በጣርማበር ወረዳ አንዲት በቅሎ ወለደች።

በአማራ ክል ሰሜን ሸዋ ዞን በጣርማበር ወረዳ በመዘዞ ንኡስ ወረዳ ኮሶበር ቀበሌ አንዲት በቅሎ መውለዷን የወረዳው መንግስት ኮምዩኒኬሺን ጉዳዮች ፅ/ቤት አስታወቀ፡፡

ፅ/ቤቱ እንዳስታወቀው የበቅሎዋ ባለቤት አቶ ሙላት ሃ/ሚካኤል በቅሎዋን በ2009 ዓ/ም በመግዛት ሲገለገሉባት እንደቆዩና ግቷ ሲጨምርም ህመም መስሏቸው እንደነበር ተናግረው መጋቢት 21/2011 ዓ.ም ከሌሊቱ 8፡00 ሰዓት አካባቢ መውለዷን ተናግረዋል፡፡

ሁኔታው አዲስ እንደሆነባቸው የገለጹት አቶ ሙላት የዚህ አይነቱ ክስተት ታይቶ እንደማይታወቅና በአሁኑ ሰዓት እናትና ልጅ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

የቀበሌው ዋና አስተዳዳሪ አቶ መርድ ተከለሃይማኖት በበኩላቸው በቅሎዋ ቀደም ሲል የእርሳቸው እንደነበረችና እንደሸጧት ገልፀው ሁኔታው አዲስ መሆኑንና በቅሎ አትወልድም የሚባለውን የሚሽር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በጫንጮ ወረዳ የእንስሳት ጤና ባለሙያ የሆኑት አቶ ግርማ ጅሬኛን ይህ ነገር እንደምን ሆነ ? ሲል በስልክ አነጋግሯል፡፡

አቶ ግርማ ጅሬኛ በሳይንሱ ይህ ክስተት ሊያጋጥም ይችላል የሚችል የሚል መላምት እንደሌለና በቅሎ ያላት ሃብለበራሂ /Chromosome/ ነጠላ በመሆኑ መውለድ የምትችልበት አጋጣሚ የለም፤ ይህ ለሳይንሱም አዲስ ክስተት ነው ብለዋል፡፡

ከዚህ በፊትም በግንቦት ወር 2009 ዓ.ም በደቡብ ወሎ ዞን ከላላ ወረዳ ማርጢቆስ ቀበሌ አንዲት በቅሎ ፈረስ መውለዷ የሚታወስ ነው፡፡

ኢ.ፕ.ድ በድልነሳ ምንውየለት

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *