“ብሔርተኝነት አማራጭ የሌለው መድሃኒት ነው እያሉ ስለተጎጂነታቸው ሲተርኩ የሚውሉ የተወጉ ሰዎችን የስቃይ ፎቶ ለመለጠፍ ቀዳሚ ናቸው። ከነሱ መሃል አንድም ሰው ስለማይገደል ምን ቸገራቸው! የፖለቲካ ነጋዴዎች ናቸው። ችግሮችን ለማራገብ አንደኛ፤ አዛኝ ለመምሰል አንደኛ፣ ሌላውን ለመኮነን አንደኛ፣ ጥፋተኞቹ ሁልጊዜ አዴፓ፣ ኦዴፓ፣ ኢህአዴግ፣ የዜግነት ፖለቲካ፣ ፌዴራል ፖሊስ፣ መከላከያ ወዘተ። በእነዚህ ጭንቅላት ነው እንዴ ሰው የሚመራው? ምንም ይሁን ምን የአውሬነት አስተሳሰብን በፖለቲካ መዋቅር ወይም በወታደር ሃይል ማስተካከል አይቻልም። በቻርለስ ዳርዊን ሃሳብ ግዙፍ፣ ጠንካራ ወይም ምጡቅ ስለተሆነ ብቻ ህልውና አይረጋገጥም። ሕልውናን ለማስጠበቅ ከጊዜና ከሁኔታዎች ጋር መለወጥና መጓዝ መቻል ብቸኛው መፍትሔ ነው። ብሔርተኝነት ኋላ ቀር አስተሳሰብ በመሆኑ በዓለም ተሸንፏል። ሌላ ቦታ የለም። ማስቆም ካልተቻለ ከብዙ እልቂት በኋላ በራሱ ይቆማል” ልጅ ግሩምበፌስ ቡክ ገሳቸው የጻፉት ነው።

ከለውጡ በሁዋላ አማራ ክልል ላይ የሚስተዋሉት ጉዳዮች አግባብነት የጎደላቸው ናቸው። ክልሉ ታሟል። ክልሉ በሆያሆዬና በቀረርቶ እየተናጠ ነው። ክልሉ ውስጡ እየነፈረ ነው። በክልሉ ሰላም አሳሳቢ እየሆነ ነው። በክልሉ የሰላም ዋስትና ጥያቄ እየከረረ ነው። ክልሉ በዚህ ከቀጠለ ሙሉ በሙሉ ሊናጋ ይችላል። ይህ ፈጠራ ሳይሆን ገፈት ቀማሹ ህዝብ በገሃድ በየአቅጣጫው የሚናገረው፣ የሚሰለፍበትና የሚያነባበት ጉዳይ ነው።

ከክልሉ ውጪ በ “አጎራባች” ክሎችና በሌሎች ስፍራዎች በሰላም የሚኖሩ የብሄሩ አባላትም እየታወኩ ነው። በማያዋጣ ቀረርቶና ፉከራ በየአቅጣጫው ጠላት እንዲጨመርለት እየሆነ ነው። ከየትኛውም የህበረተሰብ ክፍል ህጋዊ የህዝብ ውክልና ሳይኖር በስልጣን ጥማት ህዝቡን መማገድና የፖለቲካ ትርፍ ለማግበስበስ የሚደረገው ሩጫ ምስኪኖችን ማቅ እያለበሰ ነው። በሚታወቅና በማይታወቅ ማንነት በውል በጥቅም የሰከሩ ከሩቅና ከቅርብ ሆነው በየማህበራዊ ሚዲያው የሚያስታውኩ እርኩሶች የምስኪኖችን ቤት በሃዘን አጥምቀው ” እንታጠቅ” በሚል መዋጮ ለመሰብሰብ ይቀሰቅሳሉ።

በማውቅም ይሁን ባለማወቅ እነዚህን ክፍሎች የሚከተሉ፣ የእነሱን መፈክርና ቀረርቶ እያራቡ፣ እነሱ በአውቶሞቢል እየተንፈላለሱ የሚያሰሙትን የክተት ጥሪ ዜማ የሚያራቡ ሁሉም ምስኪኑን ህዝብ ለከፋ ጥቃት እየዳረጉት ነው። የሌሎች ክፋትና ሴራ ሳያንሰው የአማራ ህዝብ ከውስጡ ወጣን በሚሉ ማቅ ለብሶ እያነባ ነው። ሃዘን ትከሻውን እንዲሰብረውና በልዩ ስትራቴጂ ሲያሽመደምዱት ለኖሩት መሳቂያና መሳለቂያ፣ እንዲሁም የከበሮ ማሟሟቂያ እያደረጉት ነው።

ሰክኖ፣ መርምሮና ወቅቱን አገናዝቦ የሚበጅ መንገድ በመምረጥና በመከተል ” የፖለቲካ ተኩላ” በመሆን ከመስራት ይልቅ በየሚዳው በመትፋት፣ በማቅራራት፣ የሌለ ስዕል በመሳል በባዶ ሜዳ የራሳቸውን ህዝብ የሚበሉና የሚያስበሉ ቢኖሩ አማራ ክልል ውስጥ ናቸው። ራስን አጥርቶ፣ አትራፊ የፖለቲካ ሂሳብ በመቀመር ተንቀሳቅሶ ይህን ለዓመታት የሞት ድግስና የጥላቻ አታሞ ሲመታበት የኖረን ህዝብ ለመታደግ የማይስማሙ ክፍሎች በየትኛው መስፈርት ወገንተኛ ሊባሉ ይችላሉ?

Related stories   ሰበር ዜና – ትህነግ በዲፕሎማሲ ዘመቻ ቀውስ ገጠመው፤ “ በሃሰት መረጃ አሳፈራችሁን ” የቅርብ አጋሮቻቸው

ከለውጡ በሁዋላ ራሱን እንደገና እያደራጀ ያለውን የክልሉን መንግስትና  አመራሮች በማሸማቀቅ ድጋፍ አልባ ማድረግ፣ ግልጽ ባልሆኑ ጉዳዮች ማጠልሸት፣ መዋቅራቸውን መሰባበር፣ ከሕዝብ ጋር መነጠል፣ ክልላቸውን እንኳን መከላከል እንዳይችሉ ሽባ ማድረግ በስፋት የሚስተዋሉ ችግሮች ናቸው። አሳሳቢና እንቅልፍ የሚነሳም ነው። ለጊዜው እስኪረጋ ካለው መንግስት ጋር ልዩነትን በስልት በማራመድ አንድ ሆኖ ከመስራት ይልቅ ጭልጥ ባለ ብሄርተኛነት መንጎድ አዋጪነቱን የሚአስረዳና ማሳመን የሚችል ሃይልም የለም።

አሁን የሚታየው በግብታዊነት ራስን አማራጭና የሕዝብን ሰላም አስጠባቂ ሃይል ለማድረግ የሚደረግ የአካፑልኮ አይነት ፊልም ነው ። ዝም ብሎ ቀረርቶ፣ ሽለላ፣ ውግዘት፣ በሄዱበትና በረገጡበት ሁሉ መናከስ፣ ጠላት ማብዛትና የአዞ እንባ ማንባት ነው የሚስተዋለው። በነበረው የረመጠ ቂምና ጥላቻ ላይ ነዳጅ በማርከፍከፍ ምስኪኑን ህዝብ አሳር ማብላት፣ ማስመታት፣ ማስጨፍጨፍ የትኛውን ወገን እንደሚጠቅም የማይረዱ ክፍሎች እንዴትስ አማራጭ ሆነው ለወደፊቱ ካርድ ይከማችላቸዋል?

አዴፓ / ብአዴን ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት በአብዛኛው ለተፈጠሩበት ህዝብ ደንታ በሌላቸውና ማንነታቸው በማይታወቅ ተላላኪዎች ሲመራ ነበር። ሃፍረት በሌለው መልኩ ከሰውነት ተራ የወረዱ ባንዳዎች የህዝቡን ክብርና ልዕና ሽቅጠውበታል። ለመታገል የሞከሩትን ራሳቸው እየጠቆሙ አስመትተዋል። መካሞች፣ ጉዳዩ ቶሎ የገባቸውና የተጋፈጡ የመኖራቸውን ያህል፣ ተጠፍጥፈው የተሰሩና የሰው ጠረን የሌላቸው  በዕቅድ የተነደፈውን ክልሉንና ህዝቡን ለይቶ የሚያጠቃ ስልት አስፈጻሚ እንደነበሩ አሁንም በዛው አቋማቸው ያሉ አሉ። እነዚህን እሥሥቶች በህብረት ነቅሶ ለማውጣት ቅድሚያ ከመስጠት ይልቅ መግለበለብ መመረጡ ህዝቡን ይባስ ዋጋ እያስከፈለ፣ እስስቶቹም ቆዳቸውን እንዳሻቸው እነዲቀያይሩ እየረዳ ነው።

እንደ ድርጅት ለውጡ እውን ከመሆኑ ዓመታት በፊት ውስጥ ውስጡን በጋመ ትግል ሲያራምዱት ከነበረው የተቀነባበረ አክሳሪ መንገድ ነጻ ለመውጣትም በግንባር ቀደምትነት ዋጋ የከፍሉ አሉ። ተጸጽተው ከቀድሞ መንገዳቸው የተመለሱ አሉ። ካኮረፈው ህዝብ ጎን መቆማቸው፣ ለውጡን እውን ለማድረግ ከለውጥ ሃይሎች ጋር መስራታቸው፣ በገሃድ ሚና ለይተው መንቀሳቀሳቸውንም ማጣጣል አይቻልም። ይሉቁኑም እነሱን ከአድርባዩ በመለየት በአማራ ህዝብ ላይ የተጫነውን ቀንበርና የጥላቻ ዘመቻ በአስተዋይነት፣ በፍቅር፣ በስትራቴጂና፣ አርቆ በሚያልም ዓላማ ለመግፈፍ መትጋት ሲገባ ተመልሶ የተራመጠውን ስትራቴጂ ቆስቁሶ ማንደድ በየትኛው የፖለቲካም ሆነ የብሄርተኛነት ስሜት መረዳት አዳጋች ነው።

ከለውጡ በሁዋላ በተገኘው አጋጣሚ በክልሉ አብን የሚባል ድርጅት ተቋቁሟል። ይህ ድርጅት የአማራ ብሄርተኛነትን በማጉላት ሰፊ ንቅናቄ ፈጥሯል። ይህ ድርጅት የፖለቲካ ስራ እንዳይሰራና ራሱን እንዳያደራጅ የያዘው የለም። ጫና ተደረገብን ሲሉም አይሰማም። ይህ ከሆነ በማስተዋልና ወቅቱን ባገናዘበ መልኩ አደረጃጀታቸውን ወዳታች ማስረግ አስቸጋሪ አይሆንባቸውም። የክልሉ አስተዳደር አብሮ ለመስራት ፍላጎት እንዳለው አስታውቋል። ሲመሰረቱ ጀምሮ ድጋፍ በመስጠት፣ የሚዲያ ደጁን በመክፈት መተባበሩን ሕዝብ አይቷል። ሰምቷል። የራሱን ግምትም ወስዷል። ችግር ካለ በመነጋገር መፍታትና ማስተካከል የሚከብድ አይመስልም።

Related stories   ሰበር ዜና – ትህነግ በዲፕሎማሲ ዘመቻ ቀውስ ገጠመው፤ “ በሃሰት መረጃ አሳፈራችሁን ” የቅርብ አጋሮቻቸው

እውነታው ይህ ከሆነ አብን አዴፓ ላይ ዕለት ከዕለት የሚዘምትበት ምክንያት ግልጽ አይደለም። ጊዜው የምርጫ ዘመቻ የሚደረግበት ባለመሆኑ ክልሉን የሚመራው ፓርቲ መካሙን ከባንዳው የመለየቱ ችግሩ እንዳለ ሆኖ ስራውን እንዳይሰራ፣ መሰናክል መሆኑ ከስትራቴጂ አንጻር ማንን ይጠቅማል? የሚለው ጉዳይ የሰከኑ የህብረተሰቡ ክፍሎችን እያስገረመ ነው።

ራስን አደራጅቶ አማራጭ በመሆን በምርጫ ስልጣን ለመያዝ ከመስራት በዘለለ እግራቸው በረገጠበት ሁሉ ደም የሚፈሰው ለምንድን ነው? በሚል ጥያቄ የሚያነሱ በርካታ ናቸው። የክልሉን ገዢ ፓርቲ መዋቅር መሰባበርና ልምሻ ማድረግ ፖለቲካዊ ፋይዳው ምን ይሆን? በሸዋ፣ በጎንደር፣ በመተከል፣ አማራ እየረገፈ ነው። አማራ በተዘራበት የማጠልሸት ዘር እየተሰቃየ ነው። ሲፈናቀል ኖረ። ሲዘረፍ ኖረ። አሁንም በተመሳሳይ ይሞታል። ይፈናቀላል። ይሰቃያል። እስከመቼ በዚህ ይቀጥላል? ይህ ሁሉ እየሆነ ለፖለቲካ ድል ቡድን ለይቶ መዘላለፍ እንዴትስ ቅድሚያ ይሰጠዋል?

እንደነ አቶ ክርስቲያን አይነቱ ፖለቲከኛ ትናንት “ብአዴን ወይም ሞት” በሚል አብረዋቸው ሲሰሩ ከነበሩት የእናት ፖርቲያቸው መሪዎች ጋር እንዴት በሰከነ መንገድ መነጋገር ይሳናቸዋል? አማራው እንደ ቅጠል እየረገፈ በልዩነት ዘፈን አታሞ መምታት፣ ማሽካካት፣ ደርሶ አዛኝ ለመምሰል የሃዘን መግለጫ ለማውጣት መሸቀዳደም ምን የሚሉት ወገንተኛነት ይሆን?

አዋቂዎችን እንተዋቸው ህጻናት አይሳዝኑም? ወንዶችን እንተዋቸው እናቶች፣ ነፈሰጡር፣ እመጫቶች አያሳዝኑም? ይህ ሁሉ ከሚሆን ስልጣን ቢቀርስ? ስምና ዝና ቢቀርስ? ሁሉም ነገር ቢቀርስ?

ከዛሬ አስራ ሁለት ዓመት በፊት በጉጂ ኦሮሞና በሲዳማ መካከል የወንዶ ገነት አካባቢ ላይ ባለው ከፍተኛ የጫት ገቢ ምክንያት የባለቤትነት ግጭት ተነሳ። ሲኮራኮሙ ቆዩ። አንዴ ሲበርድ፣ አንዴ ሲግል ከረመ። አንድ ቀን ግን እንደዚህ ሆነ። ከሲዳማ የተነሱ በዘፈን ታገዘው እየሸለሉ የጉጂዎችን ቤት አነደዱ። አወደሙ። እየለዩ ሳይሆን በጅምላ አመድ አደረጉት። የደረሰው ጉዳት ክፉ ነበር። ዛሬ መረጃ የማግኛ በር ስለተበረገደ የአሁኑ ቀውስ ይራገባል እንጂ፣ በወቅቱ የደረሰው ቀውስ ክፉ ነበር። ከጀርባ የፖለኢስ አዛዦች፣ አመራሮችና ካድሬዎች እጅ ነበረበት። ከጫት ቀረጥ የሚገኘውን ገቢ ለመብላት ህዝብ ተማገደ። ከርሳም ፖለቲከኞች ህጻናት ሲሞቱ፣ ሴቶች ሲነገላቱና ሃብት ሲወድም ትርፋቸውን ያሰሉ ነበር። መጨረሻ ላይ በህዝበ ድምጽ ወደ ቦታው ኦሮሚያ ተካተተና ነገሩ ተቋጨ። ወደፊት የሚሆነው የሚታይ ነው። ዛሬ እንጃዋር ሲዳማ ሲዳማ የሚሉት ለዚህ ይሆን? ከርዕሴ ላለመውጣት ላቁመው።

Related stories   ሰበር ዜና – ትህነግ በዲፕሎማሲ ዘመቻ ቀውስ ገጠመው፤ “ በሃሰት መረጃ አሳፈራችሁን ” የቅርብ አጋሮቻቸው

ዛሬ መአማራ ክልል የጠራራ ዝርፊያ ገደብ የሚያበጅለት አልተገኘም። ዛሬ አማራ ክልል ተሽከርካሪዎች እንዳሻቸው አይንቀሳቀሱም። ዛሬ አማራ ክልል ተፈናቃዩ በርክቶ ለቁጥር እየታከተ ነው። ዛሬ አማራ ክልል መንግስት ሙሉ አቅሙን ሊጠቀም አልቻለም። ከግራና ቀኝ፣ ከውስጥና ከመካከል ተውጥሮ ለሌሎች የሚመች ዱኩማን ሆኗል። ይህንን የተረዱ እንዳሻቸው ይዘፍኑበታል። የደንሱበታል። ዳግም ወደ ህብረት እንደማይመጣ እርግጠኞች ሆነው ያሽሟጥጡታል። ለክፉም ለደጉም ዝግጅታቸውን አጠናቀው ወደ ስራቸው ገብተዋል። አማራ ክልል እንኳን ወደ ሰራ ገብቶ የህዝብ ጥያቄ ሊያስተናግድ ከራሱ ወገኖች የሚሰነዘርበትን በትርና ማጠልሸት በወጉ መመከት የቻለ አይመስልም። የዚህ ሁሉ ድምር ዛሬ እንደምናየው ሃፍረትና ሃፍረት ብቻ ነው።

ቤኒሻንጉል አማራ በቀስት ይወጋል። በከሚሴና በማጀቴ አማራ ስጋት ላይ ነው። በጎንደር ወኪሉን መግለጽ ባያስፈልግም  አማራው ክፉኛ ተጎድቷል። እርጥባን ለማኝ ሆኗል። ሜዳ ላይ እንደ ፍልፈል ተበትኗል። እድሜ ለዚህ ዘመን ልጆቹ ሃፈረት ለብሷል። እድሜ ለዛሬው ትውልድ በቀዬው አንብቷል። እድሜ ለዚህ ትውልድ በጀግኖች ስም ቀረርቶ እየተከፈተለት አከርካሬው ተመቷል። እድሜ ለዚህ ትውልድ…

ዛሬ እገሌ ከገሌ ሳይባል እጅ ለእጅ በመያያዝ የክልሉን ሰላማና ጤና ማስጠበቅ ቅድሚያ የሚሰጥበት ወቅት ነው። በመደጋገፍ ዳግም ለማበብ አድፍጦና ” ተኩላ” ሆኖ መስራት የሚያስፈልግበት ውቅት ነው። ይህ ካልሆነ ሃዘኑም፣ ውርደቱም፣ ልመናውም፣ ዱላውም፣ ሞቱም ይቀጥላል። ከዚያም ታሪክ ሆኖ መቅረት የመጨረሻው አማራጭ ይሆናል።

የክልሉ ገዢ ፓርቲም የሚቻለውን ሁሉ ወደፊት በመሄድ የማስተባበሩን ስራ ሊሰራ ይገባል። ህዝብ በተልይም ወጣቱ  ሁሉም ወገኖች ወደ ህብረት እንዲመጡ ሊያስገድድ ግድ ይላል። በተራ ቀረቶና በፊስ ቡክ አድማ አንድም እርምጃ መራመድ አይቻልም። ሃዘን በተሰማ ቁጥር ” RIP” የምትሉ፣ ” ያማል” እያላችሁ የምታላዝኑ አቁሙ። የጦርነት አታሞና ቀረቶ የሚያሰሙ፣ እንኳን ጥይት ጮሆ መናገር በሚከለከልበት አገር የሚኖሩትን አዝማቾች ሞግቱ። እንደ ሰው በማሰብ ተከራከሩዋቸው። እንደ ጋማ ከብት ዝም ብላቹህ ሲጭኗቹህ አትጫኑ። ጥንቃቄ ውሰዱ። ሁሉም ሃላፊነት መውሰድ ካልቻለ እንዲሁ እያየነው ተረት እንሆናለን። ከተረት ብናመልጥ ከውርደትና ከመቀጥቀጥ አንወጣም። ቀረርቶና ፉከራ ይቁም። በጩኸት የተሰራ አገር የለም።

ሲቋጭ ከላይ ልጅ ግሩም እንዳሉት ነውና ይታሰብበት።

ሞገስ ሰውየው አዲስ አበባ ፴/፬/፳፩፱

ምስል አልጀዚራ

ዝግጅት ክፍል – ይህን ጽሁፍ የጸሃፊው ሃሳብ እንጂ የዝግጅት ክፍሉን እምነት አያንጸባርቅም

 

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *