አምና በያዝነው ማርች ወር ላይ፣ ሀገራችን የመጨረሻ አደገኛ ሁኔታ ላይ ደርሳ በነበረችበት ሰአት፣ የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰን እና የሩሲያው አቻቸው ሰርጌይ ላቭሮቭ “ለጉብኝት” በሚል ሰበብ ወደ ሀገራችን መጥተው እንደነበር ይታወሳል። በጊዜው ሀገራችን የገጠማትን ሁኔታ ተንተርሳ አሜሪካ በተለመደ አነጋገሯ፤ ወገንተኝነቷ ለሕዝብ ፍላጎትና ለዴሞክራሲ መሆኑን ስትገልፅ፣ በአካኼዷ ሁሉ ከአሜሪካ በመቃረን አቋሟን ለማንፀባረቅ የምትጥረው ሩሲያ ደግሞ ውግንናዋ ለመንግሥት እንደሆነ አሳወቃ ነበር። ያውም ኢትዮጵያ የኒዩክሌር ኃይል ማመንጫ እንድትገነባ እገዛ ለማድረግ ፍላጎት እንዳላት በመግለፅ ጭምር።

ይህ እንግዲህ በወቅቱ ሀገራችን የገጠማትን የመበጣበጥ ሥጋት እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም፣ የእነ ሶሪያን አይነት ዕጣ ፈንታ ሊያስከትል የሚችል ፖለቲካዊ ፉክክር በሜዳችን ለማድረግ የተሞከረበት የኃያላኑ አስፈሪ ፍጥጫ እንደ ነበር መገመት አይከብድም። ሩሲያ ከሶሻሊስቱ ርዕዮተ አለም መዳከም በኋላ ከኢትዮጵያ ጋር እዚህ ግባ የሚባል የኢኮኖሚም ሆነ የፖለቲካ ትስስር እንደሌላት እየታወቀ፣ አሜሪካንን ለመፃረር ስትል ብቻ ሀገራችንን እንደነ ሶሪያ ወደ አደገኛ ሁኔታ የሚያስገባ ጣልቃ ገብነት ለመፈፀም ማንዣበብ ጀምራ እንደነበር ድርጊቱ አንድ ማሳያ ይሆናል።

እንደ ጥሩ ዕድል ሆኖ ከሚንስትሮቹ ጉብኝት ጥቂት ጊዜ በኋላ የእነ ጠ/ሚ ዐብይ ወደ ሥልጣን መምጣት ነገሮችን ሁሉ አረጋጋው። በአደባባይ ለኢትዮጵያ የኒዩክሌር ኃይል ማመንጫ ግንባታን አግዛለሁ ያለችው ራሺያም በዛው የውኃ ሽታ ሆና ጠፋች። ያው ነገሩ ከጅምሩ በሀገራችን ጉዳይ እሷም ድርሻ እንዳላት በዘዴ ለአሜሪካኖቹ ለማሳየት ያለመ እንጂ ለኢትዮጵያ በመቆርቆር የተደረገ እንዳልነበር የነገሩን አካኼድ በደንብ ያስታውቃል።

ነጥቡ፦

ሀገራችን ወደ ትርምስ ከገባች ማንም አይደርስልንም። ዐረቡም፣ ምዕራባውያኑም፣ እነ ቻይናም፣ አሸባሪዎችም፣ ጎረቤት ሀገራትም ሁሉም የድርሻውን ለመዝረፍ የራሱን ድግስ ይደግስልናል እንጂ ማንም ገላጋይ አይኖረንም። ኢትዮጵያ ውስጥ እያንዣበበ የሚገኘው የጥፋት ደመና ከዘነበ፤ በሰው ልጆች ታሪክ እጅግ ዘግናኙ ዕልቂት ሊሆን እንደሚችል መገመት አይከብድም። ለምሳሌ የሩዋንዳው የዘር ፍጅት በተፈፀመበት ጊዜ የሀገሪቱ የሕዝብ ቁጥር 10 ሚሊዮን አካባቢ ብቻ ነበር።

ነገር ግን በ100 ቀናት ጭፍጨፋ በተፈፀመ ፍጅት የሕዝቡ አንድ አስረኛ ማለትም 1 ሚሊዮን ያህሉ አልቋል። ያውም የሩዋንዳዎቹ የፀብ ጎራ ሁለት ቡድን የተከፈ ነበር፣ ቱትሲና ሁቱ የሚል። አስቡት ደግሞ የእኛን ነገር፤ የሀገራችንን የሕዝብ ቁጥር፣ የልዩነታችንና የቁርሿችንን አይነትና ብዛት፣ ማን ማንን ይገላግላል? ማን ከማን ይተርፋል? የሩዋንዳ ዕልቂት በኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛት አንፃር ቢመነዘር፤ ካለን 100 ሚሊየን ሕዝብ አንድ አስረኛው ማለትም ከ10 ሚሊየን ሕዝብ በላይ ያልቃል እንደማለት ነው።

ለማንኛውም አሁንም ቢሆን መፍትሔው ያለው በእጃችን ነው። ፈረንጆቹ ሊያግዙን ቢፈልጉ ገና ድሮ ያደርጉት ነበር። የችግራችን ዋና አባባሾች እነማን እንደሆኑ እነ አሜሪካ ሳያውቁት ቀርተው አይደለም። የራሳቸውን የምዕራባውያኑን ዜግነት በያዙ የሰው ውሾች ሀገራችን እየተበጠበጠችና እየተሸበረች መሆኗን ያውቃሉ። ግን አለ አይደል፣ ሕዝባችን እርስ በርስ ቢባላና ቁጥሩ ቢቀንስ፤ በስደት፣ በረሃብ፣ በበሽታና በእርዳታ ያጨናነቅናቸው ሸክም ይቀንስላቸዋል እንጂ ምን ይጎዳሉ? ምንም። እነሱም ልክ እንደነሶሪያ የጦር አቅም መፈታተሻ ሜዳ ያገኛሉ። ስለዚህ ከእልህ ወጥተን ስለ ሕዝብ የሚገደን ሁሉ በመተባበር እና በመናበብ የሀገራችን አተራማሾችን ለማስቆም ሁሉንም አስፈላጊ ነገሮች ማድረግ ይጠበቅብናል። ሀገር እና ሕዝብ ከጎሣ እና ከፖለቲካ በላይ መሆናቸውን ሁሌም ማስታወስ አለብን። ለሁሉም ጨርሶ ሳይረፍድ እንንቃ።

www.facebook.com/100000448486519/posts/2405166456174947

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *