የሰባት ወደቦችን ደረጃ ያሻሽላል፤ ሁለት አዳዲስ ወደቦችን ይገነባል፤የአምስት ጀልባዎችን ግዥን ጨምሮ የውሃ ላይ መስመር ስራም ይሰራበታል የተባለው ፕሮጀክት የት ገባ?

‹‹የጣናን መሠረተ ልማት ማዘመን›› ፕሮጀክት ለረጅም ጊዜ በመጓተቱ የኔዘርላንድ መንግስት ድጋፉን ማቋረጡን የኢትዮጵያ ማሪታይም ጉዳይ ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

ስራውን በ4 መቶ ሚሊዮን ብር ለማከናወን ነበር የታቀደው፤ ከዚህ ውስጥ 50 በመቶው በኔዘርላንድ መንግስት እንደሚሸፈን ከኢትዮጵያ ጋር ተስማምተው ነበር፡፡

የኢትዮጵያ ማሪታይም ጉዳይ ባለስልጣን አስተዳደር ተጠባባቂ ዳይሬክተር ካፒቴን ጌትነት አባይ እንደተናገሩት ከስድስት ዓመታት በፊት በፕሮጀክቱ የአካባቢ እና የማህበራዊ ጉዳይ ግምገማ ጥናት እና የወደቦችን ማሻሻያ የሚያሳይ ጥናት ተሰርቷል፡፡ ጥናቱን ወደ ተግባር ለማስገባት የሚያስችል ስምምነትም በ2009 ዓ.ም የካቲት መጨረሻ በኢትዮጵያ እና በኔዘርላንድ መንግስት መካከል ተፈርሞ ነበር፡ 2010 በጀት ዓመት ግን ለፕሮጀክቱ ግንባታ የሚውል ገንዘብ አልተመደበም፡፡ ይሁን እንጂ በ2011 መንግስት ለስራው በኢትዮጵያ በኩል የሚያስፈልገውን በጀት መድቧል፡፡

Related stories   “ትህነግ ከጁንታነትም ወርዶ በየጫካው ተሹለክላኪ የእህል ሌባ ሆኗል፣ ከያለበት እየታደነ ነው “ሜ/ጀ መሐመድ ተሰማ

ከስድስት ዓመታት ዝግየታ በኋላ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል የሚያስፈልጉ መስፈርቶች ተሟልተው ወደ ተግባር ለመግባት ጥያቄው ለኔዘርላንድ መንግስት ቀርቧል፡፡ ‹‹ፕሮጀክቱ ለረጅም ጊዜ ሲጓተት የቆየ በመሆኑና በሀገሪቱ ውስጥም ለስራው ድጋፍ የሚያደርገው ድርጅት በመዘጋቱ ለማቋረጥ ተገደናል›› የሚል ምላሽ የኔዘርላንድ መንግስት በተያዘው ሚያዝያ ወር እንደሰጠ ካፒቴን ጌትነት ነግረውናል፡፡

‹‹ፕሮጀክቱን ለማስቀጠል በኔዘርላንድ አምባሳደር በኩል ግፊት እየተደረገ ነው፤ ከሌላ ድርጅት ድጋፍ በማፈላለግም ስራው እንዲቀጥል ይደረጋል›› ነው ያሉት፡፡

Related stories   ብርሃኑ ነጋ አቋማቸውን ቀየሩ፤ ኢዜማ ደርግ በግፍ የዘረፈውን የግል ሃብት ለተከራይ እንደሚሸጥ ይፋ አደረገ፤ የኢዜማ የ ” ፍትህ” ሩጫ

የጣና ሀይቅን የወደብ ደረጃ ለማሻሻል በኢትዮጵያ እና በኔዘርላንድ መንግስት ትብብር ‹‹የጣናን መሰረተ ልማት ማዘመን›› የሚል ፕሮጀክት እንቅስቃሴ ላይ እንደነበር ይታወቃል፡፡

የወደብ ግንባታውን ደረጃውን የጠበቀ እና አገልግሎቱንም ቀልጣፋ ለማድረግ ነበር በአዲስ ለመገንባት ያስፈለገው፡፡ ለስራውም 4 መቶ ሚሊዮን ብር ዕቅድ ተይዞ ነበር፡፡ ከዚህ ውስጥ ግማሹ በኔዘርላንድ፣ ግማሹ ደግሞ በኢትዮጵያ መንግስት እንደሚሸፈን ነበር የተስማሙት፡፡

Related stories   አስከሬን እንዲለቀም ታዘዘ - ትህነግ የአጽም ፖለትካ ድራማ ይፋ ሆነ

ፕሮጀክቱ የሰባት ወደቦችን የግንባታ ደረጃ ከማሻሻል ባሻገር ‹‹ቆራጣ›› እና ‹‹ሰቀለጥ›› የተባሉ አዳዲስ የወደብ ግንባታዎችን ለማከናወን የሚያስችል ነው፡፡ በፕሮጀክቱ የአምስት ጀልባዎች ግዥን ጨምሮ የውሃ ላይ መስመር ስራም እንደሚሰራ መዘገባችን ይታወቃል፡፡

በባህርዳር የሚገኘው የጣና ሀይቅ ወደብ ከ1942 ዓ.ም ጀምሮ አገልግሎት በመስጠቱ በጉዳት እያጋጠመው መሆኑ ይታወቃል፡፡

ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 14/2011ዓ.ም (አብመድ)

ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሰራ

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *