ስፖርት ብሄራዊ ስሜትን በማጠናከር አሊያም በማደብዘዝ ረገድ ሚናው ግዙፍ የሆነ ትልቅ ማህበራዊ ክንውን ነው። በብሄራዊ ስሜት ግንባታ ውስጥ የስፖርቱን የተለያዩ ሚናዎችን ያሳዩ በርካታ አጋጣሚዎች ይጠቀሳሉ። ስፖርት ብሄራዊ ስሜትን የመገንባት አቅምን ለመፍጠር የሚያ ስችል ስለመሆኑ እ.ኤ.አ የ2013ቱ የደቡብ አፍሪካ ዋንጫ ትልቁ ማሣያ ይሆናል።

የዋልያዎቹ ከ31 ዓመታት በኋላ በአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ላይ መሳተፍ በእግር ኳሱ ውስጥ የብሄራዊ ስሜት ማነሳሳትን ሲፈጥር ታዝበናል። ኢትዮጵያዊነትን ከገባበት የተቀዛቀዘ ስሜት ውስጥ አውጥቶ ከዳር እስከ ዳር በሞቀ የአንድነት መንፈስ ሲያስፈነጥዝም ተመልክተናል። የልዩነት ነጋሪት ጉሰማውን ድምጽ የዋጠና የአንድነቱን ድምፀት ያጎላም ጭምር እንደነበር አይተናል። ይህ አጋጣሚ ስፖርት የወንድማማችነት፣ የወዳጅነትና የአንድነት ማጠናከሪያ አብነት ነው እየተባለ ሲነገር የነበረውን በተጨባጭ አሳይቷል።

ከሰሞኑ አዲስ አበባ ውስጥ አንጋፋው የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ የተንፀባረቀው ሁኔታም ይህንኑ የሚያጠናክር ነው። «የስፖርት ጨዋነት ምንጮች» በሚል መሪ ቃል በሸራተን ሆቴል ለሁለት ቀናት በተካሄደው የምክክር ጉባዔ ላይ በርካታ ቁምነገሮች ተነስተዋል።

በዚሁ ወቅት የሠላም ሚኒስትር ዴኤታ አልማዝ መኮንን እንዳሉት ስፖርት ለሠላም ዘብ የመሆኑን ጉዳይ በተገቢው መጠቀም ካልተቻለ በተቃራኒው ሲውል የሠላም ፀር መሆኑ አይቀሬ ይሆናል።

«ስፖርት ትልቅ የሠላም ምንጭ ነው። ስፖርት በአንድ አገር ሠላም ሲደፈርስና መረጋጋት ሲታጣ ወደ ቀደመው ሁኔታ ለመመለስ ትልቅ አቅም አለው። ስፖርት የታመመን ፖለቲካ የማከም ከፍ ያለ ስጦታም አለው» ብለዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ የዓለም ነባራዊ ሁኔታን መሠረት በማድረግ ይህንን ይበሉ እንጂ፤ በኢትዮጵያ እየተስተዋለ ያለው አሁናዊ ሁኔታ ከዚህ ፍጹም ተቃራኒ ሲሆን እየተስተዋለ ነው። በተለይ በእግር ኳሱ ስፖርት ለሠላምና ለጤንነት የሚለው መርህ ተገልብጦ ለሁከትና ብጥብጥ ምንጭ ከሆነ ሰንበትበት ብሏል። ይህንኑ መነሻ በማድረግ ሚኒስትር ዴኤታዋ ለችግሩ ዘላቂ የሆነ መፍትሄ በመስጠት ሂደቱን መስመር ማስያዝ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የአገሪቱ እግር ኳስ ክፉኛ በሆነ መልኩ «ዘረኝነት» በሚባል ወቅት አመጣሽ በሽታ ሽምድምድ ብሎ ከስታዲየም ውጪ ተኝቷል። በተለይ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክፉኛ ታሟል። ይህ ሁኔታ በዚህ ደረጃ ከቀጠለ እስከ ሞት ሊያደርሰው እንደሚችል በመድረኩ ላይ የታደሙ የዘርፉ ባለሙያዎች ምክረ ሃሳባቸውን ለግሰዋል።

ኢንተርናሽናል ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ በአገሪቱ እግር ኳስ ውስጥ ከዳኝነት ጋር ተያይዞ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ይስተዋሉበታል። እነዚህም ለስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል መንስዔ ይሆናሉ ሲሉ ገልፀዋል። ፖለቲካ እና እግር ኳሱ መለያየት እንዳለበት አፅንኦት የሰጡት ኢንተርናሽናል ዳኛዋ ዘረኞችን፣ ጎሰኞችን፣ ፖለቲከኞችን ከስፖርቱ ለይቶ መዳኘት አቅቶናል ሲሉ ችግሩ የቱን ያህል ውስብስብ ደረጃ ላይ መገኘቱን ጠቁመዋል።

የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር የቦርድ ሊቀመንበር አቶ አብነት ገብረመስቀል የሥነ ምግባር መጓደልና ሥርዓት አልበኝነት እግር ኳሱን ከመጉዳት አልፎ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በጎሣ፣ በዘር፣ በሃይማኖትና በፖለቲካ አመለካከት ላይ ያተኮሩ ልዩነቶችና መቆራቆዞች እዚህም እዚያም እየተበራከቱ መጥተዋል፤ ስፖርት ከፍ ያለ የሞራል ልዕልናን የመጠየቁን ያህል በአግባቡ ካልተመራ በተቃራኒው ነውጠኝነትና ሥርዓት አልበኝነት ሊነግስበት ይችላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሣይያስ ጂራ በሰጡት አስተያየት እግር ኳሱ የሌላ አጀንዳ መናኸሪያ እየሆነ መጥቷል። ከስፖርታዊ መርህ ውጪ «የእከሌ ዘር ተሸነፈ፣ ይኸኛው ብሔር አሸነፈ» በሚል ጤናማ ያልሆነ አስተሳሰብ ላይ ደርሰናል ሲሉ የችግሩን አሳሳቢነት ገልፀዋል።

አሰልጣኝ መሠረት ማኔ በበኩላቸው በስፖርቱ አደረጃጀት ላይ ትልቅ ክፍተት መኖሩን በመጥቀስ፤ ስፖርቱ በሙያተኞች አለመመራቱ ሌላው መሠረታዊ ችግር እንደሆነ ጠቁመዋል።

የባህል ቱሪዝምና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሐብታሙ ሲሳይ «የመንግሥት የስፖርት ተቋማት ግንኙነት እስከምን ድረስ» በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጽሁፍ ክለቦች በፖሊስ፣ በመከላከያ፣ በከተማ አስተዳደር፣ በማህበር እና መሰል አደረጃጀቶች እየተመሩ መገኘታቸው ለስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ተፅዕኖ ፈጥሯል ብለዋል። አንድ ክለብ ምን ምን መስፈርቶችን ማሟላት እንዳለበት በግልፅ ተለይቶ መቀመጥ ይገባዋል። ወጥ የሆነ ሕግም ያስፈልገዋል፤ ይህም አለመኖሩ ክፍተት መፍጠሩን አስረድተዋል።

የዘረኝነትና ብሄርተኝነት በሽታ ውስጥ የሚገኘው የኢትዮጵያ እግር ኳስን ለመታደግ በስፖርታዊ እንቅስቃሴ ውስጥ የዘር ልዩነት እንዲጠፋ፣ የኦሊምፒክና የዓለም አቀፍ የስፖርት ማኅበራት ደንብና መመሪያዎች እንዲከበሩ፣ ብሔርን መሠረት አድርገው የሚቋቋሙ ክለቦች ስማቸውን እንዲቀይሩ፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴን ጨምሮ ሌሎችም ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች መሪዎቻቸውን በችሎታና ብቃት ላይ ተመሥርተው እንዲመርጡ፣ ስፖርት በትምህርት ቤቶችና ዩኒቨር ሲቲዎች እንዲስፋፋ የመድረኩ ተሳታ ፊዎች ጠይቀዋል።

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 23/2011

በዳንኤል ዘነበ

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *