በሳምሶን ጌታቸው

እሳቱን ለማጥፋት የሚደረገው ርብርብ በሚቻለው ሁሉ መቀጠሉ የሚበረታታ ነው። በቀጣይነት ግን በሰሜን ተራሮች ላይ የተደቀነውን የጥፋት አደጋ ለመከላከልና የወደመውን መልሶ በፍጥነት ለመተካል ሶስት እጅግ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ትኩረት ተደርጎ ቢሰራ ጥሩ ሳይሆን አይቀርም።

አንደኛ ነገር በቀጣይም ሊፈፀሙ የሚችሉ ተመሳሳይ ጥፋቶችን ለመከላከል አካባቢው ከወትሮው የተለየ ከፍተኛና የተጠናከረ ጥበቃ እንዲኖረው ማድረግ ያስፈልጋል። ምክንያቱም ተደጋጋሚ የእሳት አደጋዎቹ አድራሾች ሃብቱን ሙሉ በሙሉ የማውደም ውጥናቸውን በጊዜ እያዘናጉም ቢሆን ከመሞከር ይተኛሉ ተብሎ ስለማይታሰብ ነው።

ስለሆነም በፍጥነት ለአካባቢው ዙሪያ ነዋሪዎች ከወትሮው ልዩ የሆነ የመከላከል ሥልጠና መስጠት ጠቃሚ ይሆናል። በተለይ ደግሞ በመረጃ-መገናኛ መሣሪያዎች እና በወታደራዊ ሥልጠናዎች የበቁና በመከላከያ ትጥቆች በተደራጁ ባለሙያዎች የሚመሩ ጣቢያዎችን በብዛትና በተጠና መልኩ ማቋቋም ያስፈልጋል። እንዲህ እንዳሁኑ አደጋ ሲደርስ የሰው ሀገር ደጅ ከመጥናት፤ ችሎታው ያላቸውን ሀገራት አስቀድሞ ዕውቀትና ልምዳቸውን በሥልጠና እንዲያካፍሉን እገዛቸውን ብንጠይቅ አደጋ ለመከላከልም ሆነ ከተከሰተ በኋላ በራስ አቅም ለመወጣት በብዙ መልኩ የተሻለና የሚደርሰውንም ኪሳራ የሚቀንስ ይሆናል።

ሁለተኛውና ሌላው መሠረታዊ ጉዳይ የወደመውን ደን፣ አካባቢው ላይ በነበረው የዕፅዋት ዝርያዎች ነገ ዛሬ ሳይባል መልሶ የመሸፈን ተግባር መጀመርና ማከናወን ተገቢ ነው። በእርግጥ ሳርና አነስተኛ ቁጥቋጦዎች ብዙ ጊዜ ከእሳት ቃጠሎ በኋላ ዝናብ ሲያገኙ በፍጥነት መልሰው ምናልባትም በተሻለ ሁኔታ በራሳቸው የማቆጥቆጥ ችሎታ ይኖራቸዋል። ነገር ግን በእሳት የወደሙትን የአካባቢውን ዛፎች፣ ዝርያቸውን ከተመሳሳይ አካባቢዎች በማፈላለግና በማራባት ከመጪው የዝናብ ወቅት ጀምሮ ለመተካት ከአሁኑ ጊዜ ሳይባክን፣ ችግኝ የማፍላት ፈጣን ዝግጅቶችን መጀመር ቢቻል ጥሩ ነው።

walya

ሶስተኛውና መረሳት የሌለበት ዋና ጉዳይ እሳቱ ሙሉ በሙሉ የዕፅዋት ውድመት ያደረሰባቸውና የእስሳቱ መኖሪያ አካባቢዎች እንዳሉ ተገልጿል። በመሆኑም እንስሳቱ በቀጣዩ የዝናብ ወቅት ተክሎቹ እስኪያቆጠቁጡና እስኪያገግሙ ድረስ ምንም አይነት የሚመገቡት ነገር አይኖራቸውም ማለት ነው። በተጨማሪም ከቀዳሚው አካባቢያቸው ሲሰደዱ የሚጠጡትም ውኃ አያገኙም ይሆናል።

ስለሆነም በተደጋጋሚ በሰደድ እሳት የሚጠቁት እንደ አውስትራሊያ እና የአሜሪካው ካሊፎርኒያ ግዛቶች ያሉ ሀገራት፣ በዚህ ዙሪያ ልምድ ስላላቸው ያን ተሞክሮ ለመኮረጅ ቢሞከርም ጥሩ ነው። ሀገራቱ በእሳት የተጠቁ አካባቢ መልሶ እስኪያገግም ከአደጋው የተረፉ እንስሳት በርሃብ እንዳያልቁ በተጠና መልኩ የምግብ እርዳታ እንዲያገኙ ያደርጋሉ። የሚጠጡትም ውኃ እንዳያጡ በጎድጓዳ እና ሰፋ ባሉ ዕቃዎች ያቀርቡላቸዋል። ይህንኑ ተሞክሮ የሰሜን ተራራ እንስሳትንም ለመታደግ ቢተገበር ጥሩ ነው። በአለም መተኪያ የሌላቸውን ብርቅዬ እንስሳት በምንም መንገድ ከምድረ ገፅ ጠፍተው እንዳይቀሩ የሚቻለውን ጥረት ሁሉ ማድረግና መረባረብ የዚህ ዘመን ትውልድ ኃላፊነት መሆኑ መረሳት የለበትም።

ሰብአዊ ቀውስ በተከሰተበት ሀገር ስለ ተፈጥሮ ሃብት፣ ስለ አራዊትና ደን መጨነቅ ቅንጦት ሊመስል ይችላል። ነገር ግን ከዛሬው ውጥንቅጣችን ስንወጣ የሀገራችን የተፈጥሮ ሃብቶች እንደተጠበቁ ማግኘት ካልቻልን፣ በብዙ መልኩ የተራቆተች፣ የራሷ መለያ ቀለምና ሃብት የሌላት ሌጣ ሀገር ትቀረናለች። ያኔ የቱንም ያህል ብንቆጭ ያመለጡንን ነገሮች አንመልሳቸውም። ስለሆነም ከሰብአዊ ቀውሳችን ለመውጣት ከምናደርገው ጥረት ጎን ለጎን ሰው ሰራሽ ቅርሶቻችንና የተፈጥሮ ሃብቶቻችንንም ከጥፋት ለመታደግ መረባረብ የዘመን ግዴታችን (ፍርጃችን) ነው። መንበርከክ አያስፈልግም።

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *