(ፍሬው አበበ)

እ.ኤ.አ በ2017 በኬንያ ከተካሄደው ምርጫ ጋር በተያያዘ ፖሊስ ስምንት ያህል የምክርቤት እንደራሴዎችን አንጠልጥሎ ዘብጥያ አወረደ፡፡ ፖሊስ ሰዎቹን ለማሰር የበቃው የጥላቻ ንግግር አድርገዋል በሚል ወንጅሏቸው ነበር፡፡ በወቅቱ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት አንዱ የሌላውን ጎሳ(ዘር) የማጥላላት ዘመቻ ስለማካሄዱ ፖሊስ በቪዲዮ የተደገፈ ማስረጃ አለኝ ብሏል፡፡ በኬንያ ዘርና ጎሳን የሚያጥላላ የጥላቻ ንግግር ማድረግ በሕግ ደረጃ ክልከላ የተጣለበት የወንጀል ድርጊት ነው፡፡ እናም በኬንያ የአፍ ወለምታ ለእስር እና ለማህበረሰባዊ ውግዘት ይዳርጋል፡፡

በአንድ ወቅት በርካታ አይሁዶች በጀርመንና ሌሎች አገሮች በተሻለ ኑሮ ይመሩ ስለነበር እንደ ባለጠጋ ጥገኛ ተሕዋስያን (Wealthy parasite) ተደርገው ተሳሉ፡፡ ጥቂት የማይባሉ ጀርመናዊያን (የናዚ አገዛዝ) በወቅቱ ከሌሎች የላቁ እንደሆኑ ራሳቸውን መቁጠር መጀመራቸው ውሎ አድሮ ወደ ስድስት ሚሊየን የሚጠጉ አይሁዶች ላይ ዘግናኝ ግፍን ወደመፈጸም አሻገራቸው፡፡

በአንድ ወቅት በሩዋንዳ ሁቱዎች፣ ለቱትሲዎች ያላቸውን ጥላቻና ንቀት ለመግለጽ “በረሮ” ብለው እስከመጥራት ደርሰው ነበር፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ማህበረሰብ የሚያንቋሽሽ የጥላቻ ንግግር አጠራሩንም አንዱ ቡድን በጅምላ ተቀብሎ አጽድቆታል ማለት ነው፡፡ ይህ ዓይነቱን ፍረጃም ይሁን ስያሜ መነሻው እውነት እንዲሆን አይጠበቅም፡፡ ሕዝቡም ሲጋራው በምክንያታዊነት አስቦና አሰላስሎ አይደለምና፡፡

በርማ ወይም በአዲሱ ስሟ ማይናሚር በቅርቡ ወደ አንድ ሚሊዮን አካባቢ የሆኑ የአንድ ጎሳና እምነት ተከታዮችን በጥላቻ ቅስቀሳ መነሾ ለማጥፋት ሲሞከር ማየት በ21ኛው ክፍለዘመን አሳዛኝ ክስተት ነበር። ይህ በደል የደረሰባቸው “ሮሂንጊያ” በሚል ስም የሚጠሩት የአገሪቷ ሙስሊም የአንድ ጎሳ አባላት ነበሩ።

ሮሂንጊያዎች፣ በምዕራባዊው የበርማ (ማይናሚር) ጠረፍ የሚኖሩ ፣ ብዛታቸው አንድ ሚሊዮን አካባቢ የሚጠጋ ማህበረሰቦች ናቸው። ቋንቋቸው ከስማቸው ጋር ተመሳሳይ ነው። በበርማ በስፋት ከሚነገር ቋንቋም አንዱ ነው።

በርማ የራሷን ነጻነት ተቀዳጅታ፣ ራሷን የቻለች አገር ከሆነች ጊዜ ጀምሮ ግን የሮሂንጊያዎች ፍልሰት ጥያቄ ምልክት ውስጥ ገባ። “የኛ ወገን አይደሉም ፣ ወደመጡበት ይመለሱ” የሚል ዘመቻና የጥላቻ ቅስቀሳ ተጀመረ። እናም ለነዚህ ማህበረሰቦች ዜግነት ተከለከለ። ያን ጊዜም በይፋ “አገር የለሽ ማህበረሰቦች” ሆኑ።

ከዚህ የ1948 የበርማ ነጻነት በኋላ ጥቂት ዓመታት ቆይቶ፣ በበርማ ግዛት ቢያንስ ሁለት ትውልድ ያህል የቆዩ ሮሂንጊያዎች ካሉ ዜግነት ይሰጣቸዋል ተባለ፣ ዜግነትም አግኝተው፣ አንዳንዶቹ ለፓርላማ እስከመመረጥ ድረስ ደረሱ።

በ1962 ዓ.ም በበርማ ወታደሮች መፈንቅለ መንግሥት አድርገው ሥልጣን ያዙ። ያን ጊዜ ሁሉም የአገሪቷ ዜጎች ልዩ መታወቂያ እንዲያወጡ ህግ ወጣ። በአገሪቷ 135 ጎሳዎች አሉ ተብሎም ተደነገገ፣ ያን ጊዜ ሮሂንጊያዎች እንደ ጎሳ ፣ አንድ ተብለው ሳይቆጠሩ ሆን ተብሎ ተዘለሉ። “እንዳያማህ ጥራው ..እንዳይበላ ግፋው” እንዲሉ፣ ከ1948 ዓ.ም በፊት እዚህ የበርማ ግዛት ውስጥ ይኖሩ እንደነበር የጽሁፍ ማስረጃ ካመጡ ዜግነት ይሰጣቸዋል ተባለ። ነገር ግን ማንም የዚያን ጊዜ ነዋሪነት መታወቂያ ወይም ማስረጃ በጽሁፍ ማግኘት እንደማይችል ግልጽ ነበር፡፡

በዚህ የተነሳ ሮሂንጊያዎች መስራት፣ መማር፣ መንቀሳቀስ ወዘተ. አቃታቸው። ያለ አገር ፣ ዜጋ የለሽ ሆነው ቀሩ። በ1970 ዓመተ ምህረት ፣ በርማን ከሮሂንጊያዎች ማጽዳት የሚመስል ዘመቻ ተጀመረ። ብዙ ሺህ የሚሆኑትም ወደ ባንግላዴሽና ማሌዢያ ተሰደዱ። ብዙ ስቃይ ደረሰባቸው።

በ2016 ዓ.ም የሮሂንጊያዎች መኖሪያ በሆነው ፣ ራኪን የተባለ ግዛት ውስጥ፣ ስድስት ፖሊሶች ተገደሉ ተብሎ ፣ ግዛቱ በፖሊሶችና ወታደሮች ተወረረ። ያን ጊዜ በሮሂኒጊያዎች ላይ እጅግ ዘግናኝ ዕልቂት ደረሰ። መደፈር፣ መደብደብ፣ መገደል ተራ ነገሮች ሆኑ።

ወይዘሮ አውንግ ሳን ሱ ኪ ፣ በበርማ ላደረገችው ትልቅ የሠላማዊ ትግል ተጋድሎ፣ከ20 ዓመታት በላይ በእስር ቤት ለከፈለችው መሰዋዕትነት፣እ.ኤ.አ በ1991 የኖቤል የሠላም ሽልማት አሸናፊ መሆኗ ይታወሳል። በወቅቱ ትልቅ ሥልጣን እጇ ላይ ባይኖርም፣ ከበርማ መሪዎች አንዷ ሆና ትቆጠራለች፡፡ ታዲያ ይህ ሁሉ መከራ በነዚህ ምስኪኖች ላይ ሲደርስ ለምን ዝም አለች? በሚል ትልቁ ዘመቻ እሷ ላይ ሆኗል። ወታደሮቹን ለማስቆም ሥልጣን ባይኖራትም፣ ቢያንስ ድርጊቱን በአደባባይ ማውገዝ አለመቻሏ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ፊቱን እንዲያዞርባት ምክንት ሆኗል፡፡ የዘረኝነት ጥግ ምን ያህል አስቀያሚ መሆኑን ማየት አስችሏል፡፡

የጥላቻ ንግግር ምንድነው?

የጥላቻ ንግግርን ምንነት በተመለከት ቁርጥ ያለና ወጥ ብያኔ የለም፡፡ ይሁን እንጂ በርካታ ብያኔዎች የሚጋሯቸው ነጥቦች አሉ፡፡ በመሆኑም ማንኛውም የዘር ጥላቻን፣ የሌላ አገር ዜጋን ወይንም ስደተኛን በጭፍኑ መጥላትን፣ ፀረ ሴማዊነትን፣ ትዕግሥት አልባና አግላይ የሆነ ብሔርተኝነትን፣ ቁጥራቸው አነስተኛ የሆኑ ብሔረሰቦችን ሰበብ እየፈለጉ መገለል እንዲደርስባቸው የሚሰብኩ፣ የሚያሠራጩ፣ የሚያነሳሱ፣ የሚያበረታቱና ትክክል እንደሆኑ ለማስረዳት የሚደረጉ ጥረቶች የያዙ ቃላዊ ገለጻዎች፣ ጽሑፎች፣ ምሥሎችና ሥዕሎች፣ ቅርጻ ቅርጾች በሙሉ የጥላቻ ንግግር ይሰኛል፡፡ ስለሆነም የጥላቻ ንግግር ሲባል ድምፅን፣ ጽሑፍን፣ ምሥልን፣ ቅርፃ ቅርፅን፣ የድምፅና ምሥል ቅንብሮች፣ ካርቱኖችን… ያካትታል፡፡

የጥላቻ ንግግር አድራጊው የተለያዩ ቡድኖችን ባላቸው ማኅበራዊ መሠረትና አቋም ወይንም ርዕዮተ ዓለምም ላይ በመመርኮዝ እነዚህ ቡድኖችን በጥቅል ወይንም በተናጠል አባሎቻቸውን መገለልና መድልኦ እንዲደርስባቸው ማድረግ ነው፡፡ እንደ አይሁዶች፣ ቱትሲዎች፣ ጂፕሲዎች፣ የአውስትራሊያ ነባር ሕዝቦች ብሔርን መሠረት ሊያደርግ ይችላል፡፡ በበርካታ አውሮፓና ሌሎች አገሮችም እንደሚፈጸመው ሃይማኖታዊ መነሻ ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ቀለም ላይ የተመሠረት ጥቁሮች ላይ እንደደረሰው ሊሆን ይችላል፡፡ የጥላቻ ንግግር ውጤቱ ከማኅበራዊ ተቋማት ኢኮኖሚያዊ መስክ እንዲገለሉ ወይንም እንዳይሳተፉ ማድረግ ሲከፋው እንዲገደሉ ሊያደርግ ይችላል፡፡

በአጭሩ ዘርን፣ ብሔርን፣ ሃይማኖትና እንደ ስደተኛነት ያሉ ማኅበራዊ መሠረቶችን ምርኩዝ አድርጎ የሚፈጸሙ ንግግሮች ከጥላቻ እስካልጸዱ ድረስ ወይንም ጥላቻ ካዘሉ የጥላቻ ንግግር ይባላሉ፡፡ ሕግም ሲወጣ ይኼንኑ ለመከልከል ነው፡፡ ተናጋሪውንም፣ ጥላቻን ያዘለ ንግግር ካደረገ የወንጀል ኃላፊነት እንዲኖርበት ያደርጋል፡፡ ይሁን እንጂ የጥላቻ ንግግርን በቀላሉ መለየት አዳጋች ነው፡፡ አዳጋችነቱ የንግግሩ ሰለባ ለሆነው አይደለም፤ ለሌላ ወገን እንጂ በማር የተለወሰ ንግግር ሆነው የሚቀርቡ አሉ፡፡ ለምሳሌ፣ ቅኔያዊ ንግግሮች ይሆኑና ስናነባቸው ወይንም ስንሰማቸው ወይንም ስናያቸው በአንዴ የማናስተውላቸው አሉ፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹን፣ ከአውሮፓዊው የሕግ አተረጓጎም ልማድ የሚያሳየን በዚህ መጠን የንግግር ነፃነት መገደብ ተገቢ አይደለም በሚል ምክንያት የሚያስቀጡ አለመሆናቸውን ነው፡፡ ይሁን እንጂ ጥላቻ የሌላቸው መሆናቸውን አያሳይም፡፡

የጥላቻ ንግግር “Hate Speech” ሲባል አገላለፁ በቀጥታ ከአንደበት ወይም ከንግግር ጋር የተያያዘ ይመስላል እንጂ በውስጡ በርካታ ጥቅል ሀሳቦችን የያዘ መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ ትንታኔው በጥልቀት ሲመረመር የጥላቻ ንግግር (Hate Speech) መገለጫው አንድን ማህበረሰብ ወይንም ግለሰብ ለማጥቃት ለማሸማቀቅና ለማግለል በማሰብ በንግግር፣ በምስል ፣በፅሁፍ፣ በካርቱን፣ በቅርፃ ቅርፅና በልዩ ልዩ ምልክቶች ተደግፎ ጥላቻን ማሰራጨት ማለት ነው፡፡ ጥላቻው የሚሰራጨው ከግለሰቡ ወይንም ከማህበረሰቡ ዘር፣ ማንነት፣ የቆዳ ቀለም፣ ሀይማኖት፣ ዜግነት፣ ፆታና የጤንነት ሁኔታ ጋር በተያያዘ ሊሆን ይችላል፡፡

የጥላቻ ንግግር እንደአገር ያሰጋናል?

የፌደራል መንግሥት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይም ማህበራዊ ሚዲያዎችን በተመለከተ የያዘው ጠንካራ አቋም በሚዲያዎቹ በሚንጸባረቁ የጥላቻ ንግግሮች እና የአክራሪ ዘረኝነት ምልክቶች መሰላቸቱን የሚጠቁሙ ናቸው፡፡ በተለይ ማህበራዊ ድረገጾች የጥላቻ ንግግርን እያስፋፉ ስለመሆኑ በተደጋጋሚ ስሞታ የሚያቀርብበት ርዕሰ ጉዳይ ሆኗል፡፡ በቅርቡ ጠ/ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ለማህበራዊ ድረገጽ ሥርዓትና ሕግ ለማበጀት ከፌስቡክ ኩባንያ ጋር መንግሥት ንግግር መጀመሩን የጠቆሙበት አንዱ መነሻ የጥላቻ ንግግር እና የአክራሪ ብሔርተኝነት መንሰራፋት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡

ይህም ሆኖ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ በድረገጽ የሚቀርቡ ጽሑፎች ያላቸውን የጥላቻ ንግግር (Hate speech) ባህርይና የጥላቻ ንግግሮቹን መጠን ጉዳዩ ያደረገው በአዲስ አበባና በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ጥምረት የተሰራው ጥናት ውጤት ታትሞ በቅርቡ ለንባብ በቅቷል። ይህም የጥናት ውጤት የድረገጽ አጥቃቀምን በተመለከተ ገደብ የሚያስቀምጥ ፖሊሲና ሕግ ለማውጣት ለሚጣደፈው የኢትዮጵያ መንግስት የሚጠቁመው ነገር የንግግር ነፃነትን ለመገደብ የሚያበቃ እዚህ ግባ የሚባል የአደገኛ ንግግር (Dangerous speech) ተግዳሮት አለመኖሩን ነው።

“መቻቻል” በሚል አጠቃላይ ርዕስ የቀረበው ይህ ጥናት ከ 2007 ምርጫ ጀምሮ ለሁለት ዓመት የነበረውን የማኅበራዊ ድረ ገጾች የፖለቲካ ውይይትና ክርክር የሚዳስስ ነበር። ጥናቱ ለ ሁለት ዓመት በቆየው በዚሁ የጥናት ጊዜ ውስጥ የነበሩትን ፖለቲካን፥ ሐይማኖትንና ብሔርን የተመለከቱ የማኅበራዊ ድረገጽ ውይይቶች የዳሰሰ ነበር። የጥናቱም ትኩረት በሶስት ክፍል የተመደቡ የማኅበራዊ ድረገጽ አስተያየቶችና ንግግሮች ነበሩ። ተሳዳቢ(offensive) ፥ ጥላቻ አዘልና (hateful)፥ አደገኛ (dangerous) በሚል መደብ የተመደቡትን እነዚህን አስተያየቶች የገመገመው ጥናት አደገኛ በሚል ክፍል ሊመደብ የሚችለው የፌስቡክ አስተያየት መጠን በመንግስት እንደሚነገረው የተጋነነ ሳይኾን ከአጠቃላይ ውይይቱ 0.3 % ብቻ ያህል እንደኾነ አሳይቷል። ከዚህም በላይ እነዚሁ አደገኛ የሚባሉት ንግግሮችና አስተያየቶች የጽንፈኝነት ጥግ ነክተው እንኳን ግጭት ለመቀስቀስ በሚያበቃ ስጋት የማይፈጥሩ መኾናቸውን አሳይቷል።

ጥናቱ በዳሰሳቸው የኢትዮጵያውያን የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ባህርያት ውስጥ ቀደም ሲል በብዙዎች ዘንድ ያለጥናት በግምት ብቻ ተወስደው የነበሩ አመለካከቶችን የሚቃረኑ አዲስ ግኝቶችን አሳይቷል። ከነዚህም መካከል የጥላቻና አደገኛ ንግግሮች በሚል የተመደቡት የማኅበራዊ ድረ ገጽ በተለይም የፌስቡክ መልዕክቶች ያላቸውን መጠን የተመለከተው ውጤት ነው። በዚህም ጥናት መሰረት ከዚህ በፊት ተጋነው ይታሰቡ የነበሩት ጥላቻና አደገኛ ንግግር ያዘሉ የፌስቡክ መልዕክቶች መጠን እንደሚታሰበው ብዙ አለመኾናቸውን ማሳየቱ ነው። በነዚህ ሁለት መደቦች የተመደቡት የንግግር አይነቶች በታዋቂ ሰዎች ላይ ከሚሰነዘሩ ትችቶች አንስቶ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እስከመደገፍና መቃወም እንደዚሁም የሐይማኖትና የብሔር ልዩነቶችን የተመለከቱ ንግግሮችን የያዘ ነው።

ጥናቱ ይህን ይበል እንጂ፤ በተለይ እንደፌስቡክ ባሉ የማህበራዊ ድረገጾች አንድን ቡድን፣ ብሔር የሚያንቆለጻጵሱ፣ የሌላውን ብሔር ዝቅ የሚያደርጉ፣ የሚዘልፉ፣ የሚያዋርዱ ከፋፋይ አጀንዳዎች የመራመዳቸውን እውነትነት መካድ አይቻልም፡፡ የዚህ እኩይ ድርጊት አራማጆች በተለይ ባለፉት ሶስት ዓመታት በኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝብን በጅምላ ያፈናቀሉ የብሔር ግጭቶች እንዲስፋፉ ጭምር የማይናቅ ሚና እንደነበራቸው በብዙዎች ዘንድ የሚታመን ነው፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ የአክራሪ ብሔርተኝነት አጀንዳ እንዲስፋፋ ከጀርባ ሆነው ስፖንሰር የሚያደርጉ፣ የሚገፉ የፖለቲካ ኃይሎች የመኖራቸው ጉዳይ የችግሩን አሳሳቢነት አጉልቶ የሚያሳይ ነው፡፡

አዲስ ሕግ ያስፈልጋልን?

ኢትዮጵያ ከአሁን በፊት ስለሰብዓዊ መብት አፈጻጸሟ ሪፖርት ስታቀርብ በተሰጣት ግብረ መልስ ውስጥ የጥላቻ ንግግርን ወንጀል ማድረግ አንዱ ነበር፡፡ በበጎም ተቀብላው ነበር፤ ምንም እንኳን ሕግ ማውጣቱ ላይ እመርታ ባታሳይም፡፡ ስለምን ሕግ ያስፈልገናል ብንል በርካታ ምክንያቶችን ማንሳት ይቻላል፡፡ የጉዳዩ አሳሳቢነትም መንግሥትም የተረዳው ይመስላል፡፡ በቴሌቪዥን የተለያዩ ፕሮግራሞች ሲቀርቡ ተመልክተናል፡፡ በተለይ ደግሞ በማኅበራዊ ሚዲያ ስለሚተላለፉና ስለሚሠራጩ የጥላቻ ንግግሮች፡፡ ይሁን እንጂ ይህንን ከሚያስፋፉት ውስጥ አንደኛው መንግሥት ራሱ እንደሆነ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ አንዱን የመንግሥት አድራጎት ብቻ እንመልከት፡፡ እሱም መንግሥታዊ ፍረጃን ይመለከታል፡፡ እርግጥ ነው፣ ፍረጃ የአገራችን መለያ ከሆነ ቆይቷል፡፡ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን “የዓረብ ቅጥረኞች”፣ በደርግ “ገንጣይ፣ አስገንጣይና ወንበዴዎች”፣ በኢሕአዴግ ደግሞ “ነፍጠኛ፣ ትምክህተኛና ጠባብ..” የሚሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዓላማው አሁን ያለው የአገራችንን ሁኔታ ስለሆነ ጠባብ፣ ትምክህተኛና ነፍጠኛ የሚሉትን ቃላት ብቻ እንደ ምሳሌ ይወስዳል፡፡ ስለሆነም እነዚህ ስያሜዎች ከጥላቻ ንግግር አንፃር በአጭሩ ለማየት ይሞክራል፡፡ የሁለቱን ትርጉም ኢሕአዴግ ካወጣቸው ሰነዶች በመነሳት እናስቀምቸጣው፡፡

ጠባብ ብሔርተኝነት ወይንም ጠባቦች የሚባሉት ሌሎች ብሔር፣ ብሔረሰቦችን በጭፍን በጠላትነት የሚያዩ ሲሆኑ፣ አብሮ የመኖር ጥያቄን ፈጽሞ የማስተናገድ ፍላጎት የሌለው ተደርገው ይቆጠራሉ፡፡ ትምክህተኛ ብሔርተኝነት ወይንም ትምክህተኞች የሚባሉት አመክንዮታዊነት በጎደለውና ከልክ ባለፈ ሁኔታ የራስን ብሔር፣ ቋንቋና ባህል ከሁሉም በላይ ልዕልና እንዳለው የሚያምን፣ ከዚህ ባለፈም ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች የራሳቸውን ማንነት በመካድና በመተው ትምክህተኛውን ብሔር የበላይ ነው ብለው እንዲያምኑና ያንን ማንነት እንዲላበሱ የሚፈልግ የብሔርተኝነት ዘውግ ነው፡፡

ከእነዚህ የብሔርተኝነት ዓይነቶች ኢሕአዴግ የሚዋጋቸው እንደሆኑ ይገልጻል፡፡ በዋናነት እነዚህ የብሔርተኝነት ዓይነቶች ለሁለት የብሔር የተሰጡ ስያሜዎች እንደ ይታወቃል፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ ተበደለ የሚሉትን “ጠባብ”፣ የአማራ ሕዝብ በዚህ በዚህ ቦታ ችግር እየደረሰበት ነው የሚሉትን “ትምክህተኛ” እያሉ መፈረጅ የዕለት ተዕለት ሥራ ሆኗል፡፡ እንዲህ ዓይነት የመፈራረጃ ሐሳቦች ግልጽና የማያወላዱ መለያ ባሕርያት ስለሌላቸው ከመሬት ተነሥቶ ለመኮነንና ለመውቀስ ቀላል ናቸው፡፡ እነዚህ ፍረጃዎች፣ ሰብዓዊ ክብርን የሚነኩ መሆናቸው የሚያወላዳ አይደለም፡፡ የሰፊነት ወይንም መለኪያ በሌለበት የብሔሩን መብት የጠየቀን ኦሮሞ ሁሉ ጠባብ ማለት ዞሮ ዞሮ ኦሮሞ ስለሆነ የሚመጣ ንግግር ነው፡፡ የተለያዩ ዜግነትን መሠረት ያደረጉ መብቶች የሚጠይቅን አማራ ሁሉ ትምክህተኛ ማለት አማራ ከመሆኑ የሚመነጭ ነው፡፡ ስለሆነም ጥላቻን የሚሳድግና የሚያበረታታ ነው፡፡ ይህ ስለመሆኑ ለማረጋገጥ ደግሞ ኦሮሞን በአማራ ዘንድ እንዴት እንዲሳል እንደተደረገ ማወቅ ይበቃል፡፡ አማራም በኦሮሞ ዘንድ እንዲሳል የተደረገውም ተመሳሳይ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱን አካሄድ ለማስቀረት እነዚህን ወደ ብሔር ያጋደሉ ፍረጃዎችን እንደ ጥላቻ ንግግር በመውሰድ ወንጀል ብናደርጋቸው የተሻለ ይሆናል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት የጥላቻ ንግግር እና የዘረኝነት ዝንባሌዎች በተለይ በማህበራዊ ድረገጾች እየተስፋፋ መምጣት በአያሌው አሳስቦታል፡፡ እናም ይህን ወደአስከፊ ማህበራዊ ቀውስ ሊያስገባ የሚችለውን ጅምር ለመቅጨት የሕግ ድንጋጌ አስፈላጊነት አምኖበታል፡፡ በዚህም መነሻ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የጸረ ጥላቻ ንግግር አዲስ ረቂቅ ሕግ እያዘጋጀ መሆኑን ከሰሞኑ ይፋ አድርጓል።

በማህበራዊ ሚዲያዎች እየተስፋፉ የመጡት ኃላፊነት የጎደላቸው መልዕክቶችና የሐሰት ወሬዎች በሀገሪቱ ለሚከሰቱ ግጭቶች ምክንያት በመሆናቸው መንግስት ይህን አደጋ ለማስወገድ ሕጋዊ ተጠያቂነት እንዲኖር የሚያስችል አሠራር በማርቀቅ ላይ ነው።

በተለይም ለሕዝብ የሚቀርቡ ንግግሮችና የሚተላለፉ መልዕክቶችን በተመለከተ ኃላፊነትና ተጠያቂነት ማስፈን የሚወጣው ሕግ ጥቅም እንደሚኖረው ታምኖበታል፡፡

ሆኖም እየተረቀቀ ያለው ረቂቅ ሕግ ያካተተው ዝርዝር ጉዳይ ለጊዜው ባይታወቅም፣ ድንጋጌዎቹ ሃሳብን በነጻ ከመግለጽ ሕገመንግሥታዊ ነጻነት አንጻር የቱን ያህል የተጣጣመ ነው የሚለው ዝርዝር ጉዳይ ወደፊት የሚታይ ይሆናል፡፡ የዚህ ሕግ ራሱን ችሎ መውጣት ግን ምናልባትም የአደባባይ የጥላቻ ንግግርና እሱን ተከትሎ የሚመጣውን የአክራሪ ብሔርተኝነት አጀንዳ በሕግ ሥርዓት ለማስያዝ፣ የተጋረጠብንንም አገራዊ አደጋ ለመቀልበስ እንደሚረዳ በብዙዎች ዘንድ ታምኗል፡፡ (የጸሐፊው ማስታወሻ፡- ለዚህ ጹሑፍ ጥንቅር፡- አቢሲኒያ ሎው ድረገጽ (ውብሽት ሙላት)፣ ጀርመን ድምጽ፣ አልጀዚራ፣ አርትስ ቲቪ፣ ኢዜአ፣ ዋዜማ ራዲዮ፣ Cambridge English Dictionary, Merriam- Webster Dictionary, Wikipedia… በግብዐትነት ተጠቅሜያለሁ)

(ይህ ጹሑፍ አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 21/2011 ታትሞ ለንባብ የበቃ ነው)

www.facebook.com/1623081827/posts/10217038316183084

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *