አንዳንድ ጊዜ ማመን እስከሚያቅት ድረስ አንኳር ሚስጢሮች በውስን ሰዎች በማህበራዊ ሚዲያ ሲሰራጩና ጉዳዮቹ በቀታይ ሲፈጸሙ እያየናቸው ነው። ይህ አሰራር መርጃውን የሚያሰራጩትን ውስን ወገኖች ” ጀግናና የበላይ” አስመስሎ እየሳላቸው ከመሆኑም በላይ ራሳቸውን መሪና ማን አለብኝ ስሜት ውስጥ እየከተቱ ነው። መረጃ ሆን ተብሎ እንዲራባ አስቀድሞ የሚሰጥበት አግባብ ቢኖርም፣ አሁን ያለው አሰራር ገደብ ካልተጣለለት ችግሩ የጎላ ሊሆን ይችላል።

በተለይም በአክቲቪስት ነነ ባዬች መካከል የትከሻ መለካኪያና  ” እኔ ልዩ ነኝ” የሚል ስሜት እየፈጠረ ስለመሆኑ መልክቶች አሉ። መቼም ሰው ነንና ይገባናል። አቶ ሙሼ ሰሙ ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ በፌስ ቡክ ገጹ ከነገው ጽሁፉ ላይ ቆንጥሮ የሚከተለውን ለጥፏል። ጉዳዩ አግባብ ያለውና መድረስ ለሚገባው አካል መድረስ ስላለበት ቀርቧል።

በሀገራዊ ወይም መንግስታዊ ሚስጥርና በሕዝብ መረጃ የማግኘት መብት መካካል ያለው ቀይ መስመር ተጥሷል፡፡ መረጃ ለማን፣ እንዴት፣ ለምን፣ እንደሚሰጥ የጠራ አሰራር እንደሌለ ይናፈሳል። በ “ውስጥ አዋቂ ነን” ባዮች አማካኝነት ፌስ ቡክ ላይ ከሚናኙት መረጃዎች አሳሳቢነት ለመረዳት እንደሚቻለው፤ መረጃዎቹ የሚናኙት ሕግንና ፕሮቶኮልን ጠብቀው ሳይሆን እንደዋዛ በመቀራረብና በመተዋወቅ ጭምር እንደሆነ ለመገመት አያዳግትም። በግልጽም የሚታይና ሊደብቁት የማይገባ እውነት ነው።

ፍርሃትና ስጋት በነገሰበት ማህበረሰብ ውስጥ በዚህ መልኩ የመረጃ ሞኖፖሊ ይዘው “ውስጥ አዋቂ ነን” የሚሉ አክቲቪስቶች፣ ግለሰቦችና ቡድኖች የሚያሰራጩት መረጃ ሁሌም ትክክለኛ ሆነው ባይገኙም መረጃዎቹ በሕዝቡ ውስጥ ያለውን የመረጃ ጥማትና ክፍተቶችን የሚሞሉ ናቸው። መረጃዎቹና ማስረጃዎቹ ማን እንደሚሾም፣ ከምርመራ በፊት ማን ላይ ምን ዓይነት ወንጀል እንደሚለጠፍ፣ እነማን እንደሚታሰሩና እንደሚታደኑ፣ ምን ዓይነት ግጭቶች እንደሚከሰቱ፣ ግጭቱን እነማን እንደሚመሩት፣ የግጭቱ ውጤቱ ወዴት ሊያመራ እንደሚችልና ግጭቱን የሚመሩት ኃይሎች እስከታጠቁት መሳርያ ድረስ በዝርዝር የሚዘልቁ ስለሆኑ የውስጥ አዋቂዎች፣ የአክቲቪስቶችና የፌስቡክ ተከታዮቻቸው ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ ከሚገመተው በላይ እንዲጨምርና ፌስቡክ ለኢትዮጵያውያን በቀዳሚ የመረጃ (Main stream) ምንጭነት እንዲታጭ እያደረጉት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡

ቀደም ባሉት ዓመታት የነበረውን ስርዓት (Order) ለመታገል ሲባል ለታማኝ ግለሰቦች፣ ለአክቲቪስቶች፣ ለውስጥ አርበኞች እና ለታዋቂ ሰዎች መረጃ በማሾለክ ትግሉን ማጧጧፍ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቶ ሊሆን ይችላል፡፡ ዛሬ ላይ ትግሉ ከሞላ ጎደል ተደምድሟል፡፡ አሸናፊው ኃይልም የሪፐብሊኩና የክልል መሪ ሆኗል፡፡ እናም ለትግሉ ሲባል መደበኛ ባልሆነ መልኩ መረጃን የማሾለክ አሰራር ከዚህ በኋላ ጥቅሙ ግልጽ አይደለም። ሊቆምም ይገባል።
መንግስትም መንግስት ነውና ፣ የመንግስትነቱም ሚስጢሩ የቃለ መሐላ ውጤትም በመሆኑ፣  ሚስጥሩን የሕይወት ዋጋ ጭምር በመክፈል መጠበቅ ግዴታው መሆኑን ሊዘነጋ አይገባም።

“አክቲቪስትም” ሆነ “ብሎገር” በዚህ መልኩ በመሞዳሞድ በሚያገኘው መረጃ ላይ ተመስርቶ ሁከትና ብጥብጥ እንዲሁም ልዩነትና ዘረኝነት ወይም የአንድ ወይም የሌላ ብሔር የበላይነትን እንዲያሰፍን ሊፈቀድለት አይገባም ”
“ስለ ሕግ ሳይሆን ስለ ሪፐብሊኩ አምላክ በሚል ርዕስ አዲስ አድማስ ላይ ቅዳሜ ከሚወጣ ጽሑፍ የተቀነጨበ” ሙሉውን ነገ ነገ ይመልከቱ።

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *