እድሜያቸው ወደ 60 ዓመት የሚጠጋ ወይዘሮ ናቸው። ወደ ሃኪም ዘንድ የሄዱት ደም የቀላቀለ ፈሳሽ ከማህጸናቸው መውጣት ከጀመረ ከዓመት በኋላ ነበር።

ወይዘሮዋ ቀደም ብሎ ከፍ ያለ ህክምና እንዲያገኙ በሃኪም ቢታዘዙም ባለቤታቸው ፈቃደኛ ስላልሆኑ ቤታቸው ቆይተዋል።

ችግሩ ሲከፋ ወደ ሃኪም ዘንድ ቀርበው ለዶ/ር ቤርሳቤህ መናሻ “ከዚህ በፊት አንድ ጊዜ ታምሜ ሪፈራል ተፅፎልኝ ባለቤቴ ስላልፈቀደ ችላ በማለት ሳልታከም ቀረሁ” ብለው ሲነግሯት በጣም እንዳዘነች ታስታውሳለች።

“ማህበረሰባችን የበሽታውን ክብደት ብዙም ስለማይገነዘበው በርካታ ሴቶች ህመማቸውን ይዘው ከፍተኛ ደረጃ ላይ እስኪደርስ ድረስ ይቆያሉ” ትላለች ዶ/ር ቤርሳቤህ።

ለወይዘሮዋ አስፈላጊውን ምርመራና ህክምና አድርጋ በድጋሚ ለተጨማሪ ህክምና ከፍ ወዳለ ሆስፒታል ስትልካቸው ባለቤትየው “እህል የምናበረይበት ወቅት ስለሆነ ሰው ያስፈልገኛል” ብለው ሞገቱኝ ትላለች።

ይህ አጋጣሚ የእኚህ እናት ብቻ አይደለም። ብዙ ሴቶች ይህን አሳዛኝ ታሪክ እንደሚጋሩ ዶ/ር ዳግም ታደለም “ብዙዎቹ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ሲደርሱ ነው እኛ ጋር የሚመጡት” በማለት ያረጋግጣል።

ከማህጸን የሚወጣ ፈሳሽ የካንሰር፣ የአባላዘር በሽታዎችና የሌሎች ኢንፌክሽኖች አንዱ ምልክት ሆኖ ሳለ ብዙዎች ስለጉዳዩ ዕውቀት አለማግኘታቸውና ለመነጋገር አለመቻላቸው ችግሩን አባብሶታል።

እርሶስ ስለጉዳዩ ምን ያህል ያውቃሉ?

ከማህጸን ስለሚወጣ ፈሳሽ በማህበረሰቡ ውስጥ በቂ እውቀት እንዲኖር የሚያስችል አጋጣሚ የለም የሚሉት ባለሙያዎቹ የራሳቸውን ተሞክሮ ያስታውሳሉ።

ዶ/ር ቤርሳቤህ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷ ውስጥ በግልፅ ከማህፀን ስለሚወጣ ፈሳሽ ባለመማሯ “የህክምና ሙያ ባላጠና ኖሮ ስለዚህ ጉዳይ አለላውቅም ነበር” ትላለች።

የጥቁር አንበሳ የህክምና ትምህርት ቤት ተማሪ የሆነው ሃብቶም አለሙም ዩኒቨርሲቲ ከመግባቱ በፊት ስለዚህ ጉዳይ ለምን በትምህርት ቤት ሳለ እንዲያውቅ እንዳልተደረገ ጥያቄ እንደፈጠረበት ይናገራል።

ከማህፀን የሚወጣ ፈሳሽ ምንድን ነው?

በእንግሊዘኛው ‘ቫጃይናል ዲስቻርጅ’ የሚባለው ከማህፀን የሚወጣ ፈሳሽ የአንድ ሴት የወር አበባ ኡደትን ተከትሎ በተለያየ መጠንና ዓይነት ከማህጸን የሚወጣ ፈሳሽ ነው።

ማህፀንና ፅንስን የሚያጠኑት ዶ/ር ዳግም ከማህፀን የሚወጣ ፈሳሽ ጤናማ የሆነ ተፈጥሯዊ ነገር ሲሆን፤ በሽታ ሲይዝ ግን ጤናማ ያልሆነ ሽታ ሊያመጣና ቀለሙም ሊቀየር እንደሚችል ይናገራሉ።

ይህ ከማህፀን የሚወጣ ተፈጥሯዊ ፈሳሽ ከሆርሞን የሚመነጭ እንደሆነ የሚናገሩት ዶ/ር ዳግም “አንዲት ሴት ሁሌም ይህ ፈሳሽ ሊኖራት ይችላል። እንዲያውም በቀን ከ 1 እስከ 4 ሚሊሊትር ሽታ የሌለው ከማህፀን የሚወጣ ነጭ ፈሳሽ ጤናማ ተደርጎ ይወሰዳል” ይላሉ።

ይህ ተፈጥሯዊ የሆነ የፈሳሽ መጠን ግን ሴቷ ጤናማ ሁኔታ ላይ ሆናም በእርግዝናና በአንዳንድ እርግዝና መከላከያዎች ምክንያት መጠኑ ሊቀየር እንደሚችል ዶክተሩ ይናገራሉ።

ከማህፀን የሚወጣው ፈሳሽ የማህፀን ካንሰርና በግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎች ምልክት ሊሆን ይችላል። እነዚህ በሽታዎች በሚያጋጥሙ ጊዜም የፈሳሹ መጠን፣ ጠረንና ቀለም ሊለወጥ ይችላል።

Image copyright AFP Contributor

በግልጽ የማይነገር ጉዳይ

በርካታ ሴቶች ከማህጸን ስለሚወጣ ፈሳሽ በግልጽ በአስፈላጊው ጊዜ ለመናገር አይደፍሩም። ለሃኪሞችም ቢሆን የሚገልጹት ከብዙ ጉትጎታ በኋላ ነው።

“ታካሚዎች ከማህፀን የሚወጣ ፈሳሽ ለውጥ እንዳለ የሚናገሩት ሌሎች ምልክቶችን ጠቅሰው ሲጨርሱ መጨረሻ ላይ ነው” የምትለው ዶ/ር ቤርሳቤህ ለማውራት ነፃነት እንዲያገኙም ባሎችን ወይም ሌሎች ሰዎችን አስወጥተን ነው የምናነጋርራቸው ትላለች።

አንድ ታካሚዋ ከማህጸኗ የሚወጣው ፈሳሽ ደም ከመቀላቀል አልፎ ህመም ሲበረታባት እንደመጣች የምታስታውሰው ዶ/ር ቤርሳቤህ “በርካታ ሴቶች የማህፀን ፈሳሻቸው ከተለመደው የተለየ ሲሆን ህክምና ፈልገው አይመጡም፤ ሁሌም ከእሱ ጋር የተያያዘ ሌላ ህመም ሲኖራቸው ብቻ ነው የሚመጡት” ትላለች።

በተለይ ከከተማ ውጪ የሚኖሩ ሴቶች ከማህፀን የሚወጣ ፈሳሽ ሲቀየር ህክምና ባለማድረጋቸው ምክንያት ችግሩ ከማህጸን ጫፍ ወደ ውስጥ በመግባት ኢንፌክሽን ፈጥሮ ሌላ ከባድ ችግር ሲያጋጥማቸው ወደህክምና እንደሚሄዱ ዶ/ር ዳግምም ይናገራሉ።

ዶ/ር ቤርሳቤህ እንደምትለው ከማህጸን የሚወጣው ፈሳሽ የካንሰር፣ የአባላዘር በሽታዎችና የሌሎች ኢንፌክሽኖች ምልክት ሆኖ ሳለ በጉዳዩ ላይ በግልጽ መነጋገር ስለማይደፈር፤ ያለው የህክምና አገልግሎት እርዳታ እንዳያደርግ መሰናክል እንደሆነበት ትናገራለች።

ከማህጸን በሚወጣ ፈሳሽ ላይ የሚታዩ ለውጦችን በመከታተል በጊዜ ወደ ህክምና መሄድ ከቻሉ ለካንሰርም ሆነ ለአባላዘር በሽታዎች የተሻለ ህክምና በማግኘት ጤናቸውን የማሻሻል ዕድል እንዳለ ባለሙያዎቹ ይመክራሉ።

የህክምና ድጋፍ ለማግኘትም የሚከተሉትን ምልክቶች ትኩረት ሰጥቶ ማስተዋል ያስፈልጋል። ከማህጸን የሚወጣ ፈሳሽ ሽታ ወይም ቀለም መቀየር፣ ደም መቀላቀል፣ የመራቢያ አካላት መቅላትና በግብረ ሥጋ ግንኙነት ወቅት የህመም ስሜት ካለ ባለሙያ ጋር በመሄድ ማማከር ያስፈልጋል።

ትምህርት ቤቶችና የሥነ ተዋልዶ

የትምህርት ተቋማት ለተማሪዎቻቸው ከማህጸን ስለሚወጣ ፈሳሽና ስለሌሎች የሥነ ተዋልዶ ጉዳዮች በግልጽና በአግባቡ ማስተማር ከቻሉ በህብረተሰቡ ውስጥ ያለው ሀፍረትና የህክምና ድጋፍ ለማግኘት ያለመድፈር ጉዳይ ሊቀረፍ እንደሚችል ባለሙያዎቹ ይናገራሉ።

በአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሳለች “ስለ ሥነ ተዋልዶና የተያያዠ ጉዳዮች ስንማር በአስተማሪው ተነሳሽነት ላይ ይወሰን ነበር” የምትለው ዶ/ር ቤርሳቤህ፤ ብዙም ጠለቅ ያለና ስለጉዳዩ በቂ ግንዛቤን የሚያስጨብጥ ትምህርት እንዳልሆነ ታስታውሳለች።

አክላም በመጀመሪያና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷ ወቅት ስለ ሥነ ተዋልዶና ስለየወር አበባ ብትማርም ሴቶች ስለሚያጋጥማቸው ከማህፀን የሚወጣ ፈሳሽ ምንም ነገር ስላልተማረች በወቅቱ ምንም የምታውቀው ነገር እንዳልነበረ ትገልጻለች።

አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኘው የቦሌ መሰናዶ ትምህርት ቤት መምህር የሆኑት አቶ ተሾመ መሳፍንት የባዮሎጂ መምህር ሲሆኑ፤ የሥነ ተዋልዶ ትምህርት 7 እና 8ተኛ ክፍል እንደሚሰጥ ነገር ግን በ11ኛ እና 12ኛ ክፍል የባዮሎጂ ትምህርት ውስጥ እንደሌለ ይናገራሉ።

ዶ/ር ቤርሳቤህ “ወንዶች ህክምና ካላጠኑ በስተቀር ከማህፀን ስለሚወጣ ፈሳሽ የማወቅ እድል የላቸውም” ስትል ከዚህ ተመሳሳይ በሆነ መልኩ ዶ/ር ዳግምም “ህክምና ስማር አንብቤ ነው ያወኩት” ብሏል።

ከታች ባሉት የትምህርት ክፍሎች ውስጥ ከሥነ ተዋልዶ ትምህርት ጋር ተጣምሮ ከማህጸን ስለሚወጣ ፈሳሽ ትምህርት ቢሰጥ መልካም እንደሆነ የሚገልጹት ሁለቱ የህክምና ባለሙያዎች እነሱም ስለፈሳሹ ያወቁት ህክምና በማጥናታቸው እንደሆነ ይመሰክራሉ።

BBC Amharic

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *