መገናኛ ብዙኃን ሲያሻቸው መልካም አሳቢ፣ ሲያስፈልጋቸው ደግሞ በጀብደኝነት የተሞሉ በመሆናቸው በወሬ እሽቅድድም መረጃን በማዛባት ወይም ወደ አንድ ወገን ያጋደለ የተቆርቋሪነት ስሜት በመያዝ ሚዛናዊነት የጎደላቸው ሆነው መታየታቸውን የሚናገሩ በርካቶች ናቸው።

ቀደም ሲል በኢትዮጵያ መረጃ ሲሰጡ የነበሩት መገናኛ ብዙኃን ንጉሡን በማወደስ፣ ከዚያም ማርክሲስት ሌኒኒስት ርዕዮተ ዓለምን በመስበክና የአምባገነንነትን የዕለት ተዕለት ድርጊት በመዘገብ ሕዝብ ተሸማቅቆ እንዲኖር ሲያደርጉ፤ ባለፉት 27 ዓመታት ደግሞ በልማታዊ ጋዜጠኝነት ስም የአብዮታዊ/ልማታዊ ዴሞክራሲን ፅንሰ ሃሳብ በማስረፅና የመንግሥትን ሥራዎች በማጉላት ላይ ብቻ ተጠምደው መኖራቸው ይታወሳል።

ይህ የመገናኛ ብዙኃኑ አካሄድ እንደየሥርዓተ ማህበሩ ተፈላጊ ቢሆንም እንኳ አካሄዳቸው የህብረተሰቡን ፍላጎት፣ ዓለም የደረሰበትን የሥልጣኔና የዴሞክራሲ ዕድገት ያማከለ ባለመሆኑ በአብዛኛው ሲወገዙ እንጂ ሲወደሱ አይታይም። መገናኛ ብዙሃኑ የአንድ ወገን መረጃ ብቻ አስተላላፊ በመሆናቸው ተዓማኒነት አጥተው ህዝብን አስፈላጊ ለሆነ ዓላማ ለማንቀሳቀስ ወይም ያልተረጋጉ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ ለማረጋጋት እንዳይቻል አድርጓል።

መገናኛ ብዙኃኑ በጠራ አቅጣጫ አለመመራታቸው፣በተለይም መንግስታዊ የሆኑት ልማታዊ ጋዜጠኝነትን እንደመርህ መጠቀማቸው ክፋት የሌለው ቢሆንም፤ በአተገባበሩ ህዝብ የሚያስፈልገውንና የሚጠቅመውን እኔ አውቅለታለሁ የሚል አስተሳሰብ ማንፀባረቃቸው፣ በመንግስት ስራዎች የሚታዩ እንከኖችን ለመዘገብ ፈራ ተባ የሚል ወይም ለልማቱ አስፈላጊ አይደለም በሚል ሰበብ “ገመና” ደባቂ መሆንን መምረጣቸው፣ አልፎ አልፎ ክፍተቶችን የሚዘግቡትም በመርህ (በግልፅ ኤዲቶሪያል ፖሊሲ) ላይ ተመስርተው መሆኑ የሚፈለገውን ውጤት እንዳያስገኙ አድርጓቸዋል።

ይህ አካሄድም መገናኛ ብዙኃኑን ከፕሮፖጋንዳ መሳሪያነት ለይቶ ማየት እንዳይቻልና አንድ በሙያው የተካነ ፕሮፌሽናል ጋዜጠኛ ቀርቶ ምክንያታዊ አስተሳሰብ ያለው ሰው እንኳ የሚያደርገውን ያህል የበቃ መረጃ ከማስተላለፍ ይልቅ መንግሥትን አመስጋኝነት እንዲነግስ ፣የመንግስት አካላት መግለጫ ካልሰጡበት ዜናን መፈለግና የመረጃ ምንጮችን ማስፋት እንዳይቻል እንቅፋት ፈጥሮ ቆይቷል።

በአንፃሩ ‹‹ነፃ ፕሬስ›› ተብለው መረጃን ለማስተላለፍ የተፈጠሩት የመገናኛ ብዙሃን ሀገራዊና አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ በራሳቸው ምልከታና የመረጃ ምንጭ በመጠቀም ሕዝብን የማደናገር፣ መንግሥትን ጫና ውስጥ የመክተት፣የግል የፖለቲካ አመለካከትን የመጫን ፍላጎት፣ የጠሉትን አካል የማዋረድ፣ ሃሳብን የማራከስ ተግባራት ውስጥ መሰማራታቸው የአደባባይ ሃቅ ቢሆንም፤ በጥሩ ሁኔታና በተገቢው መንገድ መረጃን ለሕብረተሰቡ ያስተላልፉ የነበሩም አሁንም ያሉ መኖራቸው ግን አይዘነጋም።

እ.አ.አ. በ2016 እንደ ደቡብ ምሥራቅ እስያ አገር ምንያማር ዜጎች የማይቆጠሩት የሮሂንጊያ ማኅበረሰቦች በአገሪቱ ወታደሮች በተፈጸመባቸው ጥቃት ከ700 ሺሕ በላይ የሚሆኑት ቤት ንብረታቸውን ጥለው ሲሰደዱ፤ ከአሥር ሺሕ በላይ ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል። ይህ የሆነበት ምክንያት ደግሞ መገናኛ ብዙኃን በአግባቡ የሕዝቦችን ማህበራዊ ትስስር የሚያጎላ ሥራ ከመስራት አፈግፍገው፤ ፌስ ቡክ የተባለው ማህበራዊ ሚዲያ የበላይነቱን በመያዙ ፅንፈኞች የመረጃ ማዛባት ተግባር በመፈፀማቸው ነው።

እ.አ.አ. 1994 ዓ.ም ሩዋንዳውያን በታሪካቸው አይተውት የማያውቁትን፣ በአለምና በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ በአስከፊነቱ ሲነገር የሚኖረውን መከራ ያመጣባቸው ለቱትሲዎችና ለሁቱዎች መተላለቅ ረዘም ላለ ጊዜ ሆነ ተብሎ በውጭ ኃይሎች ሲከናወን የቆየ የጥፋት ተልዕኮ በመሆኑ ነው። ይህ ተግባርም የመገናኛ ብዙኃን ውጤት መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም።

በተለይም በአንዳንድ የአፍሪካና የአረብ አገራት እንደተስተዋለው ማኅበራዊ ሚዲያው በሁለት ወገን የተሳለ ሰይፍ መሆኑን በኢትዮጵያም ተግባራዊ ለማድረግ የቻለውን ያህል ጥረት እያደረገ ይታያል። ማኅበራዊ ሚዲያው ጠቃሚ ማስረጃዎችን ለማቀበል፣ ለማዝናናት፣ አገርንና አካባቢን ለማስተዋወቅ መጥቀሙ እንዳለ ሆኖ፤ ጥላቻ፣ ዘረኝነትን፣ ሃይማኖትና ብሔርን ለማንቋሸሽ፣ የአንድ ወገን በደሎችን ብቻ የሚያጎሉ መልዕክቶችን ለማስተላለፍ፣ ለዕልቂት ለማነሳሳት ጥቅም ላይ ለሚያውሉት እያገለገለ ይገኛል።

ማህበራዊ ሚዲያው ለሀገራዊ ዕድገት የሚበጅ አጀንዳ ላለው፣ የህብረተሰብን አብሮ የመኖር ቱሩፋት ለማበልፀግ ለሚተጋ፣ በሕብረተሰቡ ውስጥ ያሉ የተለያዩ አስተሳሰቦችን በማንሸራሸር ትውልዱ ጠቃሚ መረጃዎችን እንዲያገኝ ለሚፈልግ ጠቀሜታው የጎላ ነው።

ይሁን እንጂ የህብረተሰብን በጋራ መኖር ማየት የማይፈልጉ ኑሮአቸውን በውጭ ያደረጉም ሆኑ ኃላፊነት የማይሰማቸው የማኅበራዊ ሚዲያ ጦረኞች፣ እነርሱ ላይ ጉዳት እንደማያስከትል የተረዱትን እኩይ ተግባር ሁሉ ፈፅመው ሰዎች እየሞቱ፣ ንብረቶች እየወደሙና በርካቶች ከቀዬአቸው እየተፈናቀሉ በምቾት የጥፋት ሥራዎቻቸውን እያከናወኑ ናቸው።

እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች ከልማታቸው በተጓዳኝ ዴሞክራሲ ሊጎናፀፉ እንደሚገባ ቢታመንም፣ ከሰላም የሚበልጥ የለምና የሕዝቦችን አብሮ የመኖርና ሰላም የሚያደፈርስ ሁኔታ በዴሞክራሲ ሥም ሲከሰት በቸልታ ሊታይ አይገባም።

በዚህ ወቅት አገሪቱ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በሌሎች ችግሮቿ ተወጥራ ባለችበት ሁኔታ ኃላፊነት በጎደለው አካሄድ በስሜታዊነት መነዳት ዛሬ እንደልብ የሚፈነጭበትን መድረክ ሙሉ በሙሉ ሊያሳጣ የሚያስችል ስህተት በመፈፀም ራሳችንም ተጎጂ የምንሆንበት ደረጃ ላይ የሚያደረሰን ይሆናል።

የመንግሥት ቅድሚያ ድርሻ የዜጎቹን የደኅንነት የመጠበቅ በመሆኑ አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል ማንኛውንም ስጋት ሊያስወግድ ይገባል። መገናኛ ብዙኃኑም በአገሪቱ የተፈጠረውን የመገናኛ ብዙኃን መብት በመጠቀም ህብረተሰቡን ለጭንቀት፣ ለመፈናቀል፣ ለሕይወት መጥፋት መንስዔ የሚሆኑ ዘገባዎችን ከማራገብ፣ አጉል የፖለቲካ ተንታኝና አስተንታኝ ከመሆን አባዜ በመላቀቅ የሕዝብን አብሮ የመኖር እሴቶችን የሚያስጠብቁ መልካም አስተሳሰብን የመገንባት ሥራ ላይ ማተኮር አማራጭ የሌለው ወቅታዊ ጉዳይ ሊያደርጉት ይገባል።  

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 25/2011 editorial

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *