መግቢያ

ሀገራችን ኢትዮጵያ ሰፊ ግዛት ፣ በብዝሃነት የተዋበ ገናና ረጅም ዘመን ታሪክ ያላት ሀገር ናት። ታሪኳም በብዙ ፈተናዎች፣መከራዎች፣ ትግሎችና ድሎች የነጠረ ታሪክ ነው። ሆኖም ግን ከጥንታዊነቷና ታላቅነቷ አንጻር ሲታይ አሁንም ድረስ ያልተፈቱ ብዙ እንቆቅልሾችና በአግባቡ ተነጋግረን የጋራ መግባባት ላይ ያልደረስንባቸው አንገብጋቢ ጉዳዮች ያሉባት ሀገር ናት። የዚህ ጽሑፍ ዓላማ መሠረታዊ የሆኑ ጉዳዮችን በመዳሰስ ለሀገር ግንባታ በሚደረገው የሀሳብ ልውውጥና ክርክር ለመሳተፍ የጋራ መግባባት ለመፍጠር ለማገዝ ነው። በጽሑፉ ያሉት ሐሳቦች የጸሐፊው የግለሰብ ምልከታ ስለሆኑ እንደ አንድ የውይይት ግበዓት ተደርጎ እንድታይ ጸሐፊው ከወዲሁ ያሰስባል።

እንቆቅልሾቻችን
ስለኢትዮጵያ ያልተፈቱ እንቆቅልሾች ስናስብ የሚነሳው የመጀመሪያው ጥያቄ ከየት እንጀምር የሚለው ነው። ኢትዮጵያ ውስብስብና ውዝግቦች የበዛበት ታሪክ አላት። ከሀገር አስተዳደር ታሪክ ስንነሳ ምንም እንኳን ለብዙ ዓመታት የሚቆጠር አገራዊ ወይንም ብሔራዊ ታሪክ እንዳለን ቢተረክም ሁሉን አቀፍ መዕከላዊ መንግስት በመለዉ ሀገሪቱ ከተዘረጋ ብዙ መቶ ዓመታት አላስቆጠርም። እንደ ኦሮሞ የገዳ ስርዓት የተለያዩ ብሔርብሔረሰቦች ራሳቸውን የሚያስተዳድሩበት የየራሰቸዉ በህላዊ ወጎች ያላት ሀገር ሆና ቆይታለች። እንደአብዛኞቹ አገሮች የሀገራችንም ሁሉን አቀፍ መዕከላዊና ዘመናዊ የአገር አስተዳደር የመመስረቱ ሂደት ችግሮች የነበረበት መሆን የማይታበል ሀቅ ነው። በሰላማዊ መግባባት የተመሰረተ ሀገር የለም። ይልቁን ትልቁ ፈተናችን እስከዛሬም ድረስ የተነሱት መንግሥታት ወደ ሥልጣን የመጡት፤በስልጣን የቆዩትም በጉልበት አሊያም በብልጠት ነው ። ስለዚህ የመጀመሪያው መነሻችን መሆን ያለበት ኢትዮጵያ ዛሬም የህዝብና የህግ የበላይነት ያልተረጋገጠባት ሀገር መሆኗን በመቀበል ነው።

ሁለተኛው ያልተፈታው የሀገራችን እንቆቅልሽ የሀገሪቱ ፖለቲካና አስተዳደር ሁሉንም አሳታፊነትና የሁለም ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የመረጋግጥ ችግር ያለበት መሆኑ ነው። ኢትዮጵያ ጥንትም ሆነ አሁን በጥቂት ብሔር ብሔረሰቦች የስልጣን ፉክክር የተቀረው ተመልካችና ትርፍራፊ ተጠቃሚ የሆነባት ሀገር ናት። ድሮ ፉክክሩ በትግሬና በአማራ መካከል ነበር፣ አሁን ደግሞ ተራው የኦሮሞ ይመስላል። የደጋውና የቆላው፣የመሃል ሃገርና የጠረፍ አከባቢ ህዝቦች ኢፍትሃዊ የስልጣንና የሀብት ተጠቃሚነት ወይንም ይገባኛል ባይነት ኢትዮጵያን እውነትኛ ፍትሕ ያልሰፈነባት ምድር እንደሆነች ያሳያል።

ሶስተኛው የሀገራችን ያልተፈታው እንቆቅልሽ በህዝቡ ዕለታዊ ኑሮና የፖለቲካ ልሂቃኑ ባነገበው ርዕዮተዓለምና ራዕይ አለመጣጠም ነው። ሀገራችን ኢትዮጵያ ብዙ ቀናኢ የፖለቲካ ልሂቃንን አፍርታለች።ምናልባትም ከሚያስፈልጋት በላይ የፖለቲካ ልሂቃንና ድርጅቶች ሰይኖራት አይቀርም። የሚያሳስበው ደግሞ ከሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ይሁን በሌላ ምክንያት ብዙ የተማረው ሃይል ከሙያ ይልቅ ወደ ፖለቲካው አድልቷል። ይህም ሆኖ ግን የፖለቲካ ልሂቃን የሚያነሷቸውና የነገቧቸው አጀንዳዎች የህዝቡን የዕለትተዕለት ኑሮ አያንጸባርቅም። ለምሳል ያህል በዛሬዪቱ ኢትዮጵያ እጅግ የሚያወዛግበው የብሔር ማንነት ጥያቄ የኢትዮጵያ ህዝብ ቀዳሚ ጥያቄ ነው ብሎ ለማመን ያስቸግራል። ለስልጣን ጥመኞች ግን በቀላሉ ስልጣን ማግኛ መንገድ ስለሚሆን አንገብጋቢ ያልሆነዉንና የትም የማያደርሰንን ዘር ቆጠራ ተያይዘን መጠፋፊያ መንገድ ይዘናል። ስለ እርሻ፣ ስለ ጤና፣ ስለ ውሃ፣ ስለ መንገድ፣ ስለ ትምህርት፣ ስለ ሥራ ፈጠራ፣ ስለ እንዱስትሪ፣ ስለ ባህል፣ ወዘተ በማውራት ይልቅ ፖለቲካኞቻችን ዛሬም የሚያወሩት ስለአደረጃጀትና ስለማንነት ነው። ማንም ሰው ሹመት ሲሰጠው ወይንም ሲሻር ክርክሩ የብቃት ሳይሆን የማን ወገን ነው የሚል ሆኗል።

አራተኛው ያልተፈታው የሀገራችን እንቆቅልሽ የዘርና የሀይማኖት ማንነት ቆጠራና ጽንፍኝነት ነው። ምንም እንኳን የብሔር ወይም የዘር ማንነት ጥያቄ 1966 ዋለልኝ መኮንን ከለኮሰው ጀምሮ እያጨቃጨቀን ቢሆንም በጥልቀት ቢመርመር ግን ይህን ያህል አተካሮ ውስጥ የሚያስገባን አልነበርም። ነገር ግን በዋለልኝ መኮንንን ቀዳዳ ተጠቅመው ፍትሓዊ ዴሞክራሲን ለማምጣት የህዝቦችን ድጋፍ ለማግኘት ሲባል በብሔር ስም የተዋቀሩ ድርጅቶች ትግላቸው በስልጣን ጥመኞች ተቀልብሶ፣ ያልነበረንና የሌለን የብሔር ጭቆና የፖለቲካ ልበወልድ በመፍጠር ላለፉት 27 ዓመታት በዘር ተኮር ፌዴራሊዝም ስም ጥላቻ፣ ልዩነትና ዘረኝነት በገሃድ ተስፋፍቷል። ማንም ኢትዮጵያዊ የወገንንና የራስን ጥቅም ከማስቀደም የፀዳ አይደለም። ይህ በራሱ ችግር አይደለም፣ መሆንም የለበትም። ነግር ግን ሁሉም ለቤተሰቡ፣ ለሐይማኖቱ፣ ለዘሩ ማዳላቱን ትቶ ለሁሉም ክብርና ጥቅም ማሰብ ካልቻለ እንደ ሀገርና እንደ ህዝብ መቀጠላችን ጥያቄ ውስጥ ይገባል። ይህ ብቻ ሳይሆን ሀይማኖተኝነታችንም ሆነ አገር ወዳድነታችን ከንቱ ይሆናል።

አምስተኛው ያልተፈታው የሀገራችን እንቆቅልሽ ከላይ ከተጠቀሰው የጽንፈኝነት አስተሳሳብ ጋር በተያያዘ የምናነሳው ሁሉን ዓቀፍ ኅብረብሄራዊ አንድነት ነው። ኢትዮጵያ በሀይማኖት፣ በአሰፋፈር፣በስራ፣ በጋብቻ፣ በባህል የተሳሰርን ኅብረተሰብ ያላት ሀገር ናት። የሀገርና የሕዝብን አብሮነትና ፍቅር መሰረት ያደረገ ብሔራዊ የጋራ ማንነት ወይንም ኢትዮጵያዊነት ላይ አብዛኛው ሰው ያምናል።ኢትዮጵያዊ ማንነትም የሁሉንም ዜጎች መብትና ጥቅም የሚጠብቅ፣ የሚያስጥብቅና የሚያንጸባርቅ መሆን እንዳለበት አያከራክርም። ዋለልኝ መኮንን የዛሬ 40 ዓመት ገደማ ያነሳውም ይህኛውን ነጥብ ነዉ።የኢትዮጵያ ብሔራዊ ማንነት አሳታፊ፣ በብዝሃነት የተዋበ፣ ኅብረብሔራዊ አንድነት መሆኑን መቀበል ማለት ነው። እስከዛሬ በመጣነዉ መንገድ ግን የኢትዮጵያዊ ብሔራዊ ማንነት በጥቂት ቡድኖች የበላይነት የተመሰረተ እንደነበረ መካድ ኣይቻልም። ነገር ግን ምንም እንኳን የአማርኛ ቋንቋና የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ለኢትዮጵያ ማንነት ዋንኛ መገለጫዎች የነበሩ ቢሆንም የብሔር፣ የሐይማኖት ብዝሃነት ግን ከሀገሪቱ አልጠፋም። እርስበርስ እየተገፋፋንም ቢሆን የዉጪውን ጠላት እየመከትን አብርን ኖረናል። ስለዚህ የአሁኗና የአዲሲቱ ኢትዮጵያ ግንባታ የቀደመውን ታሪክ መሻር አለበት ብዬ አላምንም። ኢትዮጵያዊነትን እንደብዛታችንና ተዋጽኦአችን እናስፋው ሲባልም አማርኛና ኦርቶዶክስን እንጥፋ ማለት አይደለም። የብሔር ማንነት ጽንፈኞች ችግራቸው ይሔ ይመስለኛል። የኢትዮጵያ ግንባታን ታሪክ ለጥላቻና ለስልጣን ማግኛ መጠቀሚያ ማድረግ ይፈልጋሉ። በዚህ ረገድ ትልቁ ፈተና በብዝሃነት የተዋበ ሕብረብሔራዊትና አዲስ ኢትዮጵያን መገንባት ነው። ኢትዮጵያዊነት ሁሉን ማቀፍ፣ ሁሉን በፍትሃዊ መንገድ በእኩልነት ማስተዳደር መቻል አለበት። መቀባበልና መቻቻል የግድ ይላል። የመዕከላዊ መንግስት ሚናም ህዝቦችን በሰብዓኣዊና በዜግነት ጥላ ስር እንዲሁም በርጅም ዘመን መህበራዊ ትስስር መሰርት ወደ ሰላምና ብልጽግና መድረስ ነው።

ስድስተኛው የሀገራችን ያልተፈታው እንቆቅልሽ የሚለው የተፈጥሮ ሃብት ብልጽግና፣ የሰዉ ሃይል ብዛትና የህዝባችን የድህነት አሳዛኝ ኑሮ ነው። ሀገራችን በተፈጥሮ ሀብት የታደለች መሆኗን ብዙ ሰው ይመሰክራል። ለም፣ ሰፊና ሚቹ የእርሻ መሬት ይዘን በምግብ እጦትና በረሃብ መታወቃችን የአስተዳደር፣ የባህልና የዕውቅት ማነስ ችግር እንጂ ለዚህ ስለተፈጠርን አይደለም። የፀሓይ፣ የዝናብ፣ የዉሃ፣ የማዕድናትሃብቶቻችን ተጠቅመን ኑሯችንን ኣሳመረን ሌላውን መርዳት እየቻልን በብዙ ችግሮች ተተብትበን ዛሬም ብድርና ዕርዳታ ለማኝ ወይንም ሃገር ጥለን ተሰዳጅ ሆነናል።

የሀገራችን ያልተፈታው የእንቆቅልሾች ሁሉ እንቆቅልሽ የህዝቡ የፖለቲካ አስተሳሰብና ንቃት ህሊና ነው። ብዙ ጊዜ እንደሚባለው የኢትዮጵያ ህዝብ ሀይማኖተኛና ኩሩ ቢሆንም ለምርምር፣ ለጥያቄ፣ ለምክንያታዊነት አሁንም እንግዳ ይመስለኛል። ለሚወስናቸው ውሳኔዎች፣ ለሚደግፋችው ወይንም ለሚነቅፋቸው ሀሳቦች፣ በመረጃ የተደገፈ ቅቡልነት ባላው ሳይንሳዊ ዕውቀት ሳይሆን በዘልማዳዊ ሀሳብ የበለጠ የሚደገፍ ይመስለኛል።የራሳችን ዕውቀትናስልጣኔ የሌለን ይመስል በቴሌቪዥን መስኮት በምታየዉ ሁሉ የሚዋልል፣ ምሁራኑም ጭምር ከፈረንጅ የመጣዉን ሁሉ ያለጥያቄና ጥርጣሬ የሚቀበል ነው። ከዚህም የተነሰ የራስንም ይሁን ከሌላው አለም የምንማራውን እውቀት በአገባቡ መጣጣም ከአለመቻለችን የተነሰ ከሁለቱም መሃል የሚዋዥቅ ሆነናል። በተለይ ወጣቱ ገንቢ፣ ብቃትና ክህሎት ሰጥቶት ራሱንና ሀገሩን የሚለውጥ ጥራት ያለው ትምህርት ያለገኘ፣ ተምሮም በራሱና በሀገሩ ተስፋና እምነት ያጣ የተበደለ ትውልድ ይመስለኛል። የሀይማኖት ተቋሞቻችን ጥሩ ስነምግባር ያለው ለራሱ፣ ለእምነቱና ለሀገሩ መልካም አስተዋጽኦ የሚያደርግ ሀቀኛ ዜጋ ማፍራት ተስኗቸዋል። በለፉት ዓመታቶች በሀገራችን የሰፈነዉን ግፈኛና ስነምግባር የለሽ ስርዓትን በለመኮነን፣በህዝብ ዘንድ የነበራቸውን ክብርና ተደማጭነት የቀነሰበት ሁኔታ የነበረ ይመስለኛል። ስለዚህ የሀይማኖት፣ የትምህርትናምርምር፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ የመገናኛ ብዙሃን፣ የባህልና የፈጠራ ሙያ ተቋማት ያሉበት ሁኔታ መለወጥ እንዳለባቸው አጠያያቂ አይመስለኝም። ሁለንተናዊ ለዉጥና እድገት የህዝብ ንቃት ህሊና፣ ባለቤትና ተሳትፎ እንዲሁም የተቋማት ግንባታና ጥንካሬ መተኪያ የሌላቸው አዕማዶች ናቸው። ቢሆንም ለሀገር ለዉጥ፣ እድገት ወይንም ውድቀት የመንግስትና፣የፖለቲካ ሀይሎች ሚና ከሁሉ የላቀ ነው።

የዶ/ር ዐቢይ መንግሥት ለውጦችና የወደፊት ተስፋ

አገራችን ያልተፈቱ ብዙ እንቆቅልሾች እንዳሉባት ከላይ ለመዳሰስ ተሞክሯል። ዳሰሳው አገራችን የመጣችበትን መንገድ የሚያሳይ ነው። አሁን ግን ሀገራችን ወሳኝ በሆነና ታሪካዊ የለውጥ ሽግግር ላይ ትገኛለች። ለ፪፯ ዓመታት በግፍና በግትረኝነት የተመራው የኢህኣዴግ አገዛዝ የህዝብን እምቢተኝነት ተከትሎ እንድለወጥ በመገደዱ ወደ ፊት የመጡት የዶ/ር ዐቢይ መንግሥት አገራችንን ከጥፋት በመታደግ፣ ሰላምና መረጋጋትን፣ ሀገራዊ አንድነትን (መደመርን) እንዲሁም ዘላቂ ፍትሓዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት ቀንና ሌሊት እየሰሩ እንደሆነ ሁላችን ምስክሮች ነን። የዶ/ር ዐቢይ መንግሥት ከወንድማማቾቹ የለውጥ አብዮተኞች መንግስቱናግርማዊ ነዋይ ዘመን ጀምሮ (1953) የ1960 ዎቹ ወጣቶች የተመኙት ካአንዴም ሁለት ግዜ (1966, 1983) የጨነገፈው ፍትሓዊ ስርዓት ግንባታን የመመሰረቻ ታለቅ እድል ነው። ከግፈኛዉ ስርዓት ጋር ፊት ለፊት የተጋጠሙት ወጣቶችም ይሁን ስርዓቱን በብዙ ትዕግስት ከውስጥ የለወጡት መረዎች፣ በሀገር ውስጥም ይሁን ከሀገር ውጪ ከክፋትና ኢፍትሓዊ አሰራር ጋር የተጋፈጡ ሁሉ በለቤትነት የሚሰማቸው የተጋድሎ ታሪክ ነው። ይህም የኢትዮጵያ ህዝቦች የትዕግስት፣ የትግልና የጸሎት ውጤት ነው። የዚህ ትግልና ድል በለቤቱም ብዙ ነው።

እነዚህ የለውጥ ኃይሎች በብልህ፣ ሰላማዊና ስልታዊ መንገድ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህም በአጭር ጊዜ ብዙ የእርምት እርምጃዎችን፣ አስደናቂና ገንቢ ለውጦችን አስመዝግበዋል። ስርዓቱ ሲከተል የነበረውን የጥላቻና የፀብ ፖለቲካ በመተው ያለወንጀል በግፍ ታስረው የነበሩትን የፖለቲካ እስረኞች መፍታት፣ በተለያየ የዓለም ክፍሎች ተበትነው ስርዓቱን የሚፎካከሩትን የፖለቲካ ሃይሎች ወደ ሀገራቸው መጥተው በሰላማዊ መንገድ እንዲታገሉ መፍቀድ፣ የፖለቲካ ምሕዳሩን በማስፋት ዜጎች ሀሳባቸውን በነጻነት የሚገልጹበትንና የሚያደራጁበትን ሁኔታ መፍጠር፣ አፋኝና የዜጎችን ሰብዓዊ መብት የሚጥሱ ሕጎችን ማሻሻል፣ከኤርትራ ጋር የነበረውን ትርጉም የለሽ የጥላቻና የጦርነት ምዕራፍ ዘግቶ ሰላምና መልካም ጉርብትና ማምጣት፣ በውጪ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን በሀገራቸዉ ጉዳይ ማሳተፍና በቅርቡም ደግሞ አዲስና ብቃትን ያደረገ እንዲሁም የሴቶችን ፍትሓዊ የሥልጣን ተካፋይነት ያረጋገጠ ካቢኔ ማዋቀር ተጠቃሾች ናቸው።

ምንም እንኳን የዶ/ር ዐቢይ አመራር ሥርነቀል ለዉጦችን እያደረገ፣ ከህዝቡም ሆነ ከዓለም ኣቀፍ ማኅበረሰብ አድናቆትና ድጋፍ እያገኘ ቢሆንም የተጀመረውና የሚካሄደዉ ለውጥ ያሉበት አንዳንድ ድክመቶችም ይሁን ፈጣን ለውጥ የሚስትለው መሰረታዊ ችግሮች ለዉጡ እንዳይቀለበስ ከመፍራት በዝምታ እየታለፈ ይመስለኛል። ለምሳሌ ያህል ምንም እንኳን ዶ/ር ዐቢይ ያመጡት የመደመር ሀሳብ በአብዛኛው ህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያገኘና የሚያስማማ ቢሆንም በኢህኣዴግ ውስጥ እንኳን ብዙ ያልተደመሩ እንዳሉ የማይካድ ነው። ሌላዉ ያልተጠየቀውና ያልተመለሰው ጥያቄ ራሱ የመደመር ሀሳብ የፍትህን ጥያቄ እንዴት እንደሚመልስ ነው። ትናንት የሀገርንና የሕዝብን ሃብት አለአግባብ የመዘበሩ በመደመርና በይቅርታ ስም ከተበዳዩ ህዝብ መሃል እንዲኖሩ ሆኗል። መደመር ያለርዕታዊ ፍትሕ ወደ እውነተኛ ይቅርታና እርቅ ያደርሳል ብሎ ማመን አዳጋች ነው። በእርግጥ በሀገራችን በአሁኑ ግዜ አንጻራዊ ሰላምና መረጋጋት፣ የጋለ የለዉጥ ተስፋ ይስተዋላል። በአንጻሩም በብዙ የሀገሪቱ ክፍሎች ጠብ፣ ጭቅጭቅና መፈናቀል እየበዛባት ነው።

በተጨማሪም ሁሉም የራሴን ክልል፣ ዞን፣ ወረዳ እያለ ነው። ለዚህም ዓይነተኛው ምክንያት በሀገሪቱ የተዘረጋው ብሔር ተኮር ፌዴራሊዝ የወለደው የጎሰኝነት ፖለቲካ መሆኑ ግልጽ ነው። ጎሳ ወይም ዘር ተኮር ፌዴራሊዝም መነሻውም በሀገራችን የረጅም ዘመን ታሪክ በህዝቦች መካካል የተፈጠረ የጭቆና ስርዓት እንዳለ በማመን ነው። ይኼ መሰረታዊ እውነተኝነት የሚጎድለው አስተሳሰብ በህዝቦች መካካል ቅራኔንና የተበዳይነትን ትርክት በመንዛት በክፉም በደጉም፣ በሰላሙም በጭቅጪቁም አብሮ የኖረውን፣ በጋብቻ፣ በሀይማኖት፣ በልዩ ልዩ ማህበራዊ ትስስሮች አንድነቱን በልዮነት አቅፎ የኖራውን ልዮ ሀገራዊ እሴትና በህል የሚቃረን የመሰሪዎች ፈጠራ ነው። በዚህ ወሳኝ የሽግግር ወቅት እየተፈጠረ በላዉ መቀራራብ መሰረት አድርጎ የዶር አብይ መንግስት በሀይማኖትና በዘር ማንነት የሚደረገውን የፖለቲካ አደርጃጃት መጋፈጥ ካልቻሉ አካሄዱ አለባብሶ መራስ ይሆንና የለውጡ ስርነቀልነት ግን አጠያያቂ ይሆናል።

የዶ/ር ዐቢይ መንግሥት ለዉጦች ዳካማ ጎኖች አሉት ከሚያስብሉ ምክን ያቶች አንዱ በአመራሩ ስር የተደርጉትን የማሽሻያ አዋጆች ጥራትና ጥልቀት ነው። ለዚህ አንዱ ማሰያ በቅርቡ የታወጀው የብሔራዊ እርቅ አዋጅ ነው። ከብዙ አገሮች ልምድ እንደምታወቀው የብሔራዊ እርቅ አካሄድ በፖለቲካ ምክያት የተፈጸሙ የራጅምና የቅርብ ዘመን ግፎችን ተዓማንነት፣ ገለልተኝነት ባለው መልክ፣ ለህዝብ ግልጽ በሆነ ተደምጦ፣ አጥፊዎቹ ታውቀው፣ ተበዳዮቹ መልስ አግኝተው ሀገራዊ ትምህርት አግኝተን የሚናልፍበትና ዘላቂና አስተማማኝ መሆን ነበረበት። እየሆነ ያለው ግን በተፈጸመው ግፍ በቀታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ተሳታፊ የነበሩ ሰዎች ጭምር ተሹመዋል። አዋጁ ራሱ ሰላም እንጅ ፍትሕ ተኮር አይደለም። ያለፍትሕ ሰላም ማረጋገጥ ከባድ ይመስለኛል።

ምንም እንኳን የዶ/ር ዐቢይ መንግሥት ባሳየው አመራርና ባደረገው ለዉጦች እኛንም ሆነ መላዉን አለም እያስደመመ ቢሆንም አሁንም እንደጥንቱ በአንድ ሁሉን ፈጣሪ፣ ሁሉን አድራጊ መሪና አመራር ስር መሆናችን ግልጽ ነው። ዶ/ር ዐቢይ ደግ፣ቀና፣ ሀገር ወዳድ መሪ እንደውም በፈተና ቀን ሀገራችንንና ሕዝባችንን ለማዳን የተገለጡ ፖለቲካዊ መሲህ ቢሆኑም አሁንም ጥያቄዉ ለዉጡን ተቋማዊ፣ አሳታፊና የሕግ ማዕቀፍ በመፍጠር ዘለቄታዊነቱንና ሕዝባዊነቱን ቢያረጋገጡ ለሀገራችን ሰላምና ብልጽግና ተስፋ ያለው ይሆናል።

የሁላችን ሚና
በኢትዮጵያ ለሚካሄዱ ለውጦች የመንግስትና ሀገራዊው አመራር ሚና ከሁሉ የላቀ ነው ብለናል። ከመንግሥትና መንግሥታዊውን ሥልጣን ለመያዝ ከሚፎካክሩ ሀይሎች ብዙ ይጠበቃል። የምንመኘውና ለማየት የምንናፍቀዉ ፍትሓዊ ሥርዓት እንዲመጣና የሁላችን ኑሮ እንዲሻሻል ከሁሉም ዜጋ ትጋትና ተሳትፎ ይፈለጋል። ከሁሉ በፊት የአስተሳሳብ ለዉጥ ማምጣት አለብን። የፖለቲካ አመለካከታችንም ከዘውግና ዘር ቆጠረ በፊት በሁሉም ሰው ሰብዓዊነትና በጋራ የዜግነት መሰረት ማትኮር ይኖርበታል። የእያንዳንዱ ዜጋ ንቃተህሊና በበሰለ የፖለቲካ እውቀት ካልዳበረ የሀገራችን ህልውናም ሆነ እድገት ትልቅ ፈተና ይጠብቀዋል። የሁላችን ተሰትፎ ከሚያስፈልጋቸው ወሰኝ ጉዳዮች አንዱ ፖሊቲካ ነው። በሀገራችን አንዳንድ ወሰኝ ምዕራፎች ህዝባዊ ተሳትፎና ንቅናቄ ዋንኛዉ የለውጥ ምክንያት ቢሆንም እስካአሁንም ድረስ በየወቅቱ የመንግስት ስልጣን ከያዘው ፓርቲ ውጪ የህዝቡ የፖለቲካ ተሰትፎና አደረጃጃት ደካማ ነው። የፖለቲካ ፓርቲዎችም በምርጫ ወቀት ተይተው የምጠፉ ክስተቶች ናቸው። አሁንም የፖለቲካ ፓርቲዎቻችን በምርጫ ማሸነፍ ህልም ከማትኮር ይልቅ ህዝቡን ከታች ጀምሮ በማስተማርና በማደራጀት ንቁና ትጉ የፖለቲካ መህበርሰብ ለመፍጣር መስራት አለባቸው። አሁን ያለን የፖሊቲካ በህል በቀላሉ ወደ የትም አቅጣጫ ሊመራ የሚችል ነው። የፍትሕና የሕግ የበላይነት ያረጋጋጠ የመንግስትን ሚና በአግባቡ መለየት፣ የተጠናከረ ተቋማት ግንባታ፣ በሀገር ህልዉናናጥቅም ላይ ያተኮረ የፖሊቲካ ሀይሎች የጋራ መግባባት የህዝብን ንቃተህሊናና ተሳትፎ ማሳደግ መቀጠል አለበት። በማጠቃለያም የሀገራችን መጻኢ ዘመን የሰላም፣ የፍትሕ እና የህዝቦች የጋራ እድገትና ብልጽግና እንዲሆን እርስበርስ በመነጋገር ስለቀድሞ ታሪካችን፣ ስለአሁኑ ሁኔታና ስለወደፊቱ አቅጣጫ መያዝና መስያዝ አለብን።

በብሔር ተደራጅቶ ስልጣን መያዝ ከቀረ፣ ማንም በሰብዓዊናበዜግነት መብቱ የትም መኖርና መስራት ከቻለ፣ ሀገራችንንና ሀብቷ የሁላችን እስከሆነና ሁሉን በፍትሓዊነት የሚያስተዳድ ብቃት ያለ መሪ ከተገኘ፣ ኦሮሞ ቢሆን ትግሬ፣ አማራ ቢሆን ጉራጌ፣ ቤንሻንጉል ቢሆን ሱማሌ፣ ወንድ ቢሆን ሴት፣ ሙስሊም ቢሆን ጴንጤ፣ መምህር ቢሆን ሙዝቀኛ እኔ አይገደኝም። ፍትሓዊ ስርዓት፣ ሙያዊ ብቃት ያለው መገናኛ ብዙሃን፣ ነጻና ገለልተኛ ፍርድ ቤት፣ የሀገር አለኝታ የሆነ አገር ወዳድ መከላከያ፣ አድልዎን የሚዋጋ ቀልጣፋ፣ ግልጸነት ያለው አሰራር ነው ዋስትነችን። የአብሮነት በህልና ትስስራችንን ግን አንርሳው። እንከባበር፣ እንቀባበል አለዚያ በጽንፈኞች ወጥመድ እንዳንጠፋፋ፣ ጀግኖች እናቶቻንንና አባቶቻችን ያወረሱንን አገር እንዳናፈርስ። ቅድሚያ ለሰብዓዊነት! ለዜጋነት!

የካቲት 2011
ለማ ደስታ – ኦስሎ (ኖርዌይ)

Lemma Desta

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *