በአዲስ አበባ ላይ ባለኝ “ጉልበት ያለው ተሸክሟት ይዙር” አቋም ምክንያት በወዳጆቼና በጠላቶቼ መካከል ንትርክ መፈጠሩን ሰምቻለው። ስለዚህ ግጭቶችን ለመቀነስ ያለኝን አቋም ግልጽ በማድረግ ሰላም ለመፍጠር የሚከተለውን ማብራሪያ ለማቅረብ ተገድጃለው

አንድ ሰው፣ ቡድን ወይም ፓርቲ ለሕግ በታች እንጂ የተለየ ሆኖ አይታይም። ኦሮሞም ቢሆን። በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 9 ስለ የሕገ መንግሥት የበላይነት የተዘረዘረው እንዲህ ይላል፡፡ “ሕገ መንግሥቱ የአገሪቱ የበላይ ሕግ ነው፡፡ ማንኛውም ሕግ፣ ልማዳዊ አሠራር፣ እንዲሁም የመንግሥት አካል ወይም ባለሥልጣን ውሳኔ ከዚህ ሕገ መንግሥት ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈጻሚነት አይኖረውም”

ዋናው ጉዳይ:- የአዲስ አበባ ስያሜ …

በመጀመሪያ የአዲስ አበባ ባለቤትነት ጥያቄም ሆነ ምላሽ መጀመር ያለበት ከምንድነው? በእኔ አመለካከት አንድ መሰረታዊና ህጋዊ መፍትሔ አለው ብዬ አምናለው። የአዲስ አበባ ነዋሪ በመጀመሪያ በህግ ማሳመንና ማጽናት ያለበት የከተማዋን ስም (ስያሜ) ነው። ከዚያ በኋላ አብዛኛው ንትርክ መፍትሔ ያገኛል የሚል ጠንካራ እምነት አለኝ።

አዲስ አበባ የፌዴራል መንግሥቱ ዋና ከተማ ነች፡፡ ፌዴራል መንግሥቱ አዲስ አበባ ይላታል፡፡ የከተማዋ አስተዳደርም አዲስ አበባ ይላታል፡፡ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ በመሆኗም በዓለም አቀፍ ደረጃ አዲስ አበባ በሚለው ስያሜ ትታወቃለች፡፡ ይሁን እንጂ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አዲስ አበባ ብሎ ከመጥራት ይልቅ በኦፊሴላዊ አጠራር ፊንፊኔ ይላታል፡፡

በመንግሥትና በፓርቲ ቁጥጥር ሥር ያሉት ሚዲያዎች የኦሮምኛ ኘሮግራሞች የሚጠቀሙት ፊንፊኔ የሚለውን ስያሜ ነው፡፡ በአንድ ጣቢያ ውስጥ ለሌሎች ቋንቋዎች አዲስ አበባን የሚለውን ስያሜ ሲያገለግሉበት በዚያው ጣቢያ ያለው የኦሮምኛ ቋንቋ ማስተባበሪያ በፊንፊኔ ሲጠቀም ይሰማል፡፡ ይህ የብሔራዊ መግባባት ችግር ነው፡፡ የአዲስ አበባ ስም አዲስ አበባ እንጂ ፊንፊኔ አይደለም፡፡ አንድን ከተማ በሁለት የተለያዩ ስያሜዎች መጥራት በምንም ዓይነት መልኩ ተገቢ አለመሆኑ የፌዴራል መንግሥቱ መቀመጫዬ አዲስ አበባ ይባላል እያለ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፊንፊኔ ማለቱ ከሕግ አግባብ አንፃር ትክክል አይደለም። የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በተለያዩ ደረጃዎች የሚለዋወጣቸው ደብዳቤዎችም ሆኑ የጽህፈት ቤቱ መቀመጫ ፊንፊኔ እንደምትባል ሲገልፅ ይህ በምን መስፈርት እንደሆነ ግልፅ አለመሆኑንና አንድን ከተማ በሁለት ስያሜ መጥራቱ ያለውን የብሔራዊ መግባባት ችግር የሚያሳይ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት አንቀፅ 49 ስለ ርዕሰ ከተማ የሚዘረዝር ሲሆን የፌዴራሉ መንግሥት ርዕሰ ከተማ አዲስ አበባ ነው ሲል በዚሁ አንቀፅ ላይ ተደንግጓል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም በሕገ መንግሥቱ በተሰጠው መብት መሠረት ከተማዋን በቻርተር ሲያስተዳድር የከተማዋ ስያሜም አዲስ አበባ መሆኑን በቻርተሩ ላይ ያመለክታል፡፡

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት መቀመጫ ከአዲስ አበባ ወደ አዳማ እንዲዘወር ከተወሰነ በኋላ ተመልሶ በአዲስ አበባ የሆነው ምርጫ 97ትን ተከትሎ ነበር፡፡ በወቅቱ ለተወሰደው እርምጃ የተለያዩ ትርጓሜዎች የተሰጡት መሆኑ ይታወሳል፡፡ በብዙ ጥናት ወደ አዳማ ማዕከሉን ማዛወሩን የገለፀው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት፣ ወደ አዲስ አበባ ተመልሶ ቢገባም ለክልሉ ቤተ መንግሥትና የመሥሪያ ቤት ስራዎች የተገነቡት ሕንፃዎች ለአዳማ ከተማ ተጨማሪ ገፅታ ፈጥረውላታል፡፡

የኦሮሚያ ዋና ከተማ አዳማ እንድትሆን መወሰኑም በዚያው ተዳፍኖ ቀርቷል፡፡ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት መቀመጫ አዲስ አበባ ከመሆኑ ላይ ምንም ዓይነት በስያሜው ተቃውሞ እንደሌለው ግን የክልሉ መንግሥት ከተማዋን ፊንፊኔ ከማለት ይልቅ አዲስ አበባ ብሎ መጥራት እንዳለበት ገልጸው ነበረ። አዲስ አበባ የሚለው ስያሜ የአገሪቱንም ሕዝብ ሆነ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡን የሚያስማማ በመሆኑም ፊንፊኔ የሚለው ስም ከተማዋን እንደማይወክላት በወቅቱ የነበረው የኦህዴድ አመራር ገልጿል። አሁንም የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል ሕገ መንግሥት የክልሉ መቀመጫ ፊንፊኔ ነው ማለትና መሰየም አይቻልም። በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 49 የአገሪቱ መንግሥት ርዕሰ ከተማ አዲስ አበባ ነው የሚለው በምንም ዓይነት መልኩ በክልሎች ሕግ ሊሻር አይቻልም፡፡ በዚሁ መሠረት የክልሉ መንግሥትም መቀመጫ ፊንፊኔ እንደምትባል በህግም ከታሪክ አንፃርም አይቻልም።

ፊንፊኔ በአዲስ አበባ ውስጥ የአንዲት ቦታ ስያሜ ተደርጐ ሊቆጠር ይችላል፡፡ እንደ ቦሌ፣ ጉለሌ፣ መካኒሳ፣ ሣሪስ ወይም መርካቶ ተብሎ አዲስ አበባ ግን የተለያዩና ሰፊ የሆኑ ቦታዎችን የያዘችና የአገሪቱ ርዕሰ መዲና ተደርጋ በዓለም ደረጃ የምትታወቅ በመሆኑ የሚያስማማው በአንድ ስም መጥራት ነው። አንድ የአለም አቀፍ የዲፕሎማቶች ከተማ በሁለት ስም በኦፊሴላዊ መንገድ ቢጠራ በዓለም አቀፍ ግንኙነት፣ በኢንቨስትመንት፣ በእርዳታ፣ በቱሪዝም እና በሌሎች መስኮች አሉታዊ ተፅእኖ ይገጥመዋል፡፡

የፌዴራሉ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 49 ንዑሥ አንቀፅ 5

“የኦሮሚያ ክልል፣ የአገልግሎት አቅርቦት ወይም የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀምንና የመሳሰሉትን ጉዳዮችን በተመለከተ እንዲሁም አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሃል የሚገኝ በመሆኑ የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ያለው ልዩ ጥቅም ይጠበቅለታል፡፡ ዝርዝሩ በሕግ ይወሳል” የሚል ሲሆን የአገሪቱን ርዕሰ መዲና ስያሜ ኦሮሚያ ክልል የሚቀይርበት መብትና አግባብ በህግ አልተፈቀደም።

በኢትዮጵያ ውስጥ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የከተሞች፣ የትምህርት ቤቶች፣ የወረዳዎች፣ የከተማዎች፣ የጤና ጣቢያዎች የሚጠሩበት ስያሜ እየተቀየረ የመጣ ሲሆን የናዝሬት አዳማ መባል፣ የደብረ ዘይት ቢሾፍቱ መባል፣ የአዋሣ ሃዋሣ መባል እና ሌሎችንም መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከተሞቹም በኦፊሴላዊ መንገድ በአዲሱ ስያሜያቸው ሲጠሩ በተለምዶና በመግባቢያ ደረጃ በተሠረዘው ስማቸው ይጠራሉ። መልካም ነገር ነው።

በዚህ ጉዳይ የመጀመሪያው ስራ መሆን ያለበት አዲስ አበባ የሚባለው ስያሜ ኦፊሴላዊ ሆኖ ኦሮሚያ ክልልም በ1997 አምኖ እንደተቀበለው አሁንም ስያሜውን ተቀብሎ መስራት ይኖርበታል። ፊንፊኔ የሚለው ሥያሜ እንደ ሸገር ኦፊሴሊያዊ ሳይሆን መጠቀም እንደሚቻልም ውሳኔ ሰጥተው ነበረ። አሁን ያለው ፊንፊኔ የሚለው አጠራር ግን በአንዲት አገርና በአንድ መንግሥት ውስጥ የማይደረግና አግባብነት የሌለው ፖለቲካዊ ብልግና ነው።

በስያሜ ጉዳይ ሃሮማያ በቀድሞው አለማያ ዩኒቨርሲቲ ስያሜ ከፍተኛ ችግር በትምህርት ተቋሙ ውስጥ ተነስቶ እንደነበረ ይነገራል። የኦሮሚያ ክልል በስሩ ያሉ ከተሞችን ስያሜ የመለወጥ፣ የማስተካከል፣ ሙሉ መብት አለው። ሆኖም ግን ከላይ እንደጠቀስኩት ከሕገ መንግሥቱ ራሱ ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚቃረን ሕግ ከወጣ ተፈፃሚነት የለውም ይላል። የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የመቀመጫውን ስያሜ አዲስ አበባ ማድረግ ካለበት የኦሮሚያ ክልልም የፌዴራሉን ዋና ከተማ ስያሜ መቀበል አዲስ አበባ በሚለው ስያሜን ሁሉም ወገን መስማማት አለበት። በህግ አዲስ አበባ በሚለው ስያሜ ብቻ ተቀባይነት እንዲኖረው ማድረግ የመጀመሪያው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች አላማና ግብ መሆን አለበት። አዲስ አበባ የሚባል የኦሮሞ ብሔረሰብ ብቻ የሆነ ከተማ አለመሆኑ የከተማው ትክክለኛ ስያሜ ራሱ ይናገራል።

Leje Gerume Facebook

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *