” ቅስቀሳው ልክ እንደ አልበሽር ኢሳያስን በህዝባዊ ዓመጽ ለማስወገድ ይቻላል የሚል ነው። የበሽር መወገድ የድፍረቱ መነሻሻ ቢንዚን ነው። ይህን እውን ለማድረግ ሰራዊቱ ውስጥ ለመግባት ይሞከራል። በኤርትራ ያሉትን ችግሮች በማጎላትና በማሳየት አመጹን ለማንደድ ጥድፊያ አለ። ጥድፊያው የሚጠቅመው ማንን ነው የሚለውን መመርመር አግባብ ነው። ከአመጹ በሁዋላ ማን ነው ተጠቃሚው የሚለው ብቻ ሳይሆን ቀጣዩ የአገራችን እጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል ብለን ተረጋግተን ካልመረመርን ለሃዘንም ጊዜ ላይኖረን ይችላል። እንደ እኔ ቢሆን ኢሳያስ ራሳቸው ሰላማዊ ሽግግር እንዲያደርጉ ስልታዊ ጫና ማድረግና እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ያሉ ወዳጆቻቸው እንዲመክሩዋቸውና እንዲጫኑዋቸው ማድረጉ የተሻለ ነው….” ነዋሪነቱ ስዊዲን የሆነ ኤርትራዊ ከተናገረው የተወሰደ

ለሁለት አስርት ዓመት በኢትዮጵያና በኤርትራ ህዝብ ላይ ያለፍላጎታቸው የተወሰነባቸው የመለያየት ግንብ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ወደ ስልጣን በመጡ ማግስት መነሳቱ የወቅቱ ከፍተኛና ዓለምን ሳይቀር ያስደመመ ፖለቲካዊ ድል ነበር። ይህን እንጂ የተከፈቱት ብዙም ሳይቆዩ እንዲዘጉና እንዲከፈቱ ተደርገዋል። ዛሬ የወጡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ደግሞ ዳግም ድንበሮቹ ሙሉ በሙሉ ተዘግተዋል። በኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ላይ የሚሸረቡ ጉዳዮች እንዳሉ የሚያውቁ የኤርትራ ሕዝብ ለአገሩ ሲል ጥንቃቄና ትዕግስት የተላበሰ አካሄድን እንዲመረጥ የሚመክሩ መኖራቸውም እየተደመጠ ነው።

ለድንበሮቹ መዘጋት አግባብ ካላቸው የመንግስት አካላት በይፋ ምክንያቱ ባይነገርም፣ ድንበሮቹ መዘጋታቸው እውነት መሆኑ ማረጋገጫ ተሰጥቷል። የትግራይ ክልል ድንበሮቹ የተዘጉበትን ምክንያት የፌደራል መንግስት እንዲያብራራ መጠየቁም በቢቢሲ ተመልክቷል።

ከድንበሮቹ በድንገት መዘጋት ጋር ግንኙነት ይኑረው አይኑረው ባይታወቅም ካሱዳኑ መሪ አልበሽር መወገድ በሁዋላ ኤርትራ ላይ በተመሳሳይ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፉወርቂን በዓመጽ ለማስወገድ፣ የአገሪቱን የሰራዊት አመራሮች የማስተባበር ስራ መሞከሩን የሚጠቁሙ አሉ።

ለዛጎል መረጃ ያደረሱ እንደሚሉት በኢትዮጵያ ለውጡን ተከትሎ በርካታ ፖለቲካዊ ውሳኔዎች ተሰስነዋል። እስረኞች ተፈተዋል። የፖለቲካ ምህዳሩ ሰፍቷል። የፕሬስ ነጻነት ያለገደብ ተፈቅዷል። በአገሪቱ ሃሳብን ያለገደብ ማንሸራሸር ገድብ የማይጣልበት መሆኑ ተረጋግጧል። አገራቸውን ጥለው እንዲወጡ የተደረጉ በሰላም እንዲገቡ ተጋብዘው ለአገራቸው ምድር በቅተዋል። ኢሳያስ ግን የወሰዱት የለውጥ እርምጃ የለም በሚል ህዝባዊ ዓመጽ ለማቀጣጠል ውስጥ ውስጡን ስራ መጀመሩን የኤርትራ መንግስት ደርሶበታል።

Related stories   መከላከያ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ “ጁንታውን” ሙሉ በሙሉ መደምሰሱን አስታወቀ! በርካታ በቁጥጥር ስር ውለዋል

የመረጃው ክፍሎች እነማን ልዩ እርዳታ እንደሚያደርጉና ኢሳያስ አፉወርቅ ላይ ዓመጽ ለማቀጣጠል በጀት መድበው እንደሚንቀሳቀሱ ይፋ ባያደርጉም የመከላከያና የድህንነት የጋር ስምምነት የፈረመችው ኢትዮጵያና የኤርትራ መንግስት ጉዳዩ በውል ያውቁታል። በኤርትራ እንዲህ ያለው አክሳሪ አካሄድ እንዳይቀሰቀስ በጋራ እንደሚሰሩ ግን አልሸሸጉም።

ፕሬዚዳንት ኢሳያስ በአገራቸው ለውጥ ለማካሄድ እቅድ መያዛቸውንና የዚሁ እቅድ አካል የሆነውን መረጃ በግንቦቱ የድል በዓላቸው ላይ ይፋ ሊያደርጉ እንደሚችሉ መረጃ ያላቸው እንዳሉት፣ የኤርትራ ሕዝብ ምንም ጉዳይ ውስጥ በስሜታዊነት እንዳይገባ ይመክራሉ። ይህ ካልሆነና አገሪቱን ወደ አለመረጋጋት በሚያመራ አኳኋን የለውጥ እሳት ከተለኮሰ አስቸጋሪ ቀውስ ሊከሰት እንደሚችልም ያስጠነቅቃሉ።

አክቲቪስቶች ሁሉንም መመርመርና መፈተሽ እንደሚገባቸው፣ ተቃዋሚ ሃይሎችም የበሰለ አካሄድ ሊከተሉ እንደሚገባ በተለያዩ ወቅት በስፋት የኤርትራን ጉዳይ የሚከታተሉ ምክረ ሃሳብ የሚሰነዘርበት ጉዳይ መሆኑ የሚታወስ ነው። ሟቹ መለስ ዘናዊ ኤርትራ ባሏት ብሄረሰቦች ብዛት በክልል ተከፋፍላ ፌደራላዊ ስርዓት ሊመሰረለትላት እንደሚገባ፣ ይህም በጥናት ደረጃ መጠናቀቁና ኢሳያስ አፉወርቅ ሲወገዱ ተግባራዊ እንደሚሆን መናገራቸው አይዘነጋም።

ይህንን የሚያስታውሱ እንዳሉት እንዲህ ያለው የዘር ፌደራሊዝም ኢትዮጵያን አሁን ላለችበት መካራ መዳረጉን ኤርትራዊያን እንደሚረዱና ይህን ክፉ አካሄድ ወደ አገራቸው ፈልገውና ፍቅደው እንዳይጋብዙ ያሳስባሉ። በተለይም በሱዳን ያለው አካሄድና የፖለቲካ ለውጥ ያሳሰባቸ ክፍሎች ኤርትራ ላይ አስቸኳይ ለውጥ እንዲቀጣጠል አቅማቸውን አሟጠው ለመጠቀም መጓጓታቸውን ከግምት ውስጥ አግባብ መሆኑንን ይገልጻሉ።

ቢቢሲ አማርኛ ይህንን ዘግቧል።

ኢትዮጵያን ከኤርትራ ጋር የሚያገናኙት ሁሉም የድንበር በሮች ሙሉ በሙሉ መዘጋታቸውን የየአካባቢዎቹ ባለሥልጣናት እና ነዋሪዎች ለቢቢሲ አረጋገጡ።

የሁመራ-ኦማሃጀር ድንበር ባሳለፍነው ሳምንት የተዘጋ ሲሆን፤ ዛሬ ደግሞ የቡሬ-አሰብ ድንበር መዘጋቱን የአፋር ክልል የሕዝብ ግንኙነት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኦስማን እድሪስ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የተቀሩት ሁለቱ ድንበሮች ከዚህ በፊት በተለያዩ ጊዜያት ዝግ መደረጋቸው ይታወሳል።

Related stories   ሰበር ዜና – ትህነግ በዲፕሎማሲ ዘመቻ ቀውስ ገጠመው፤ “ በሃሰት መረጃ አሳፈራችሁን ” የቅርብ አጋሮቻቸው

ምንም እንኳ ድንበሮቹ ለመዘጋታቸው ይፋዊ ምክንያት ባይሰጥም፤ ይፋዊ ያልሆኑ መረጃዎች በሁለቱ ሀገራት መካከል የቪዛ እና የቀረጥ ጉዳዮችን መልክ ለማስያዝ በሚል ምክንያት በእግር እና በመኪና ድንበር ማቋረጥ ለማስቆም በማሳብ የድንበር በሮቹ ዝግ መደረጋቸውን ይጠቁማሉ።

ቢቢሲ ድንበሮቹ የተዘጉበትን ምክንያት ለማጣራት የሚመለከታቸውን አካላት ለማነጋገር ጥረት አድርጓል።

በአሥመራ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በጉዳዩ ላይ ምላሽ መስጠት የሚችለው የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር ነው ብሏል። የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር በበኩሉ በድንበር ጉዳዮች ላይ የጠቅላይ ሚንስትሩን ቢሮ አነጋግሩ ብሎናል።

በጠቅላይ ሚንስትሩ ቢሮ የፕሬስ ሴክተሪያት አቶ ንጉሱ ጥላሁን ቆይተን እንድንደውል ነግረውናል። ተጨማሪ መረጃ እንዳገኘን እናቀርባለን።

የትግራይ ክልል የኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊዋ ወ/ሮ ሊያ ካሳ፤ “ድንበሮቹ የተዘጉበትን ምክንያት የፌደራል መንግሥት ለሕዝብ ማብራሪያ እንዲሰጥ ጠይቀናል” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

ከወራት በፊት ድንበሮቹ መከፈታቸውን ተከትሎ በሁለቱ ሀገራት ዜጎች መካከል ንግድ ተጧጡፎ እንደነበረ መዘገባችን ይታወሳል።

ለምሳሌ ለሱዳን ቅርብ የሆነው ሁመራ-ኦመሃጀር ድንበር ሳይዘጋ በፊት ከፍተኛ የሆነ የትራፊክ ፍሰት ነበረው። በሑመራ ገንዘብ መንዛሪዎች ንግድ ደርቶላቸው ዶላር ወደ ናቅፋ እንዲሁም ናቅፋ ወደ ዶላር ይመነዝሩ ነበር። ዛላምበሳ-ሰርሃ ደንበር እንዲሁም ንግድ ተጧጡፎ ነበር።

ኢትዮጵያና ኤርትራ ወደ 1ሺህ ኪሎ ሜትር የሚጠጋ ድንበር ይጋራሉ። ለመሆኑ በዚህ ረጅም ድንበር ሁለቱን ሀገራት የሚያገናኙ አራቱ መግቢያና መውጫ በሮች የትኖቹ ናቸው?

1. ዛላምበሳ-ሰርሃ

ቀድመው ከተከፈቱት ሁለት በሮች የዛላምበሳ-ሰርሃ ድንበር አንዱ ነበር። በቅድሚያ የተዘጋውም ድንበር ዛላምበሳ-ሰርሃ ነው።

አንድ ሰው ከመቐለ ከተማ ተነስቶ፣ አዲግራትን አልፎ፣ ዛላምበሳን ቢሻገር የኤርትራዋን ሰርሃ መንደር ያገኛል። ጉዞውን ገፋ ቢያደርግ ደግሞ ከፊቱ ሰንዓፈ አለች። መንገዱ፤ ዓዲ ቀይሕን እና ደቀምሃረን የተሰኙ አነስተኛ ከተሞችን አልፎ አሥመራ ድረስ ይዘልቃል።

የዛላምበሳ-ሰርሃ መስመር መስከረም 01፣2011 ዓ. ም. ከተከፈተ በኋላ፤ ፈጣን የንግድ ልውውጥ የተጀመረው ወድያውኑ ነበር። እህልና ሸቀጦች የጫኑ ግዙፍ መኪኖች መስመሩን ማጨናነቅ የጀመሩትም ድንበሩ መከፈቱን ተከትሎ ነበር።

Related stories   “ዶላር እናወርዳለን” የውጭ አገር ዜጎችን የዝርፊያ ድራማ ፖሊስ አለሳልሶ ይፋ አደረገው

ባለፈው ህዳር ወር ላይ ግን ይህ መስመር መልሶ ተዘግቷል። በአሁኑ ወቅት፤ ለተለመዱት ማህበራዊ መስተጋብሮች በድንበሩ አካባቢ የሚኖሩ የሁለቱም ሃገራት ዜጎች በእግር ከሚያደርጉት ግንኙነት ውጪ፤ መንገዱ ለመኪኖች ዝግ ሆኗል።

2. ራማ-ክሳድ ዒቃ

ኢትዮጵያና ኤርትራ በዚህ መስመር የሚገናኙት በመረብ ወንዝ ላይ በተዘረጋው ድልድይ አማካይነት ነው። በድልድዩ ሁለቱ ጫፎች፤ በኢትዮጵያ በኩል ራማ በኤርትራ በኩል ደግሞ ክሳድ ዒቃ አለች።

በአድዋ በኩል ወደ አሥመራ መግባት የሚፈልግ ሰው፤ በዚሁ መስመር ዓዲ ኳላን እና መንደፈራን አልፎ አሥመራ ድረስ መዝለቅ ይችላል።

ይህ መሰመርም መስከረም ወር ላይ ተከፍቶ ህዳር ወር ላይ ዳግም ተዘግቷል።

3. ሁመራ-ኦምሃጀር

ሁመራ-ኦማሃጀር ሌላኛው በትግራይ በኩል ኢትዮጵያን ከኤርትራ የሚያዋስነው ድንበር ሲሆን፤ ለሱዳን ቅርብ የሆነው በር ነው። ድንበሩ የተከፈተ ሰሞን በድንበሩ አቅራቢያ ከፍተኛ የሆነ የትራፊክ ፍሰት ተስተውሎ ነበር።

ይህ መስመር ዘግየት ብሎ በዕለተ ገና የሁለቱ ሃገራት መሪዎች በተገኙበት ታህሳስ 29፣2011 ዓ. ም. ነበር የተከፈተው።

ከፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ እና ከጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ በተጨማሪ የትግራይ ክልል አስተዳዳሪ ዶ/ር ደብረፂዮን ገብረሚካኤልና የአማራ ክልል አስተዳዳሪ የነበሩት አቶ ገዱ አንዳርጋቸውም በዚሁ ሥነ ስርዓት ላይ ተገኝተው ነበር።

ይህ የድንበር በር ለሱዳን ብቻ ሳይሆን ለአማራ ክልልም ቅርብ ነው። ስለዚህም፤ ከጎንደር ወደ ኤርትራ መዝለቅ የፈለገ ሰው ይህን መስመር መምረጡ አይቀሬ ነው።

በሁመራ በኩል ተሰነይንና ባረንቱን አልፎ፤ አቁርደት እና ከረንን ረግጦ አሥመራ የሚያደርሰው ይህ መስመርም ከቀናት በፊት ተዘግቷል።

4. ቡሬ-ደባይ ሲማ

ከላይ የተጠቀሱት ሦስቱ የድንበር በሮች በትግራይ በኩል የሚያዋስኑ ሲሆን ቡሬ-ደባይ ሲማ ደግሞ በአፋር በኩል የሚያገናኘው ነው።

በአፋር ክልል አድርጎ ኢትዮጵያን ከአሰብ ወደብ ጋር የሚያገናኛት ይሄው መስመር ነው።

ቡሬ- ደባይ ሲማ መስመር የተከፈተው የሰርሃ ዛላምበሳው መስመር በተከፈተበት የኢትዮጵያውያን አዲስ ዓመት ላይ ነበር። ይህም የድንበር በር ዛሬ መዘጋቱ ተረጋግጧል።

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *