የቃጠሎው መነሻ ምክንያት በውል ያልተነገረለትና አገር ወዳድ ወገኖችን ከንፈር እያስመጠጠ ያለው የሰሜን ፓርክ ብሄራዊ ፓርክ ቃጠሎ አሁንም መፍትሄ አልተበጀለትም። በከፍተኛ ደረጃ እየወደመ ያለው ይህ ፓርክ እሳቱ ከተነሳበት ጊዜ ጀመሮ በአየር ለማጥፋት እንቅስቃሴ አለመጀመሩ አሳዛኝ ሆኗል። ይህ ወደር የማይገኝለት የአገር ሃብት እየወደመ እንቅልፍ የሚወስዳቸው ወገኖች ቢያሳፍሩም፣ በሚችለው ሁሉ እሳትን በመጋፈጥ ላይ ያለው ወገን ግን ክብር የሚሻው ነው።

የእሳት ማጥፊያ አውሮፕላን ወይም ሄሊኮፕተር ባለቤት አለመሆናችን ከሚፈጥረው ቁጭት በላይ ደኑ እየጋየ በውስጡ ያሉ ብርቅ እንስሶች እያለቁ አማራጭ መፍትሄ አለመገኝቱ ነው። አማራጭ መፍትሄ አለመገኘቱ እያነጋገረ ባለበት ወቅት ዛሬ የአማራ መገናኛ ብዙሃን ከኬንያ ሄሊኮፕተር  ለማስመጣት እየተሰራ መሆኑንን ገልጹዋል።

በፓርኩ ላይ የተነሳውን እሳት ማጥፊያ ሄሊኮፕተር ለማስመጣት በሂደት ላይ መሆኑን ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ። በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ላይ የተነሳውን እሳት ማጥፊያ ሄሊኮፕተር ከኬንያ ለማስመጣት በሂደት ላይ መሆኑን ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታውቋል።

ከኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመሆን ጉዳዩን ለማስፈፀም እየተሰራ መሆኑን በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የውጭና ዓለማቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ አባተ በተለይም ለአብመድ ተናግረዋል።

ኬንያ ፈቃደኛ መሆኗንና የእሳት ማጥፊያ ሄሊኮፕተሩን በቶሎ ለማስመጣትና ቃጠሎውን ለመቆጣጠርም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ከኬንያ መንግስት ጋር እየተነጋገሩ መሆኑንም አቶ ገዛኸኝ ነግረውናል። ሁሉም ፓርኩን በማዳኑ ስራ እንዲረባረብም ጠይቀዋል።

የኢፌዴሪ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን፣ የቱሪስት አስጎብኝ ድርጅቶች እና ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ፓርኩ ስለተጋረጠበት አደጋ አሁን አዲስ አበባ ላይ እየመከሩ ነው።

ከውይይቱ በኋላም በተቀናጀ መልኩ እሳቱን ለማጥፋት በሚያግዝ ኃላፊነት አደጋው ወደ ተከሰተበት ቦታ እንደሚሄዱ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን አስታውቋል። ሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ አሁንም እየተቃጠለ፤ ብዝሀ ሕይዎቱም ለአደጋ እየተጋለጠ ነው።

ፓርኩ ከ21 ዓመታት ለአደጋ የተጋለጡ የጎብኝ መዳረሻ ስፍራዎች መዝገብ ውሰጥ ቆይታ በኋላ “ከአደጋ ነፃ” ከተባለ ሁለት ዓመታት ሆኖታል። አሁን ደግሞ ተደጋጋሚ ቃጠሎ እየደረሰበት ይገኛል። ከሳምንት በፊት በተከሰተው እሳት ከ342 ሄክታር በላይ የፓርኩ ክፍል ላይ ጉዳት መድረሱ ይታወሳል።

ዘጋቢ፦ አስማማው በቀለ – አማራ መገናና ብዙሃን

ፎቶ፦ በደስታ ካሳ

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *