ፖለቲካና የፖለቲካ ልዩነት የተንጸባረቀበት የጽዳት ዘመቻ በተለያዩ ክልሎችና ከተሞች ተካሂዷል። ቆሻሻና ክርፋትን ለማጽዳት ትብብር የሌላቸው አካላት ነገ ሰኞ በሚደረገው የኢህአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ በአገሪቱ ጉዳይ ለመምከር ስብሰባ ይቀመጣሉ። ይህንን የታዘቡ አካላት ” የጠነባ የጤና ጠንቅ ቆሻሻ ለማጽዳት ህብረት የሌላቸው ድርጅቶች አገሪቱ የገባችበትን ቀውስ ለመፍታት አንድ ነን ብለው መሰባሰባቸው እንደ ዜጋ ተስፋ አስቆራጭ ቢሆንም፣ ጤናማ ዜጎች ልዩነታቸውን ወደ ሁዋላ በመተው ከመቼውም ጊዜ በላይ ህብረት ሊፈጥሩና የለውጥ ሃይሉን ለመደገፍ መነሳት እንዳለባቸው የሚያመላክት ነው” ብለዋል።

አንድ የማህበራዊ ድረ ገጽ አስተያየት ሰጪ ይህ አካሄድ ኢህአዴግ መበስበሱን የሚያሳይ መሆኑንን ጠቁሞ ” አማራጭ ድርጅት የሌላት አገር ነዋሪዎች መሆናችን እንጂ መጥረግ የነበረብን በሴራ ድር የሸተተውን ራሱን ኢህአዴግን ነበር” ብሏል።

የጠሚ/ር ዐቢይ አሕመድ መልእክት

“ጥሪ በተደረገዉ መሠረት በመላዉ ኢትዮጵያ ጠዋት ጽዳት ሲደረግ ቆይቷል። አብዛኛዉ ቦታ ላይ ያለዉ እንቅስቃሴ የሠመረ ነው። የሰፈርና የአእምሮአችንን ቆሻሻ እያጸዳን በንጹሕ ልቡና እና አእምሮ ሀገራችንን እናድስ። ሀገራችንን እንገንባ። እንደ ባሕል በየጊዜዉ እንዲቀጥል ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል እንድትቀጥሉበት እጠይቃለሁ። ዛሬ መዉጣት ያልቻላችሁ ከዚህ ትምህርት ወስዳችሁ ኃላፊነታችሁን እንደምትወጡና ባሕልእስኪሆን ድረስ እንደምታስቀጥሉት አምናለሁ። ወጥታችሁ ላጽዳችሁም ምስጋናዬን አቀርባለሁ::” 

Image may contain: 7 people, outdoor

የአዲስ አበባ ሕዝብ በዚህ መልኩ ነው ከተማውን ሲያጸዳ የዋለው

ከማለዳ ጀምሮ በሀገሪቱ የተለያዩ ከተሞች፣ መንገዶች እና ሰፈሮች የፅዳት ዘመቻ ተካሄደ። የትግራይ ክልል ካቢኔ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ መሰረት ጽዳት እንደማይደረግ የክልሉ የካቢኔ አባል መናገራቸውን ተቀማጭነታቸው መቀሌ የሆነ የማህበራዊ ሚዲያ አክቲቪስቶች ገልጸው ነበር።

ከጠዋት 1 ሰዓት ከ30 ጀምሮ በተካሄደው የፅዳት መርሃ ግብር በአዲስ አበባ ከተማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ መሪዎች በዘመቻው መሳተፋቸውን የመንግስት መገናኛዎች አመልክተዋል።

የጠቅላይ ሚኒስቴር ፅህፈት ቤት የምናጸዳው በክብርና በንጹሕ አከባቢ መኖር መብታችን እንደሆነ ስለምናምን ነው ። የምናጸዳው ለጤናችን ነው፤ ማጽዳትም ኃላፊነታችን ነውም ሲል ገልጿል።

ለኢትዮጵያ ጽዳት በአንድነት እንነሳ በማለት ጥሪ ያስተላለፈው ፅህፈት ቤቱ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ለአካባቢ ፅዳት በአንድነት መነሳት እንዳለባቸው ጠቁሟል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የፅዳት ዘመቻው መልካም አስተሳሰብን ለመስበክ እንደሚያግዝ ማስታወቃቸው የሚታወስ ነው፡

በጽዳት ዘመቻው እንደማይሳተፉ በይፋ ያስታወቀው የትግራይ ክልል ውሳኔ ፖለቲካዊ መሆኑ ታውቋል። በአብዛኛው ለፌደራል መንግስት መታዘዝና መገዛት ያቆመው የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር በካቢኔ አባሉ አማካይነት ጥሪውን እንደማይቀበል የገለጸው ጠቅላይ ሚኒስትሩን ካለማክበር የተነሳ መሆኑንን አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ።

ጃዋር መሐመድ በፌስ ቡክ ገጹ እነዚህ ሃይሎች ናቸው ነገ ሰኞ ” አንድ ነን” ብለው ለኢህአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ የሚቀመጡት ሲል አስተያየቱን አስፍሯል። የትግራይ ክልል መሪዎች በህግ የሚፈለጉትን በመሸሸግ፣ የመከላከያ ሰራዊትን ነጻ እንቅስቃሴ በማገትና በአገሪቱ በሚከሰቱና በተከሰቱ ቀውሶች ጀርባ ትልቁን ሚና የሚጫወት  እንደሆነ በተደጋጋሚ የሚከስስ መሆኑ ይታወቃል። ህወሃት ግን ይህንን ክስ አይቀበልም። ማስረጃ አልባ ውንጀላና የራስን ሃላፊነት ያለመወጣት ችግር ነው ሲል ያጣጥላል።

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *