ከጉጂ ዞን ሻኪሶ ተነስቶ በቦረና ዞን ያቤሎ የተያዘው ወርቅ ግምቱ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ መሆኑን የኦሮሚያ ማዕድንልማት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ይርዳው ነጋሽ ገልጸዋል፡፡

ወርቁ በህገ ወጥ መንገድ ከአገር ሊወጣ ሲል በህብረተሰቡ ጥቋማ፣ በባለስልጣኑና በጸጥታ ኃይሎች ትብብር ኮድ 2 አዲስ አበባ በሆነች ፓትሮል መኪና ውስጥ በያቤሎ መጋቢት 15 ቀን 2011 ዓ.ም መያዙን ገልጸዋል።

በክልሉ በተለይ በሻኪሶ አካባቢ ወርቅ፣ ኤሜራልድና ሌሎች የከበሩ ማዕድናት በህገ ወጥ መንገድ የሚዘዋወሩ መሆኑን ጠቁመው ህብረተሰቡ በንቃት በመከታተል ለሚመለከተው አካል ጥቆማ እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል።

ህገ ወጥ ደላሎች ከመንግስት መዋቅር ጋር በመመሳጠር የከበሩ ማዕድናትን ጨምሮ የተለያዩ ህገ ወጥ የእቃ ዝውውሮችን በማድረግ ላይ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በተለይ በአዲስ አበባ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዮ ዞኖች እንዲሁም ምስራቅ እና ምዕራብ ሸዋ አካባቢ በህገ ወጥ መንገድ ለግንባታ ግብዓት የሚውሉ ማዕድናት እየወጡ መሆኑን ተናግረዋል።

በእነዚህ አካባቢዎች የሚገኙ ደላሎች ያለምንም ደረሰኝ ማዕድናቱን በማውጣት በህገ ወጥ መንገድ እየሸጡ በመሆኑ ባለስልጣኑ እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

በዚህም በአሽከርካሪዎች፣የአሽከርካሪ ባለቤቶች እና ማዕድኑን ያለደረሰኝ በሚገዙ ግለሰቦች ላይ በቀጣይ እርምጃ እንደሚወሰድ ገልጸዋል።

ያለምንም ደረሰኝ በግዥ የሚሳተፉ አካላትን ህብረተሰቡ ለጸጥታ አካላት፣ በየደረጃው ለሚገኘው የባለስልጣኑ ተቋማት ጥቆማ እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል።

በክልሉ የሚገኙ ወጣቶች ከ300 በላይ በሚሆኑ ማህበራት ተደራጅተው አነስተኛ ማዕድን በማውጣት ስራ ላይ መሰማራታቸውን ኢንጅነር ይርዳው በዚሁ ወቅት ተናግረዋል።

በኦሮሚያ ክልል 76 ተቋማት ከፌዴራል መንግስት ማዕድን የመፈለግና የማውጣት ፍቃድ የወሰዱ ሲሆን÷ በስራ ላይ ያሉት ግን ጥቂት መሆናቸውም ተገልጸዋል።

ምንጭ፡- ኢ ዜ አ

 መጋቢት 16፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ)

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *