ኢራን የአሜሪካ ማዕቀብ ከኒውክሌር ስምምነቱ እንድትወጣ ሊያደርጋት እንደሚችል አስታወቀች
ኢራን የአሜሪካ ማዕቀብ ከኒውክሌር ስምምነቱ እንድትወጣ ሊያደርጋት እንደሚችል አስታወቀች። የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጃባድ ዛሪፍ ቴህራን የዋሽንግተንን አዲስ ማዕቀብ ተከትሎ ሌላ አማራጭ ለማየት እንደምትገደድ ተናግረዋል።
ከአማራጮቹ አንዱ ደግሞ ቴህራን ከሃገራት ጋር ስምምነት የደረሰችበትን የኒውክሌር ፕሮግራም ስምምነትን ማቋረጥ ሊሆን ይችላል ነው ያሉት። ጃባድ ዛሪፍ በዚህ ጉዳይ ላይ የኒውክሌር ስምምነቱ አካል የሆኑት የአውሮፓ ሃገራትም ኢራንን እያገዟት እንዳልሆነም ገልጸዋል።
አሜሪካና ኢራን ያላቸው ግንኙነት በተለይም ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ ይበልጥ ሻክሯል። ትራምፕ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ አሜሪካን ከ2015ቱ የኒውክሌር ስምምነት ውጭ አድርገዋታል።
ከሳምንት በፊትም የኢራንን አብዮታዊ ዘብ በአሸባሪነት የፈረጁ ሲሆን፥ ሃገራት ከኢራን ምንም አይነት ነዳጅ እንዳይገዙም ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል። ይህን ተላልፈው ለነዳጅ ገበያ ቴህራን ጋር የሚደራደሩ አካላት ካሉም ከባድ ማዕቀብ እንደሚጥሉ መግለጻቸውም የሚታወስ ነው። ይህን ተከትሎም የሁለቱ ሃገራት ፍጥጫ እየተባባሰ መምጣቱ ይነገራል።
ሩሲያ አዲስ የጦር መሳሪያ ቁጥጥር ስምምነት ከአሜሪካ ጋር ለመፈጸም ፈቃደኛ መሆኗ ተነገረ
ሩሲያ አዲስ የጦር መሳሪያ ቁጥጥር ማድረግ የሚያስችል ስምምነት ከአሜሪካ ጋር ለመመፈጸም ፈቃደኛ መሆኗ ተነገረ። የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሩሲያና ከቻይና ጋር አዲስ የጦር መሳሪያ ቁጥጥር ማድረግ የሚያስችል ስምምነት ለመፈጸም ፍላጎት እንዳላቸው መግለጻቸው ይታወሳል። ይህን ተከትሎም ከፍተኛ ባለስጣኖቻቸው በጉዳዩ ዙሪያ ከሃገራቱ ጋር የሚደረገውን ድርድር እንዲያስጀምሩ ትዕዛዝ አስተላለፍዋል።
ሞስኮም በጉዳዩ ላይ ከአሜሪካ ጋር ለመነጋገርነ ስምምነት ለመፈጸም ዝግጁ ስለመሆኗ ሬውተርስ የክሬሚሊን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ረዳት አማካሪ ዩሪ ኡሻኮቭን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።
ረዳት አማካሪው በሃገሪቱ የቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርበው ባደረጉት ንግግርም ሞስኮ በጉዳዩ ላይ ለመነጋገር ዝግጁ ስለመሆኗ አመላክተዋል። እርሳቸው ይህን ይበሉ እንጅ የክሬሚሊን ቃል አቀባይ ግን የትራምፕን እቅድ እርግጠኛ ያልሆነ በማለት ገልጸውታል። ትራምፕ በጦር መሳሪያ ዝውውር ላይ ጠንከር ያለ ቁጥጥር እንዲደረግ ፍላጎት እንዳላቻው ይነገራል።
ለዚህ ደግሞ ከዚህ ቀደም ከነበረው የተሻለና አዲስ የጦር መሳሪያ ዝውውርን የሚቆጣጠር ህግ ይኖር ዘንድ ከሞስኮና ቤጂንግ ጋር ለመደራደርና ስምምነት ላይ ለመድረስ ማሰባቸው ነው የሚነገረው።