አማራ – “በራሱ ልጆች” የሚደማ፣ የሚዋረድ ሕዝብ ” በሚል ርዕስ ምገስ ሰውየው የተባሉ በዚሁ ገጽ የጻፉትን እንዳነበብኩ ይህንን አጠር ያለ መልዕክት / ሃሳብ  ለማስተላለፍ ወደድኩ። እኔም እንደ ጸሃፊው ጉዳዩን በቅርብ የምከታተል የአዲስ አበባ ነዋሪ የመተከል አካባቢ ተወላጅ በዜግነት ኢትዮጵያዊ፣ በብሄር ደግሞ ዛሬም ሆነ ትናንት መከራ እየደረሰበት ካለው የአማራ ወገን ነኝ።

ጽሁፉ አንድ ተቆርቋሪ፣ የተናደደና እልህ የተናነቀው ሰው የጻፈው ይመስላል። ከጥቅል ሃሳቡ ለመረዳት እንደቻልኩት በአማራ ክልል ውስጥ ያሉ ሁለት ወይም ከዛ በላይ ድርጅቶች እንዴት አብረው መስራት አቃታቸው? የሚለውን የበርካቶች ሃሳብ ለማጉላት በሚል በከረሩ ቃላቶች ጭምር ይራገማል። ችግር ያላቸውን አብይ ጉዳዮች በማንሳት ህብርት ለመፍጠር ከዚህ የተሻለ አጋታሚና አስገዳጅ ምክንያት ሊኖር እንደማይችል በመጥቀስ ግራ መጋባቱን ያትታል። አክሎም በአማራ ላይ ይህ ሁሉ ጉድ እየደረሰ እርስ በእርስ ለመግባባት አለመቻሉ ስሌት አልባ እንደሚሆበት እሳት ሆኖ ይጠይቃል። የግንቦት ሰባትንም ሆነ የሌሎች ጡረተኛ “ፓርቲዎችን” ስም አላነሳም። አብን ሲል ግን ጣቱን ቀስሯል።

የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ / አብን ተቃዋሚም አይደለሁም። ነገር ግን ተደራጅተው ለአማራው ህዝብ አማራጭ ሆነው መቅረባቸውን አደንቃለሁ። ይሁን እንጂ ዛሬ ዓለም የሸሸውን፣ ያረጀውን፣ የሚያሳንሰውን፣ ከሰውነት አቅል ውጪ የሚያደርገውን ብሄር ላይ የተመሰረተ እርምጃቸውን ብዙም አልወደውም። የተሳካ ውጤት የሚያመጡ መስሎ አይታየኝም።

ከግል ስሜቴ ሰወጣና ለመሰንዘር ወደፈለኩት ሃሳብ ሳመራ ጸሃፊው አብን የኮረኮሙበትና ክልሉን እየመራ ያለውን ድርጅት ያዩበት መነጽር የተመጣጠነ መስሎ አልታየኝም። አብን አዲስና በወጣቶች የተገነባ ድርጅት ነው። እነሱ እንደሚሉት በዘውግ የተደራጁት ዓማራው ላይ እየደረሰ ባለው ግፍ የተነሳ ከለላና ጠባቂ ለመሆን ሲሉ ነው። በዚሁም አመለካከታቸው በአጭር ጊዜ ሰፊ መነቃቃት ፈጥረዋል። የወደፊቱ ባይታወቅም ለጊዜው ሰፊ ድጋፍና ሃይል አላቸው። ይህ ብቻውን ሊወደስ የሚገባ ሲሆን፣ ሃላፊነቱን ወስደው ይህንን የሰሩትም አካላት አቶ ክርስቲያንን ጨምሮ መመስገን አለባቸው። ከዚህ የዘለለ ማለት አልችልም።

ጸሃፊው ይህንን አድንቀው ወደ ወቀሳቸው ቢዛወሩ ሃሳባቸው ሙሉ ይሆን ነበር። ወደፊት ከንዴት ነጻ ሆነው የተመጣጠነ አስተያየት እንደሚሰጡ ልባዊ ተስፋ አደርጋለሁ።

ብአዴን፣ የዛሬው አዴፓ የህወሃት የበኩር ልጅ ሆኖ ክልሉን ሲመራ የሰራው ጥፋት መጠን የለውም። አሽከርነቱም ወሰን አልነበረውም። አንዳንዶቹ ሰው ስለመሆናቸው ጭምር እስኪያጠራጥር ድረስ በአጎብዳጅነት ሁለት አስርት ዓመታትን አሳልፈዋል። በዚህ ሁሉ ጊዚያት አማራው ቁልቁል ሄዷል። እኩል ተጠቃሚነት ሳይሆን ያለውን እንዲያጣ ተደርጓል። እንደ ጫጩት እየታፈሰ በየስፍራው ሲወረወርና ሲፈናቀል ተከራካሪ አልነበረውም። በራሱ “ወኪሎች” ትምክሀተኛ፣ ነፍጠኛ፣ የድሮ ስርዓት ናፋቂ እየተባለ ይፈረጅ ነበር።

ሌሎች አየር ላየር የሚመላለሱበት ጎዳናና የኢንዱስትሪ ባለቤት ሲሆኑ አማራው የጠርብ ድልድይ የሚሰራለት አጥቶ በገመድ እየተንጠላጠለ ወንዝ ይሻገራል። ልጆቹ እንኳን ምርጥ ትምህርት ቤት ሊገነባላቸው በየዛፍ ጥግና በወላለቀ ፍራሽ ስር እንዲማሩ ተፈርዶባቸዋል። መክነዋል። ተፈርጀው በጥላቻ እንደ ጠላት እንዲታዩ ተደርገዋል። ይህ ሁሉ ሲሆን ብአዴን ሬሳ ነበር። ይህን ሃቅ ማንንም አይክደውም። ዛሬም ሆነ ቀደም ሲል ቤኒሻንጉል ጉምዝ ኮሽ ባለ ቁጥር አማራው ላይ ቀስት የሚወረወረው ከተዘራው ጥላቻ የተነሳ አማራ ጠላት ተደርጎ በመታየቱ ነው። ምስክርነቴን ልስጥ።

በወያኔ የተፈበረከው የጎሳ ፌደራሊዝም ይፋ ሲሆን ቢኒሻንጉል ጉምዝ ” የናንተ፣ የትወላጆች ናት” ተብሎ ተነገራቸው። አማራ ወራሪ ተድርጎ ሲፈረጅ በረከት የሚመራው፣ አዲሱ የሚከተለው ብአዴን ቁጭ ብሎ እያየና እያስፈጸመ ነበር። ህገ መንግስቱ በቁጥር በክልሉ ካሉ ጎሳዎች ሁለተኛ ደረጃ የያዘው አማራ ህዝብ ባይተዋር ሲያደርግ ብአዴን የቤት ስራ አስፈጻሚ እንጂ ተቆርቋሪ አልነበረም። በዚሁ የተነሳ ዛቻ ተጀመረ። በድንገት በገበያ ቀን አድፍጠውና መክረው ፭፮ ሰዎችን ጨፈጨፉ።

የኬሚሴ ኦሮሞ፣ ወላይታው፣ ሃድያው፣ ከንባታው … በአማራ ስም ተሰየፈ። የ፬፮ ቀበሌ ታጣቂ ሚሊሻ እሳት ጎርሶ ለጣናበለስ ፕሮጀክት ሃላፊዎች በጣሊያን ባለሙያዎች በተገነቡት አርባ ቪላ ቢቶች ውስጥ የሚኖሩ አመራሮችን ወረረ። እጅ እንዲሰጡ ጠየቀ። ኤሌክትሪክ አቋርጦ፣ ውሃ ዘግቶ አስገድዶ ከቀናት በሁዋላ ቤታቸው የነበሩትን እጃቸውን ያዞ ረሸናቸው። የሺናሻ ተወላጅ የሆነው ዋና አስተዳዳሪ አሰፋ ኢናቡን ስምንት ኪሎ ሜትር ግድም ጫማውን አስወልቀው በባዶ እግሩ ከነዱት በሁዋላ፣ አልሙ መንደር ሰባት ” አፋፋሙበት” በውቅቱ ፌደራል ፖሊስ፣ መከላከያ ቢኖሩም የሕዝቡን ቁጣ ለመቋቋም እንደማይችሉ በማመን ዳር ቆመው ትዕንቱን ሲያዩ ነበር። በነገራችን ላይ ወርቅ የሚዝቅበት ከማሼ ዞን ላይ ግን ምንም ጸብ የለም። ለምን የሚለውን አቶ ሞገስ በነካ እጅዎ ይግቡበት።

ይህንን ያነሳሁት ለጀብድ አይደለም። የወቅቱ የአማራ ክልል መሪዎች እንዴት አድረገው በሂደት ይህን ህዝብ ራሱን እንዳይከላከል ሽባ አደረጉት የሚለውን ቁጭት ለመግለጽ ነው። አቶ ሞገስ እንዳሉት ይህ ሁሉ ሲሆን የሚንገበገቡና የሚቆጩ የድርጅቱ አባላት እንደሚኖሩ ጥርጥር የለውም። ያ ቁጣና መቆርቆር አድጎ ከሕዝብ አመጽ ጋር እንደተቀላቀለ አብዛኞች ይስማማሉ።

እንደተባለው ከለወጡ በሁዋላ በአማራ ክልል የሚታየው አለመረጋጋት አሳሳቢ ነው። ይህንን አሳሳቢ ጉዳይ አንድ ሆኖ መመከት ካልተቻለ መከራው እንደሚበረክት ጥርጥር የለውም። የተናጠል ትግልና የእርስ በእርስ ሽክቻ ትርፍ የለውም። በፖለቲከኞቹ ቋንቋ ያሰብት ስፍራ አይደርስም። በመሆኑም ከላይ የተቀመጠው ማመጣጠኛ ሃሳብ እንዳለ ሆኖ፣ ለግዜው የእርስ በርስ ሽክቻን ወደ ጎን በማድረግ በህብረት የክልሉን ሰላም ለማስጠበቅ መጣበቅ ያስፈልጋል። በዚህ ወቅት ስለ ልዩነት ማስላት ህዝቡን ይባስ ተጠቂ ያደርገዋል።  በሞራልም ሆነ በማህበራዊ ቀውስ እንዲደቆስ ያደርገዋል።

አገር ሲረጋ ምርጫ አለ። በምርጫ ህዝብ የሚወስነው ውሳኔ እንደ ከረመው ዘመን በሌብነት የሚጭበረበር አይደለም። ስድቡ፣ የእርስ በእርስ ሽክቻ ፣ መወቃቀስ የዛኔ ከደረስን ለምርጫው ጊዜ ይቀመጥልን። አሁን ባለበት ወቅት የተፈናቀሉትን መርዳት፣ ተጨማሪ መፈናቀል እንዳይኖር መረባረብ፣ የብልጠት ፖለቲካ ማራመድ፣ የብአዴንን ልምድ መቅሰም፣ የሚያሻግር ዓላማና ግብ በመያዝ ” ፖለቲከኛ ” መሆን ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል።

ዝንጀሮ ቅድሚያ መቀመጫዬ እንዳለችው አብን የመጎሻሸም ትግሉን ለጊዜው ጋብ በማድረግ አሁን ቁጭት ከሚያንገበግባቸው የአዴፓ አመራሮችና አባላት ጋር ይህንን ችግር ለማለፍ ሲባል በጋራ ሊሰራ ይገባል። አብን ዓላማው የአማራን ሕዝብ መታደግ ከሆነ ዛሬ ነገ ሳይባል ይህንን ችግር ለምናልፍበትን መንገድ ቅድሚያ ሊሰጥ ይገባል። ወንበር በህዝብ ይሁንታ በጊዜ ገደብ የሚሰጥ በመሆኑ በየትኛውም ጊዜ አይቀርም። ከዚህ ውጭ እርስ በእርስ በመካሰስ ከማያገገም ኪሳራ ላይ እንዳንወድቅ እንጠንቀቅ። በርካታ መስመር ያልያዙ ጉዳዮች ባሉበት ሁኔታ ከህዝብ ይሁንታ ውጪ ወደ መንበር ለመምጣት ሙከራና ቅስቀሳ ማድረግ ማንንም አሸናፊ አያደርግም። ከተሞከረም ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ላናገግም እንወድቃለን የሚል ፍርሃቻ እንዳለኝ ለመግለጽ እወዳለሁ።

ውድ አዲስ ሃይል የሆናችሁ ኣብን አባላት፣ ዛሬ በለውጥ ውስጥ ዳግም ስማችሁን ለማደስ እየሰራቹህ ያላቹህ የአዴፓ አመራሮች፣ በክልሉ የምትንቀሳቀሱ ድርጅቶችና ታዋቂ ሰዎች ጊዜው የህብረት እና የአንድነት በመሆኑ ተደጋግፋቹህ ይህንን ጨለማ ታልፉት ዘንድ እንደ አንድ ተወላጅና ዜጋ እለምናለሁ። ክልሉ ላይ እጃችሁን የምታነሱ ቅጥረኞችም አደብ ግዙ። እጃችሁን ከንጹሃን ላይ አንሱ። ስሜታዊነትን በማስወገድ የአማራ ህዝብ ሰላሙን እንደሚያውጅ አትጠራጠሩ።

መልካሙ አስማማው

ዝግጅት ክፍሉ – ይህ ጽሁፍ የጸሃፊው ሃሳብ እንጂ የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያንጸባርቅም

 

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *