አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 10፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ለቀድሞ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳና ለሌሎች ከፍተኛ ነባር አመራሮች የምስጋና እና የሽኝት ፕሮግራም ተካሄደ።

በአዳማ ከተማ በተካሄደው በዚህ መርሃ ግብር ላይ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፣ የትግራይ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳደር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል እና የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ተገኝተዋል።

በተጨማሪም ከፍተኛ የፌዴራል እና የክልል ባለስልጣናት የምስጋና እና የሽኝት መርሃ ግብሩ ላይ ተሳትፈዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በመድረኩ ላይ በመገኘትም በዛሬው እለት ለተሸኙ አመራሮች ምስጋና በማቅረብ፥ ለአዲሱ አመራርም መልዕክት አስተላልፈዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በመልዕክታቸው፥ አቶ ለማ መገርሳ የኦሮሞን ህዝብ ፖለቲካ ማነቃቃትና መቀየር የቻሉ ናቸው ሲሉም ተናግረዋል።

በተለይም የዛሬ ሁለት እና ሶስት ዓመት የኦሮሞን ህዝብ ትግልን ወደ አዲስ ምእራፍ በማሸጋገር ራሳቸውን መስዋእት ለማድረግ ዝግጁ የነበሩ መሆናቸውን በማንሳትም ዛሬ ደግሞ ለከፍተኛ የፌዴራል ሀላፊነት ታጭተዋል ብለዋል።

አዲስ በተሾሙበት የሀገር መከላከያ ሚኒስትርነት ስፍራም በሀገሪቱ የተፈጠረውን ችግር በአጭር ጊዜ በሀገሪቱ እንዲሁም በአፍሪካ አዲስ ታሪክ እንደሚያስመዘግቡ ሙሉ እምነት አለኝም ብለዋል።

በዛሬው እለት የተሸኙት ዶክተር ወርቅነህና ሌሎች አመራሮቸም ከዚህ ቀደም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ገልፀው፤ በቀጣይም በሚጠበቅባቸው ሀላፊነት ከፍተኛ ሚና አንደሚጫወቱ አምናለሁ ብለዋል።

አዲሱ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳም ከፍተኛ ሀላፊነት መረከባቸውን ገልፀው፤ ባላቸው ብቃትና ተነሳሽነት ከፍተኛ ውጤት እንደሚያስመዘግቡ እምነት እንዳላቸው ገልፀዋል።

በቀጣይ ጊዜያትም ወደ ህብረተሰቡ በተለይም ወደ አርሶ አደሩ በመውረድ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ እንዲያገለግሉም መልእከት አስተላፍዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን አሁን ያለንበት የለውጥ ጊዜ ነው፤ የሀገራችን ብልፅግና እውን የምናደርግበት ምእራፍ ላይ እንገኛለን ብለዋል።

አሁን ያለበት የለውጥ ምእራፍ ላይ ለመድረስ ብዙ ዋጋ ተከፍሎበታል፤ ለውጡ ብዙ ውጤት እያስመዘገበ ቢሆንም ተግዳሮቶች ገጥመውታል፤ በአንድነት በመሆን ተግዳሮቶቹን በማሸነፍ ለውጡን ማስቀጠል አለብን ብለዋል።

ይህንን ካደረግን ዜጎች የሚኮሩባት ሀገር መገንባት እንችላለን ነው ያሉት።

በዚህ ታሪካዊ ወቅት እንደ አቶ ለማ የለውጡ አነቃቂ በመሆን ለሀገራዊ ለውጡ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ፥ ለከፍተኛ ኃላፊነት ወደ ፌዴራል በመምጣታቸውን ደስታ ይሰማናል ብለዋል።

የኢፌዴሪ የሀገር መከላከያ ሚኒስትር በመሆን በዛሬው እለት ለተሾሙት አለቶ ለማ መገርሳም መልካም የስራ ጊዜ ተመኝተዋል።

ለኦሮሚያ ክልል ምክትል ርእሰ መስተደድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ባስተላለፉት መልእክተም ክልሉን መምራት ከፍተኛ ኃላፊነት መሆኑን ገልፀው፤ ከስራ ባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን ይህንን ሀላፊነት በስኬት እንደሚወጡም መልካም ምኞታቸውን ገልፀዋል።

በሀገሪቱ በተደረገ ከፍተኛ ትግል ለውጥ መምጣቱን አውስተው፤ አሁን ያለንበት ምእራፍም ከፍተኛ ትግል የሚጠይቅ ነው ብለዋል።

ከቀድሞ አመራሮች ትምህርት ልንቀስም ይገባል ያሉት አቶ ሽመልስ፥ ይህንን ካደረግን ራእያቸውን በማሳካት ለተተኪ ትውልድ ቦታ እየለቀቅን መሄድ እንችላለን ሲሉም ተናግረዋል።

ከነባር አመራሮች የተቀበልነውን አደራ ከግብ ለማድረስ በአንድነት በመሆን በከፍተኛ ቁርጠኝነት መስራት ይጠበቅብናል ሲሉም ገልፀዋል።

የትግራይ ክለል ምክትል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል በበኩላቸው፥ ዛሬ የተገኘንበት የስልጣን ሽግግር መርሃ ግብር ላይ ነው ብለዋል።

አቶ ለማ መገርሳ የኦሮሚያ ክልልን በርእሰ መስተዳድርነት እስከ ዛሬ ድረስ በርካታ ውጤታማ ስራዎቸን ሲያከናውኑ ቆይተው አሁን ደግሞ ለሌላ ሀላፊነት ወደ ፌደራል የተወሰዱበት የሽግግር ጊዜ ላይ ነን ብለዋል።

እንደ ሀገርም የሽግግር ጊዜ ላይ እንገኛለን ያሉት ዶክተር ደብረፅዮን፥ ሽግግሩ ግን ፈታኝ ነው፤ በአንድነት በመሆን ችግሮቹን መፍታት ይጠበቅብናል ሲሉም ተናግረዋል።

አሁን ያለውን የፌደራል ስርዓትና ህገ መንግስት አጥብቆ በመያዝና የጎደለውን በመሙላት ሀገራችንን የምናሸጋግርበት እድል ተገኝቷል ሲሉም ነው የተናገሩት።

የትግራይ ህዝብ ለፌደራል ስርዓቱ ከፍተኛ መሰዋእትነት መክፈሉን ያነሱት ዶክተር ደብረፅዮን፥ አሁንም ቢሆን ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በመተባበር ችግሮችን ለመቅረፍ ዝግጁ ነው ብለዋል።

ለአዲሱ የኦሮሚያ ክልል አመራር መልካም ምኞት የተመኙ ሲሆን፥ የትግራይ ህዝብ እና መንግስት ሁሌም ከጎናችሁ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይም ለአቶ ለማ መገርሳ፣ ለዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ፣ ለወይዘሮ ጠይባ ሀሰንና ለዶክተር አለሙ ስሜ ከፍተኛ የሜዳሊያ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

በሙለታ መንገሻ

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *