በ19ኛው ክፍለ ዘመን በዓለም ላይ ሁለት ትላልቅ ዘመቻዎች ተካሂደዋል። የመጀመሪያው እ.አ.አ. በ1812 የፈረንሳዩ ናፖሊዮን ሩሲያን ለመውረር ያደረገው ዘመቻ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ አፄ ሚኒሊክ እ.አ.አ. በ1896 ዓ.ም የኢጣሊያንን የቅኝ ግዛት ወረራ ለመመከት ያደረጉት የአድዋ ዘመቻ ነው። በእነዚህ ዘመቻዎች የአፄ ሚኒሊክ ጦር በአሸናፊነት የቅኝ ግዛት ወረራን ሲመክት የናፖሊዮን ጦር ደግሞ በሩሲያዎች ተሸነፈ። የአደዋን ድል የነጮችን የበላይነት በማሸነፍ በኢትዮጵያ ስር የተጠቃለሉትን ብሔሮች ከቅኝ አገዛዝ ስርዓት ታድጓቸዋል። በአንፃሩ የሩሲያዎች ድል ደግሞ በናፖሊዮንን ኢምፓዬር (አገዛዝ) ስር የነበሩትን አብዛኞቹን የአውሮፓ ሀገራት ነፃ እንዲወጡ አስችሏል። በአህዳዊ አንድነት ላይ የተመሰረተው የናፖሊዮን አገዛዝ በመላው አውሮፓ በብሔር ፖለቲካ እንዲከፋፈል እና በእርስ-በእርስ ጦርነት እንዲታመስ አድርጓል። የነጮች የበላይነትን መመከት የቻለው በብዙሃንነት ላይ የተመሰረተ አንድነት የዛሬዋን ኢትዮጵያ እንድትመሰረት አስችሏል። ስለዚህ በአህዳዊ አንድነት ላይ የተመሰረተ ስርዓት አውሮፓን ለጦርነት ሲዳርጋት በብዙሃንነት ላይ የተመሰረተው የኢትዮጵያ አንድነት የጋራ ሀገር መስርቷል። አክራሪ ብሔርተኝነት በሚለኩሰው ግጭትና ጦርነት ሲታመስ የነበረው ምዕራብ አውሮፓ ዛሬ ላይ በአውሮፓ ህብረት ስር በትብብርና አብሮነት ላይ የተመሰረተ ሰላማዊ ግንኙነትና ጥምረት መስርተዋል። በትብብርና አብሮነት ላይ የተመሰረተችው ኢትዮጵያ የብሔር ፖለቲካ በሚለኩሰው አክራሪ አመለካከት አማካኝነት ልክ እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ድረስ በአውሮፓ የተከሰተው ዓይነት የእርስ-በእርስ ግጭትና ጦርነት ውስጥ ለመግባት የኋሊት ጎዞ ከጀመረች ግማሽ ክፍለ ዘመን ሆኗታል። በሌላ አነጋገር አውሮፓዊያን የብሔር ፖለቲካ የፈጠረባቸውን ጠባሳ ለመሻር ጥረት ማድረግ ከጀመሩበት ግዜ አንስቶ ኢትዮጵያ ራሷን በብሔር ፖለቲካ ለመጥበስ ቅድመ-ዝግጅት ስታደርግ ቆይታለች። ሲምታታብህ እንዲህ ነው! አውሮፓዊያን በልዩነት ውስጥ አንድነትን በመሻት በአብሮነት ለመኖር ባደረጉት ጥረት ልክ ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ውስጥ ልዩነትን በመሻት ለመለያየት ጥረት ያደርጋሉ። ታላቁ ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን ስለዚህ ጉዳይ ተጠይቆ፣ አበው ኢትዮጵያ ውስጥ ከመቶ አመት በፊት ያደረጉትን አውሮፓዊያን ከግማሽ ክፍለ ዘመን በኋላ በአውሮፓ ህብረት አማካኝነት እያደረጉት እንደሆነ ገልፆ ነበር። በእርግጥ አውሮፓዊያን ከስህተታቸው ተምረው ችግራቸውን ሲቀርፉ ኢትዮጵያዊያን ግን የአውሮፓን ስህተት ለመድገም አበክረው ይጥራሉ። ያደለው ከሌሎች ስህተት ይማራል፣ ያልታደለው የሌሎችን ስህተት ይደግማል!! መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ነው!!!

Related stories   ይልቃል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተለውጡዋል ለምትሉ ተችዎችና ነቃፊዎች!!

Vis seyum Teshome

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *