ክልል አካባቢ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለስልጣን ተናግሯል፡፡

(አብመድ) ባለፉት ሰባት ዓመታት በጣና ሐይቅ ላይ የተጋረጠውን የእንቦጭ አረም አደጋ ለመከላከል በመንግሥትና በሕዝቡ የሚደረገው ድጋፍ አልተቋረጠም፡፡ ምንም እንኳን አረሙን ለማስወገድ የሚደረገው ዘመቻ ወቅታዊ ሆኖ ወጥ የሆነ አፈፃፀም ባይኖረውም ድጋፎች ግን እንደቀጠሉ ናቸው፡፡

ከየካቲት 2010 ዓ.ም ጀምሮም ‹‹የጣና ትረስት ፈንድ›› ተቋቁሞ በጣና ላይ የተከሰተውን የእንቦጭ አረም መቆጣጠር እንዲቻል ገንዘብ የማሰባሰብ ሥራ ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ የጣና ትረስት ፈንድ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጣ የራሱ የሆነ የሥራ አስፈፃሚ ቦርድ አባላት ያሉት ሲሆን የገንዘብ ማሰባሰቡም ሆነ ወጭ የማድረጉ ሥራ በቦርዱ የበላይ ተቆጣጣሪነት የሚከናወን ነው፡፡

አብመድ የእንቦጭ አረምን ለማስወገድ የሚሠሩ ሥራዎችን ሲዘግብ ከተከታታዮቹ በሚነሱ ጥያቄዎች መሠረት የተሰበሰበው ገንዘብ ምን ያክል ነው? የተሰበሰበው ገንዘብስ ለምን ሥራ እየዋለ ነው? በሚል የሚመለከታቸውን አካላት ጠይቋል፡፡

ፈንዱ ከተቋቋመ ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ድረስ ከ54 ሚሊዮን 900 ሺህ ብር በላይ ተሰብስቧል፡፡ ገንዘቡ የተሰበሰበው ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ ድርጅቶች እና ግለሰቦች ብቻ መሆኑን የአካባቢ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለስልጣን የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ጋሻው እሸቱ ገልጸዋል፤ ‹‹እስካሁን በጣና ትረስት ፈንድ በኩል ከሀገር ውጭ ባሉ ግለሰቦችም ሆነ ድርጅቶች የገባ ገንዘብ የለም›› ብለዋል፡፡

ከተማ ከበደ (ኬኬ ኃ/የተ/የግ/ማ) 15 ሚሊዮን ብር፣ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ)፣ አዋሽ ባንክ እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እያንዳንዳቸው 10 ሚሊዮን ብር፣ የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም (አብቁተ)፣ ዳሽን ባንክ፣ ወጋገን ባንክ እና ታይስና ኔህኮ የግል ድርጅት እያንዳንዳቸው ሁለት ሚሊዮን ብር፣ አቶ በላይነህ ክንዴ 1 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር፣ ኮሎኔል ደራርቱ ቱሉ 2 መቶ ሺህ ብር፣ አትሌት መልካሙ 112 ሺህ ብር፣ ቤአካ ጄኔራል ትሬዲንግ 159 ሺህ ብር፣ ከሞባይል ባንኪንግ 60 ሺህ ብር እና ከተማሪዎችና ልዩ ልዩ አካለት 150 ሺህ ብር መሰብሰቡን የኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተሩ አቶ ጋሻው ለአብመድ በሰጡት ማብራሪያ አስታውቀዋል፡፡

‹‹ከየካቲት 2010 ዓ.ም ጀምሮ እስካለፈው ጥር ወር 2011 ዓ.ም ድረስ ትኩረታችን በቂ ገንዘብ መሰብሰብ ላይ ነበር›› ያሉት ደግሞ የአካባቢ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር በላይነህ አየለ ቦርዱ ለመጀመሪያ ዙር 23 ሚሊዮን ብር አረሙን ለመቆጣጠር ሥራ ላይ እንዲውል መወሰኑን አስታውቀዋል፡፡

ከተወሰነው ገንዘብ ከፊሉ ለሰው ጉልበት ክፍያ እና 9 ሚሊየን ብሩ ደግሞ ለተለያዩ የእንቦጭ አረም የማስወገጃ ዘዴዎች እንዲውል እንደሚደረግና የመጀመሪያው አፈፃፀም እየታዬ እንደሚቀጥል ዶክተር በላይነህ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ወደ ገዳማት ለመግባት በእምቦጭ ምክንያት ለተቸገሩ መነኮሳት የአረሙ ማስወገጃና የጀልባ መግዣ 825 ሺህ 500 ብር ወጭ መደረጉም ታውቋል፡፡ ዶክተር በላይነህ ‹‹ለጣና ትረስት ፈንድ የተሰበሰበውን ገንዘብ አፈፃፀም ማወቅ ለፈለገ ሁሉ መረጃ ለመስጠት ዝግጁ ነን›› ሲሉም ቃል ገብተዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *