በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፤ መተከል ዞን፤ ዳንዱር ወረዳ ላይ በተፈፀመ ጥቃት 17 ሰዎች መገደላቸውን የአማራ ክልል የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አሰማኸኝ አስረስ ለቢቢሲ አስታወቁ። ግጭቱ ሚያዚያ 17 /2011 ዓ.ም የተፈጠረ ሲሆን በጫኝና አውራጅ ሥራ በተሰማሩ ሁለት ግለሰቦች ግላዊ ጠብ ሰበብ እንደሆነ ተናግረዋል። ኃላፊው እንደሚሉት በጊዜው የነበረው ፌደራል ፖሊስ የሁለቱን ግለሰቦች ግጭት ለማረጋጋት ሲሞክር በመካከል አለመግባባት ተፈጥሮ በተተኮሰ ጥይት አንድ የጉሙዝ ተወላጅ ሕይወቱ ሊያልፍ ችሏል። ከዚህ በኋላ ግጭቱ እንደተባባሰ ኃላፊው ያስረዳሉ።

“በክልሉ አንድ ጉሙዝ ከተገደለ፤ የቆዳ ቀለማቸው ቀላ ያሉ ሰዎችን የመግደልና የመበቀል ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት አለ” የሚሉት አቶ አሰማኸኝ፤ በዚህም ምክንያት በየቦታው ያሉ የአማራ ክልል ተወላጆች ላይ ግድያና ንብረቶቻቸውን የመዝረፍ ጥቃት ተፈፅሞባቸዋል። አቶ አሰማኸኝ 17ቱ ሰዎች በምን አይነት ሁኔታ ተገደሉ ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ በአከባቢው በቀስት እና በጥይት ሰዎችን የመግደል ልማድ አለ። ይሁን እንጂ እኚህ ሰዎች በምን አይነት ሁኔታ እንደተገደሉ የሚያሳይ ዝርዝር መረጃ የለኝም ብለዋል።

ግጭቱ ለተከታታይ አራት ቀናት የዘለቀ ሲሆን የ17 ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተረጋግጧል። ከእነዚህ መካከል አስራ አንዱ የአማራ ክልል ተወላጆች ሲሆኑ ስድስቱ የእዚያው አካባቢ ተወላጆች መሆናቸውን አቶ አሰማኸኝ ተናግረዋል። ለጊዜው ጉዳት ያጋጠማቸው ግለሰቦችን ቁጥር በእጃቸው ባይገኝም ጥቃቱ በተበታተነና በተለያየ አካባቢ በመፈፀሙ የሟቾቹ ቁጥር ሊጨምር ይችላል ብለዋል።

በግጭቱ ስጋት ያደረባቸው ሰዎች እንጂ የተፈናቀሉ ሰዎች አለመኖራቸውም አክለዋል። በአካባቢው የፌደራልና የመከላከያ የፀጥታ ኃይሎች እንዲገቡ የተደረገ ቢሆንም አካባቢው ጫካና የተበታተነ የአኗኗር ስርዓት በመኖሩ ለማረጋጋት ቀናት ሊወስድ ችሏል ብለዋል አቶ አሰማኸኝ። ትናንት ሌሊት ፓዊ ወረዳ፤ አባውርኛ ቀበሌ ላይ 25 የሚሆኑ የአካባቢው ተወላጅ ቤቶች የተቃጠሉ ሲሆን ዛሬ ሌሊት በአንፃሩ መረጋጋት እንደታየ ነግረውናል።

የአማራ ክልል ከሚደግፋቸው ታዳጊ ክልሎች መካከል አንዱ የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መሆኑን የሚጠቅሱት ኃፊው በአካባቢው ባለ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ምክንያት በአማራ ተወላጆች ላይ በተደጋጋሚ ጥቃት መፈፀሙን ኃላፊው ያስታውሳሉ። ይሁን እንጂ ይህንንም ለመከላከል የሁለቱ ክልል አመራሮች በቅርቡ በእንጂባራ ከተማ ተገናኝተው የመከሩ ሲሆን በጋራም እየሰሩ እንደሚገኙ ገልፀዋል። በዚህ ግጭት ሳቢያም በስጋት የሚፈናቀሉ ሰዎች እንዳይኖሩ ከሁለቱ ክልሎች የተውጣጡልዑካን ወደ አሶሳ እያመሩ መሆናቸውን ገልፀውልናል። የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባለስልጣናትን ለማነጋገር ያደረግነው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል።

BBC Amharic

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *